ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በተገኙበት ሲከበር የነበረው የኢሬቻ በዓል፤ ዘንድሮ የኮቪድ -19 ወረርሽኝን ከግምት ባስገባ መልኩ እንደሚከበር አባገዳዎች ዛሬ አስታወቁ።
የሆረ ፣ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል መስከረም 23 ቀን 2013 ዓ.ም የሚከበር መሆኑን እና የሆረ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል ደግሞ መስከረም 24 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚከበር አባገዳዎቹ በመግለጫቸው ላይ ጠቁመዋል።
በበዓሉ ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ቁጥር በሽታውን ለመከላከል በሚያመች መልኩና የጤና ባለሙያዎች በሚሰጡት ምክር መሰረት የሚወሰን ነው በሚል አባገዳዎቹ የገለጹ ቢሆንም ፤ የሀጫሉ ግድያን ተከትሎ በተነሳው ኹከት ላይ እንደታየው ከኦሮሚያ ክልል ፈልሰው ወደ አዲስ አበባ ለረብሻ የመጡ መንጋዎችም ሆኑ በሌሎች የኦሮሚያ ዞኖች የታዮ ተቃውሞዎች ሙሉ ለሙሉ ጥንቃቄ አልባ መሆናቸው አሁንም በአዲስ አበባ ነዋሪ ዘንድ ስጋትን ፈጥሯል።
የገዳ ሥርዓት ባለቤት የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ የአባገዳዎችን ጥሪና የጤና ባለሙያዎችን ምክር ተከትሎ በዓሉን እንዲያከብር አባገዳዎቹ በመግለጫቸው መልእክት ቢያስተላልፉም ፤ አሁን ላይ የኦሮሞ ፖለቲከኞች መታሰርና ከፊንፊኔ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ በዓሉ አከባበር ላይ ልቅ የሆነ አሠራር ከጸጥታ ኃይሎች እስከ ከከተማዋ ባለሥልጣናት ድረስ በውስጥ ትእዛዝ ሊተገበር ይችላል ተብሎ ተገምቷል።