ለግዜር የተፃፈ ደብዳቤ || አሌክስ አብርሃም

ለግዜር የተፃፈ ደብዳቤ || አሌክስ አብርሃም

እንደምነህ እግዜር

ሰማይ ቤት እንዴት ነው
እመጣለሁ ብለህ ቆየህሳ ምነው?

እኛማ…..
ለእልፍ አእላፍ አለቃ… ማመልከቻ ፅፈን
ለወፈ ሰማይ ህዝብ …መድረክ ላይ ለፍፈን
ፆለት ቤታችንን ….እኛው ላይ ቆልፈን
የምድር አተካራ …..ህግጋቱን አልፈን
ደብዳቤ ላክንልህ፤

አይንህን ካየነው ሁለት ሽ ዘመን እንደቀልድ አለፈ
የመምጣትህ ተስፋ እየኮሰመነ መቅረትህ ገዘፈ
እንደውም እንደውም…
‹‹በመጣለሁ ተስፋ ሁለት ሽ ዘመን ቀጥሮን ከጠፋ
በቀጠሮው ሰአት መምጣት ከተሳነው
‹‹እግዜር አበሻ ነው›› እያሉ ያሙሃል!!

እኔ ምን አውቃለሁ…
አመስግነው ሲሉ እልልታ የማቀልጥ
ቃሉን ስማ ሲሉኝ …ሰባኪው እግር ስር በደስታ እምቀመጥ
እግዚኦ በሉ ሲባል …እንባየን የማፈስ
ሃሌ ሉያ ሲሉኝ …በሳቅ ልቤ እሚፈርስ
ምናምኒት እውቀት ውስጤ ያልፀደቀ
እንበረከክበት ጉልበቴ ያለቀ
እኔ ምን አውቃለሁ…

ግን አንተ ደህና ነህ?
ከምር እንደሚያሙት ምፅአት ቀረ እንዴ ?
የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አትከፋም አንዳንዴ!

ከሆነስ ሆነና ሰማይ ቤት እንዴት ነው?
አብረሃም ሰላም ነው…
እዛስ ቤት ገነባ ዛሬም በድንኳን ነው ?
እኛማ ይሄውልህ…
በቤት ኪራይ ችንካር እየተሰቀልን
‹‹ኤሎሄ›› እንላለን ጎጆ እንድጥልልን….
ወደላይ ገነባን ወደጎን አሰፋን
ወደላይም ከላይ ወደጎንም ከጎን እ ን ደ ጉ ድ ተገፋን
ቤት ለእንግዳ ማለት ጭራሹኑ ጠፋን !!

አባታችን ሙሴ እነዴት ነው ለክብሩ
ውቂያኖስ መክፈያው ደህናናት ብትሩ?
እኛማ ይሄውልህ….
እንጀራ ፍለጋ ባህር ስናቋርጥ
የተስፋዋን ምድር አሸዋ ሳንረግጥ
የትም ውሃ በላን የትም አሳ ላሰን
ን ገ ር ል ን ና ብትሩን ያውሰን ?!

እናልህ እግዜር ሆይ….
ከተስፋዋ ምድር ወደሌላ ተስፋ አለን እየኳተን
መሄጃው ሲገርመን መመለሻ መንገድ መቆሚያ ቦታ አጥተን…!
ላባታችን ሙሴ እንደምትልልን…
‹‹የመሄድ ዘመን ነው ባህር የመሻገር
‹‹ዱላህን ላክልን›› ብሎሃል በልልኝ!!

ሰማይ ቤት እንዴት ነው? ….ዳዊትስ ደህና ነው?
ዛሬም ይዘምራል …ዛሬም ይፎክራል ?
ሰላም ነው ጠጠሩ …. ሰላም ናት ወንጭፉ?
እዛስ አቅል ገዛ ጎሊያድ ተራራው ጎሊያድ ግዙፉ?
እልፍ አላፍ ጎሊያድ ከቦን ሲደነፋ
ወንጭፉን ጠቅልሎ ምነው ዳዊት ጠፋ ?
ብሎሃል በልልኝ!!
ለረከሰ ጠጠር ለሞላ ወርዋሪ
‹‹ወንጭፍህን ስጠው ለዚህ ታሪክ አውሪ››
ብለህ እዘዝልን!!

እንዴት ነህ ጌታ ሆይ… ሰማይ ቤት እንዴት ነው?
የሙሴ አልጋ ወራሽ እያሱ ሰላም ነው….?
ያቆማትን ፀሃይ ግቢ ቢላት ምነው?!

ያው እንደምታውቀው
አስራ ሶስት ወራት ነው ፀሃይ የምንሞቀው…
ኧረ ፀሃይ በዛ
ኧረ ፀሃይ በዛ
ኧረ ፀሃይ በዛ

የመጣው ወር ሀሉ ፀሃይ እያዘለ
የተሸመው ሁሉ ‹ፀሃይ ነኝ› እያለ
ያስራ ሶስት ወር የግዜር ፀሃይ
ያስራ ሶስት ወር የሰው ጀምበር
ባቃጠላት ምድጃ አገር
ምን ታምር ሊኖር ይችላል ፀሃይ ሁኖ እንደመፈጠር!!
ኧረ እግዜር በናትህ….
ኧረ እግዜር በናትህ…በጭንቅ አማላጇ
ባዘለህ ጀርባዋ ባቀፉህ እጆቿ
ወይ ዝናብ ላክልን ወይ ዝናብ ሁነህ ና
ሙቀት ገደለና!!

እናልህ እግዜር ሆይ ማጣፊያው አጥሮናል
ስም ያለው ሞኝ ነው ሁሉም ይጠራናል…
ጳውሎስ ሲሉን …አቤት
ጴጥሮስ ሲሉን …ወይየ
ይሁዳ ሲሉንም አቤት እንላለን
ስማችንን ሸጠን …ሰላሳ ጭብጨባ እንቀበላለን!
ስንቱ ባለካባ ክብርህ የተሰጠው
ለሰላሳ ፍራንክ ለተራ ጭብጨባ አደራህን ሸጠው !

ተወው የኛን ነገር …ሰማይ ቤት እንዴት ነው ….
ሂዋንስ ደህና ናት?
ያው የልጅ ልጆቿ በግሯ ተተክተው
የፍሬው ሲገርምህ ግንዱንም አንክተው
ለፍጥረተ አዳም ባይኑ ያገምጡታል
ሰይጣንም ደህና ነውኑሮ ተስማምቶታል….
ሰውን ለማሳሳት ላይ ታች ማለት ትቷል
ሳይጠራው የሚጎርፍ ህዝብ በዝቶለታል…!
ኧረ እግዜር በናትህ በጭንቅ አማላጇ
ባዘለህ ጀርባዋ ባቀፉህ እጆቿ
ወይ ዝናብ ላክልን ወይ ዝናብ ሁነህ ና
ሙቀት ገደለና!!
(እናት ፍቅር ሐገር ከሚለው የግጥም መፅሃፌ ገፅ 9 የተወሰደ)

LEAVE A REPLY