ወይ ለኦሮሚያም አልሆነ….!? || ደረጀ ደስታ

ወይ ለኦሮሚያም አልሆነ….!? || ደረጀ ደስታ

ይሄ ነገር እኮ ወይ ለኢትዮጵያ አልሆነ ወይ ለተዘመረላት ኦሮሚያም አልሆነ። ትግራይም እየተቀየመ አማራውም እየታመመ ደቡብና ሌላውም እያጉረመረመ ኤርትራም እየተገረመ ከሆነ ተጠቃሚው ማነው? ዝምብሎ ተነስ ተነስ ቢሉት ምን ይመጣል? መነሳቱንማ ተነስቷል። ያውም እሚያስፈራ አነሳስ። አገር አልተቀመጠም።

አገር ተነስቶ አይኑን አጉረጥርጦ ደረቱን ገልብጦ ቆሟል። እናስ ወዴት ልሂድ እያለ ነው። እናማ ምን ንግግርና ክርክር ምን አቅጣጫ ያስፈልገዋል? ወዲያ እሚገለበጠውን መገለባበጥ ነዋ እየተባለ ነው – እሱ ነገር መስሎኝ እየሆነ ያለው። ያው እንግዲህ ሰው እየተፈናከተና እየሞተ ነው። ያውም እኔ ያልኩት ካልሆነ ገና ምን አይታቻሁ እየተባለ። – ወይ ውረድ ወይ ፍረድ ይላል የጨነቀው። “አልወርድም አልፈርድም” ያለ እንደሆነስ ሲባል ? ያው ተመልሶ ያልተነሳውን ደግሞ ተነስ ታጠቅ ዝመት ማለት ነዋ ይባላል።

ለነገሩ አሁንም እኮ በሌላው ወገን እየሆነ እየተባለ ያለው ይኸው ነው….ግራ የገባው ነገር። መንገዱ የገባው እንኳ ቢኖር አቅም የለው – አቅም ያለው መንገዱ አልገባው! ለነገሩ አቅም ማለት መፍትሔው ፍንትው ብሎ ሲታይ ማለት ነው። መፍትሔ ካለ አቅም አለ። መፍትሔ ማለት ቢያንስ አብዛኛውን ወገን የሚያስማማ አቅም መፍጠር ማለት ነው። የሌላው እንኳ ቢቆይ የራሴ ወገን ነው ካሉት ጋር የሚያደማምጥ የሚያደራጅ ለአስተማማኝ ለውጥ የሚያዘጋጅ ማለት ነው። ወገንህ ሲሞት ብቻ ሳይሆን ወገንህ ሲገድልም፣ በቀል በበቀል ሲበቅልም ፣ አደጋው ካልታየህ የመጪው እልቂት ምልክት አልታየህም ማለት ይመስለኛል።

ሚሊዮን ተከታዮች አሉኝ ለሚል ሞገደኛ አስር ሚሊዮኖችን ሊነሱበት ይችላሉ። ነገሩ የቁጥሩ ማነስ መብዛት አይመስለኝም አንዲትም ምላጭ አገር ትላጫለች ጊዜም የሰጣት ቅል ድንጋይ ትስብራለች! ጠቅላይ ሚ/ር ሆይ! አጓጉል ለሆኑት ለድርጅትዎ አባላትና የጉሮሮር አጥንት ለሆነብዎት ሰው ተከታዮችና ደጋፊዎችም የዚህን ነገር ኪሳራ አበክረው ያስረዷቸው። የስሙኒ ዶሮ የሁለት ብር ገመድ ይዛ ጠፋች እንዳይሆን።

LEAVE A REPLY