የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 18 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 18 ቀን 2011 ዓ.ም

ጃዋር መሐመድ ከፌስ ቡክ ገጹ ላይ ጽሑፎቹን ማጥፋት ጀመሯል

ረቡዕ በተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎችን ተከትሎ የተፈጠሩ ግጭቶች የብሔርና የሃይማኖት መልክ ይዘው ለቀናት ከቀጠሉ በኋላ አሁን ላይ መርገብ ጀምረዋል::ከ67 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ህይወት ከቀጠፉ በኋላ በድርጊቱ ተሳትፈዋል የተባሉ ተጠርጠሪዎች እየተያዙ መሆናቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው::

በትናንትናው ዕለት በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ሰልፎች እንደሚካሄዱ የሚገልጹ መልዕክቶች መውጣታቸውን ተከትሎ ዛሬ ሰኞ ግጭቶች ሊኖሩ ይችላሉ ግምቶች በብዙዎች ዘንድ አሳድሮ ነበር::

ይሁንና ራሱን የኦሮሞ ሕዝብ ብቸኛ አዛዥ አድርጎ የሾመው ጃዋር መሐመድ ለዛሬ ታስቦ የነበረውን አመጽ በምን ምክንያት እንደሆነ ባይታወቅም እንዳይካሄድ ትዕዛዝ በመስጠቱ ቀርቷል::

“እኛ ብንፈልግ የኦሮሚያ ወጣቶች አመጽ እንዳይቆም ማድረግ እንችላለን” በማለት አቅሜን በአደባባይ አሳይቻለሁ በማለት የፎከረውና በአንጻሩ ሚሊዮን ወጣቶች ከእሱ በተቃራኒ ሲቆሙ በድንጋጤ የራደው ጀዋር መሐመድ ጀሌዎቹ የፈጸሙትን አሳፋሪ ግድያና ዕልቂት ለማመን ያለሞከሩን ያህል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋፊ የኦሮሞ ተወላጆች አማካይነት የጣለውን ወሳኝ ነጥብም ላለመቀበል ሲሞክር በመስተዋል ላይ ነው::

ትናንት ምሽት በፌስ ቡክ ገጹ ” ቄሮዎች ሰልፍ እንዳትወጡ፣ መንገድም እንዳትዘጉ” በማለት የዛሬውን አመጽ ያስቀረው ጃዋር መሐመድ ዕውነት ለኦሮሞ ወጣቶች አዝኖ ሳይሆን አሁን ባለው የኃይል አሰላለፍ የኦሮሞ ተወላጆች ለሁለት ከመከፈላቸው ባሻገር የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የማያዳግም ዕርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ በመሆናቸው ፍላጎቱ መና እንደሚቀር በመገንዘቡ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ::

ጃዋር መሐመድ ከሰሞኑ በጠራው የድረሱልኝ የአመጽ ጥሪ ለደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ተጠያቂ መሆኑን የሚገልጹ ጥያቄዎች መበራከታቸውን ተከትሎ አክቲቪስቱ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲጠቀምባቸው የነበሩ ግጭት ቀስቃሽ ጽሑፎቹ መሀል የተወሰኑትን ከፌስ ቡክ ገጹ ላይ ማንሣት ወይም መሠሰዝ መጀመሩን ከትናንትና ጀምሮ ለመታዘብ ችለናል::

ግለሰቡ ከዚህ ቀደም የጻፋቸውን ማነሳሻዎች ከይፋዊ ገጹ ላይ ለማንሳት ይሞክር እንጂ በወቅቱ ሼር በማድረግ ወይም ኮፒ በማድረግ እንቅስቃሴውን ሲተቹና ሲደግፉ ከነበሩ ከበብዙ ሺኅ በሚቆጠሩ ሰዎች ዘንድ መኖሩ ይታወቃል:: በተለይም የግለሰቡን እንቅስቃሴ በሚከታተለው የመረጃና ደሕንነት ቢሮ ውስጥ እነዚህ ጽሑፎች በማስረጃነት በበቂ ሁኔታ ተደራጅተው ተቀምጠው ሊሆን ይችላል የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ አለ::

በሌላ ዜና ሠሞኑን በግጭት ውስጥ የከረሙት የኦሮሚያ ክልል የተለያዮ ከተሞች ዛሬ ላይ የተሻለ መረጋጋት እንደታየባቸው ቢቢሲ የተለያዮ ነዋሪዎችን በማነጋገር ዘግቧል:: መረጃውን ከተጨማሪ ጥቆማዎች ጋር በማጣመር በዚህ መልኩ አቅርበንላችኋል::

                     ሐረር

በፍቅር ተምሳሌቷ ሐረር ከተማ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ዛሬም በከተማዋ የነበረው እንቅስቃሴ መቀዝቀዙን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ትምህርት ቤቶች አሁንም ዝግ ሲሆኑ ወደ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተገልጋዮች ስለማይታዩ ጭር እንዳሉ ውለዋል:: አብዛኛው ሱቆች የተከፈቱ ቢሆንም በጸጥታ ስጋት ሥራ ያልጀመሩ ሱቆች በአንጻሩ ዝግ ሆነው ውለዋል።

በከተማዋ ያሉ መንገዶች እምብዛም ተሽከርካሪዎች ስለማይታዩባቸው ጭር ማለታቸውን የጠቆሙት ነዋሪዎች፤ የጸጥታ አካላትም በከተማዋ እየተዘዋወሩ ጥበቃ እያደረጉ እንደሆነ አረጋግጠዋል:: የጸጥታ አካላት ስለትም ሆነ ዱላ ይዞ መንቀሳቀስን ከልክለዋል። እነዚህን ቁሶች ይዘው ከሚገኙ ሰዎች ላይ እንደሚቀሙ እና ሰልፍም ሆነ ግጭት በዛሬው ዕለት አልታየም::

                         ሞጆ

ዛሬ ሰኞ ጠዋት በሞጆ ከተማ በተከሰተ ሁከት ሁለት ሰዎች በጥይት ተመተዋል ተብሏል።

በከተማዋ ‘የታሰሩ ሰዎች ከእስር ይለቀቁ’ በማለት ሰልፍ የወጡ ሰዎች ከመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች ጋር ተጋጭተው በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የከተማው ከንቲባ ወ/ሮ መሰረት አሰፋ  ማረጋገጫ ሰጥተዋል ። ቅዳሜ ሌሊት ላይም በከተማዋ በምሽት ሰልፍ ተካሂዶ እንደነበርም አስረድተዋል።

“ቅዳሜ ሌሊት ‘ቤተክርስቲያን ተቃጥለ’ የሚል ወሬ ተናፍሶ ሌሊቱን ሁከት ከመፈጠሩ ባሻገር በንብረት ላይ ጉዳት ደርሶ ነበር” ብለዋል። ቅዳሜ ሌሊት ቤተ-ክርስቲያን ተቃጥሏል እየተባለ የተናፈሰው ወሬ ሃሰት መሆኑን እና ይህ የተደረገው “በከተማው ሆን ተብሎ ረብሻ ለመፍጠር” ታስቦ መሆኑን ከንቲባዋ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ መልኩ እነዚህ ነዋሪዎች ዛሬም ‘የታሰሩ ሰዎች ከእስር ይለቀቁ’ በማለት አደባባይ እንደወጡ እና ከጸጥታ አካላት ጋር እንደተጋጩ እንዲሁም በተከፈተው ተኩስ ሁለት ሰዎች መጎዳታቸውን አስረድተዋል።እስካሁን የብሔር ግጭት ለመቀስቀስ የሞከሩ 9 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የተናገሩት ከንቲባዋ፤ ዛሬ ተከስቶ የነበረው ሁከት በቁጥጥር ሥር ውሎ በከተማዋ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ጨምረው ተናግረዋል።

                        አዳማ

አዳማ ከሰሞኑ ሁኔታ በተሻለ መልኩ አንጻራዊ ሰላም እንደሚታይባት ተሰምቷል። የአዳማ ከተማ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሓላፊ ወ/ሮ ራውዳ ሁሴን በከተማዋ ዛሬ ጠዋት የታውሞ ሰልፍ ለማካሄድ በማህበራዊ ሚዲያዎች የተለያዩ ጥሪዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ይህን ለማስቆም ጥረት ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

በነዋሪዎች ዘንድ ከሚስተዋለው የደህንነት ስጋት ውጪ ከተማዋ ከሞላ ጎደል ወደ ቀድሞ የንግድ እንቅስቃሴ እየተመለሰች መሆኑን ነዋሪዎችም አስመስክረዋል።

                         ሰበታ

ሰበታ ከተማ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴዋ እየተመለሰች መሆኑን የከተማው ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሓላፊ አቶ ታዬ ዋቅኬኔ ተናግረዋል::

የንግድ ተቋሞቻቸውን ዘግተው ከነበሩት እና ከአጠቃላይ ነዋሪው ጋር ውይይት ማድረጉ እንደቀጠለ ተናግረው፤ መልካም የሚባል ለውጦች እየተመለከቱ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል።

                    ባሌ እና ጎባ ከተሞች

በማሕበራዊ ሚዲያዎች ዛሬ ጠዋት በባሌ ዞን በሚገኙ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች እንዲደረግ ሲጠሩ ነበር። ይሁን እንጂ በከተሞቹ ምንም አይነት የተቃውሞ ሰልፎች አለመካሄዳቸውን ከነዋሪዎች ተረጋግጧል።

በተመሳሳይ መልኩ በነዋሪዎች ዘንድ ካለው የደህንነት ስጋት ውጪ በከተሞቹ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ነዋሪዎች አስረድተዋል።

ዶ/ር ዐቢይና ለማ መገርሳ ከአባ ገዳዎችና ከኦሮሞ ማኅበረሰብ ጋር ተወያዮ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ እና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዲሁም ከአባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር በሰሞነኛው የኦሮሚያ ከተሞች ግጭት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል::

”  እኛ የኦሮም ህዝብ ጥያቄ እና የፌዴራል ስርዓትን ወደኋላ ለመመለስ አንሰራም፤ ከእኛ የሚነሳ ሀሳብ የማይስማማው ካለ ሌላ አማራጭ ሀሳብ ማቅረብ ነው ያለበት” በማለት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “እርስ በእርስ በመገዳደል እና በመጎዳዳት መሻገር አይቻልም ፤ መንግስት የፌደራል ስርዓትን ወደኋላ የሚመልስ ምንም አይነት ሥራ እየሠራ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል” ሲሉ አብራርተዋል። የሀገር ሽማግሌዎች እና እና አባ ገዳዎች ያኮረፉ አካላትን እንዲያናግሩ እንዲሁም መንግስት ከህዝቡ ሀሳብ እና ፍላጎት ውጭ ከወጣ ያኔ ውሳኔ ሊያሳልፉ እንደሚገባም መክረዋል።

“ይህንን መንግስት በሁለት ቀን እንበትናለን የሚሉ አካላት እንደዚህ አይነት አቅም ካለቸው፤ ለምን ባለፉት ዓመታት ህዝብ ሲሰቃይ ሀገር ጥለው ሸሹ? ለምንስ እነሱ ሄደው የኦሮሞ ህዝብ ሲቸገር ከረመ? ወይስ ኦሮሞ ሀገር መምራት ሲጀምር ነው ነገር የቀለለላቸው?” በማለት የእነ ጃዋር መሐመድን ሰሞነኛ እቅስቃሴ ያጣጣሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ አይነት ነገር አይጠቅምም፤ አንዱ አንዱን መናቅ ትክክል አይደለም ሲሉም መክረዋል::

በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሁለቴ የተሳሳቱትና ብዙኃኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያስከፉት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር እንዲረጋጋ ያደረጉትን አካላት ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል::

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ   ትናንት እዚህ ልንደርስ የቻልነው በመደማመጥ፣ በመደጋገፍና በአንድነት በመቆም ነው ካሉ በኋላ “እዚህ ቦታ የተደረሰው ከፍተኛ መሰዋዕትነት በመክፈል ነው ፤ እዚህ የደረሰውን ትግል ማሻገር የሁሉም ተሳትፎ ይጠይቃል፤ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ወደኋላ አይመለስም፤ ለዚህም ስጋት አይግባችሁ” ሲሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል::

የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የአስፈጻሚዎች ስልጠና መጀመሩ ታወቀ

ክልል የመሆን ጥያቄን ተንተርሶ ባለፈው ዓመት መገባደጃ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ከፍተኛ ዕልቂት ያስከተለው ጉዳይን ወደ ትክክለኛው መስመር የተባለው ሕዝበ ውሳኔ አስመልክቶ የአስፈጻሚዎች ሥልጠና መጀመሩ ተነገረ::

እስከ ሃሙስ ድረስ በሚቆየው ስልጠና ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአስፈጻሚ ሰልጣኞች  ሊሳተፉ ይችላሉ የሚል ግምት መኖሩን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል:: የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርድ አባል ወይዘሪት ብዙወርቅ ከተተ፥ ስልጠናው በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየተካሄደ መሆኑን ለሚዲያዎች በገለጹበት ወቅት ለመረዳት ችለናል።

ለህዝበ ውሳኔው የሚያስፈልጉ የህግ ማዕቀፎች፣ የመራጮች የምዝገባ ሂደት፣ የህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ፣ ቆጠራ እና ውጤት አገላለጽ፤ እንዲሁም የህዝበ ውሳኔው ውጤት መገለጹን ተከትሎ የሚነሱ ቅሬታዎች የሚፈቱበት መንገድ ላይ ትኩረት ያደረገው ሥልጠና በዛሬው ዕለት ተጀምሯል ።

ሰልጣኞቹ ህዝበ ውሳኔው ተዓማኒ፣ ገለልተኛ እና ከተፅዕኖ የፀዳ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንዲወጡም በዚሁ አጋጣሚ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

ሰልጣኞች በህዝበ ውሳኔው ምዝገባና የምርጫ ሂደት በቂ ግንዛቤ እንዲይዙና ህዝበ ውሳኔዉን በገለልተኝነት ማስፈጸም እንዲችሉ ለማድረግ ያለመ ስልጠና ሲሆን፤ የህዝበ ውሳኔው ድምጽ መስጫ ቀንም ወደ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም መዛወሩን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል::

ሊሸጥ የተቃረበው  የኢትዮጵያ አየር መንገድወደ ቤንጋሉሩ ቀጥታ በረራ ጀመረ

ለውጭ ሀገር ባለሃብቶች ወይም ሃገራት በሽያጭ ሊዘዋወር እንደሚችል በአደባባይ የተነገረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቤንጋሉሩ ከተማ የቀጥታ በረራ መጀመሩን አስታውቋል።

ትርፋማነቱ የማያጠራጥረውና የሀገሪቱ ኩራትና አርማ በለውጡ ቡድን አማካይነት ለሽያጭ መቅረቡ ከፍተኛ ተቃውሞን በተለያየ አቅጣጫ እያስተናገደ ቢገኝም በበላይ አካላት ዘንድ አሁንም  ተቋሙን የመሸጥ ሀሳብ እንዳልተቀየረ ነው የሰማነው::

በዚህ  ሂደት ውስጥ እያለፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዛሬው ዕለት የቴክኖሎጂ ማዕከል ወደ ሆነችው የደቡቧ ህንድ ቤንጋሉሩ ከተማ ቀጥታ በረራ ጀምሯል:: ወደ ሰፍራው የቀጥታ በረራ አገልግሎት መጀመሩን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም ናቸው ያበሰሩት።

በዚህም መሠረት ቤንጋሉሩ አየር መንገዱ ወደ ህንድ በሚያደርገው በረራ ከዴልሒ እና ሙምባይ ቀጥላ ሦስተኛ የህንድ መዳረሻ ከተማ መሆን ችላለች::

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቤንጋሉሩ በሳምንት ለአራት ቀናት የሚጓዝሲሆን፤ በሂደት ወደ ከተማዋ የሚደረገውን በረራ በየቀኑ የሚከናወን ሳምንታዊ ጉዞ ለማድረግ ዕቅድ መያዙንም ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

አማራ ክልል የገባው የአንበጣ መንጋ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አላደረሰም ተባለ

ሰሞኑን በአማራ ክልል የተለያዮ ወረዳዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንዳላደረሰ የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ። የአማራ ክልል የግብረና ቢሮ ምክትል ሓላፊ ሰለሞን አሰፋ (ዶ/ር) ለቢቢሲ እንደገለጹት መንጋው የተከሰተው ክልሉን ከአፋር ጋር በሚያዋስኑ ወረዳዎች ብቻ ነው።

“በሰሜን ወሎ፤ በራያ ቆቦ እና ሃብሩ ወረዳዎች፤ በደቡብ ወሎ ደግሞ ወረባቦና አርጎባ እንዲሁም በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ደዌ ሃረዋ፣ ባቲ እና አርጡማ ፉርሲ” የአምበጣ መንጋው መከሰቱን ያመላከቱት ሓላፊ ፣ የአንበጣ መንጋው ወደ አማራ ክልል ከመዛመቱ በፊት በአፋር እና ሶማሌ ክልል የመከላከል ሥራዎች ቢሠሩም ከጥቅምት ወር ጀምሮ ወደ አማራ ክልል ሊገባ መቻሉን እና አንበጣው ጉዳት እንዳያደርስ የተለያዩ የመከላከያ ዘዴዎች ተግባራዊ መደረጉንም አብራርተዋል።

“ያደገው አንበጣ ሰብል የማይበላ ቢሆንም ለእርባታ ምቹ ሁኔታን ካገኘ እንቁላሉ ሙሉ የዕድገት ሂደቱን እስኪያጠናቅቅ አውዳሚ ስለሆነ ለበልግና መስኖ ሥራ አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጥራል:: ስለዚህም የመከላከል ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ሰለሞን። በመኪና፣ በሰው በአውሮፕላንን እንዲሁም በባህላዊ መንገድ እየተከላከልን ነው ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል::

በአውሮፕላን የታገዘው የመድኃኒት ርጭት በትላንትናው ዕለት ደዌ ሃረዋ አካባቢ መሠራቱም ታውቋል። እስካሁን የአንበጣ መንጋው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አላደረሰም ያሉት ሓላፊ ክልሎች እና ግብርና ሚኒስቴርን በማቀናጀት የህይወት ሂደቱን ካለቋረጥን በበልግ እና በመስኖ ሥራችን ላይ ችግር ስለሚፈጥር መረባረብ አለብን ሲሉም ተደምጠዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ ክልል በትግራይ ደቡባዊ እና ምዕራባዊ ዞኖች ተመሳሳይ የአንበጣ መንጋ ተከስቷል።

የአከባቢው ነዋሪዎች በባህላዊ መንገድ የአምበጣ መንጋውን ለማበረር ቢሞክሩም እየተደረገ ያለው ጥረት ግን እጅግ አድካሚ እና የተፈለገውን ውጤት ሊያስገኝ አልቻለም። የአንበጣ መንጋው ባለፈው ዓመት ሰኔ መጀመሪያ ላይ ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ኢትዮጵያ ነገ በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል።

LEAVE A REPLY