ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የ4 ኛ ዓመት ህክምና ተማሪ የነበረችውን ሀይማኖት በዳዳን በመግደል ወንጀል ጥፋተኛ የተባለው ደግነት ወርቁ በ21 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ በፍርድ ቤት ተወስኗል።
የቅጣት ውሳኔውን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የከባድ ግድያና የውንብድና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሽ ደግነት ወርቁ በግንቦት 17 ቀን 2012 ከቀኑ 11:00 ሰዓት አካባቢ የ4ኛ ዓመት ህክምና ተማሪ የነበረችው ሀይማኖት በዳዳ በጥቁር አንበሳ እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፋርማሲ ላብራቶሪ ክፍል ስትገባ ተከሳሹ ተከትሎ በመግባትና የክፍሉን በር ከውስጥ በመቆለፍ ያለሽን አምጪ ብሎ በማስፈራራት ቦርሳዋን አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ላፕቶፕ ኮምፒዩተር በመቀማትና አይፎን ሞባይል ስልኳን ፖተርን አልከፍትም ስትለው መሬት ላይ ገፍትሮ በመወርወር አንገቷን በቢላ በአሰቃቂ መልኩ ጥቃት በማድረስ ህይወቷ እንዲያልፍ አድርጎል ሲል ዓቃቢህግ በ1996 የወጣውን የወንጀል ህግ 671 ንዑስ ቁጥር 2 ስር ያለውን ድንጋጌ በመተላለፍ በከባድ ውንብድና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
በጊዜ ቀጠሮ ምርመራ ወቅት ወንጀሉን መፈጸሙን አስረድቶ የነበረው ተከሳሽ ደግነት ወርቁ ክሱ ከደረሰው በኋላ ወንጀሉን አልፈጸምኩም ማለቱን ተከትሎ ከሳሽ ዓቃቢ ህግ ወንጀሉን ለመፈጸሙ የሚያስረዱ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቆርቦ ማሰማቱ ይታወሳል።
ፍርድ ቤቱም በቀረበው ማስረጃ የግድያ ወንጀሉን መፈጸሙን ተረጋግጧል ሲል በጥቅምት 11 ቀን 2014 የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎበት ነበር።
ይሁንና ፍርድ ቤት በድጋሚ ለቅጣት ውሳኔ ለዛሬ በሰጠው ቀጠሮ በተሟላ ዳኛ ተሰይሞ ዓቃቢህግ በዕድሜ ልክ እስራት ይቀጣልኝ ሲል ያቀረበውን የቅጣት ማክበጃ ውድቅ በማድረግ የተከሳሹን የመድሐኒት ፈጠራ ውጤት ማስረጃና የቀደመ የወንጀል ሪከርድ እንደሌለበት የቀረበ የቅጣት ማቅለያን በመያዝ በ21 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ሰቷል።