በኮንሶ ዞን በተፈጠረ ግጭት ሠባት ሰዎች ሞቱ፣ 800 መኖሪያ ቤቶች በእሳት ወደሙ

በኮንሶ ዞን በተፈጠረ ግጭት ሠባት ሰዎች ሞቱ፣ 800 መኖሪያ ቤቶች በእሳት ወደሙ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በደቡብ ሕዝቦች ኢትዮጵያ ክልል በተለይም በኮንሶ ዞን በሚቀሰቀሱ ግጭቶች የሰው ሕይወት በከፍተኛ ሁኔታ እየጠፋ እንደሚገኝና ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ መኖሪያ ቤቶችም በእሳት እየወደሙ መሆናቸው ተሰማ።

በአካባቢው ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ንጹሃን ዜጎችን የቀጠፈ ግጭት በተደጋጋሚ ቢቀሰቀስም የክልሉ መንግሥትም ሆነ የፌደራል መንግሥቱ ችግሩን ለመቅረፍ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ አልቻለም ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው።
በደቡብ ክልል በኮንሶ ዞን እና በአሌ ልዩ ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ግጭት ከሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም አጋማሽ ወዲህ ብቻ ከ800 በላይ መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንዲቃጠሉ፣ የሰው ሞትና የአካል መጉደል አደጋ እንዲከሰት አድርጓል ነው የተባለው።
መንግሥት በጸጥታ ኃይሉ አማካይነት እርምጃ አለመውሰዱን ተከትሎ ካለፈው ቅዳሜ ወዲህ በተቀሰቀሰ ግጭት የ7 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ሸገር ራዲዮ ዘግቧል።
የኮንሶ አካባቢ አሁንም በውጥረት ላይ መሆኑንን የገለጹት የአካባቢው ተወላጆች በስፍራው በተፈጠረውና መብረድ ባልቻለው ግጭት ምክንያት በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸውንና አብዛኞችም መኖሪያቸውን ለቅቀው ለመሰደድ መገደዳቸውን ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY