ዛሬ ጠዋት “አዴፓ የሚባለው ድርጅት በህይዎት አለ ወይ?” ብየ ጠይቄ ነበር። ከተሲዓት የአዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሃንስ “አዎ አለን” ብለው የሚከተለውን መልስ በአማራ ቲቢ በኩል ሰጠዋል።
‹‹የተሸከምነው የትዕግስታችን ቀንበር ከብዶናል፡፡ ይሄ መታወቅ አለበት፡፡ እኛ ተላላኪውንና እንጨት ይዞ የሚዞረውን አይደለም የምንፈልገው፡፡ ላኪውን ነው የምንፈልገው!››
እኔም የሚከተለውን የመልስ መልስ ልኬላቸዋለሁ። የአዴፓ ወዳጅ ጓደኞቸ ለአቶ ዮሃንስና ለአዴፓዎች አድርሱልኝ።
አዴፓዎች ሆይ መኖራችሁ መልካም ነው። ይሁን እንጅ ካልሰሩበት መኖር ብቻውን ትርጉም የለውሞ። ከላይ አቶ ዮሃንስ የትዕግስታችን ቀንበር ከብዶናል ብለዋል። እኔ ግን የሚመስለኝ የከበዳችሁ የትዕግስታችሁ ቀንበር አይመስለኝም።
ሲጀመር ትዕግስት ቀንበርም ሸክምም ሊሆን አይችልም። ትዕግስት ከባድ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም አንድ ነገር “ትዕግስት” ነው የሚባለው ምክንያታዊ; ሚዛናዊ እና በልኩ ሲሆን ነው። ትዕግስት ሚዛናዊ እስከሆነ ድረስ ደግሞ ከባድም ቀንበርም አይሆንም። ትዕግስት ከልክ ካለፈ ግን ትዕግስት ሳይሆን ፍርሃት ነው። ትዕግስት ከሚዛን ሲያልፍ ግልጽ የሆነ ፍርሃት ነው። እናማ አያ ዮሃንስ የከበዳችሁ ትዕግስት ሳይሆን አንድም ፍርሃት ነው። አንድም የመሪነት አቅም ማጣት ነው።
አያ ዮሃንስ ይመኑኝ አሁን ያላችሁበት ሁኔታ አንድም ፍርሃት ነው። ወይም ደግሞ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ግራ የመጋባት ሁኔታና የመምራትም አቅም ማጣት ውስጥ ነው ያላችሁት። አሁን ያላችሁበት ሁኔታ በምንም መለኪያ ትዕግስት አይባልም። ወገን እያለቀ; አገር እየጠፋ የምን ትዕግስት ነው?
የሚከተሉትን ሁለት ነጥቦች ለአቶ ዮሃንስ እና ለድርጅታቸው ማስገንዘብ እፈልጋለሁ።
1. በፌደራል ደረጃ ዶ/ር አብይ የጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣናቸውን መጠቀም አቅቷቸዋል። ምክንያቱም እናት ድርጅታቸው አምጾባቸዋል። ኦህዴድ/ኦዴፓ ውስጥ ከዶ/ር አብይ ጋር ከቆመው አመራርና አባል ይልቅ ከእሳቸው በተቃራኒ የቆመው ይበልጣል። ኦዴፓ ዶ/ር አብይን ወደ ጎን ብሎ የጃዋርንና ኦነግን አላማ ነው እያስፈጸመ ያለው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርጅታቸው ካልታዘዛቸው ደግሞ እጃቸው ሽባ ሆነ ማለት ነው። የሰሞኑን እንቅስቃሴ በምሳሌነት እንውሰድ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማው ፊት በአሸባሪው ጃዋር ላይ የሕግ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ አስጠነቀቁ። በምትኩ ጃዋር መሃመድ ማን እውነተኛ ስልጣን እንዳለው ፎከረና በተግባር አሳያቸው። ጃዋርና ቡድኑ ወደ መቶ የሚቆጠሩ ንጽሃንን አስጨፈጨፉ። ቤተ ክርስትያናትን እና የንግድ ቤቶችን አቃጠሉ።
ፓርላማዉ ፊት ማስጠንቀቂያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስቴር በማስጠንቀቂያቸው መሰረት ጃዋርንና ቡድኑን ለፍርድ ያቀርባሉ ተብሎ ሲጠበቅ እሳቸውን ግን በሚያሳፍር ሁኔታ ከጃዋር እግር ስር ተንበርክከው መለማመጥ ነው የያዙት።
ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የጃዋርን የጥፋት እርምጃ ተከትሎ ጊዜ ሳያጠፉ የኦሮሞ ሽሜግሌዎችንና አባገዳዎችን ናዝሬት/ አዳማ ላይ ሰብስበው ከጃዋር ጋር ስምምነት እንዲያወርዱላቸው ልመና ነው የያዙት። ወንጀለኛውን ለፍርድ ማቅረቡ ቀርቶ ጃዋርን ያስቀየመውን ሰው ለፍርድ እናቀርባለን ብለው እየማሉ ነው ለጃዋር ሽምግልና የላኩበት።
ይኸ ማለት ኦህዴድ/ ኦዴፓን እየመራ ያለው አብይ ሳይሆን ጃዋር ነው። ዶ/ር አብይ ኦህዴድን ወክለው የኢህአዴግ ሊቀመንበር ቢሆኑም ኦህዴድን በተግባር ባለማያዛቸው የጠቅላይ ሚኒስቴርነት መንግስታዊ ስልጣናቸውን ለመጠቀም አቅም አነሳቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስትና ፓርቲ አንድ መሆናቸው የታወቀ ሀቅ ነው። ስለዚህ የመንግስት መሪው ፓርቲውን ማዘዝ ባለመቻሉ እጁ ሽባ ሆነ ማለት ነው።
በእኔ እምነት ይኸንን ክፍተት መሙላት የሚችለው አዴፓ ብቻ ነው። ዝርዝሩን ከታች እመለስበታለሁ።
2:- ኦህዴድ/ ኦዴፓ የኦሮማራ ጥምረትን አፍርሶ በአጋሩ አዴፓ ላይ ግልጽ ክህደት ፈጽሟል። ኦህዴድ በአሁኑ ሰዓት ልቡ ከአዴፓ ይልቅ ወደ ህዎሃት ነው። ኦህዴድና ህዎሃት የአላማና የስትራቴጅ አንድነት አላቸው። አዴፓ ደግሞ ከለውጡ በኋላ ከእነዚህ ድርጅቶች ጋራ የራዕይም ሆነ የስትራቴጅ አንድነት ፈጽሞ የለውም። ምናልባት ኦዴፓ ውስጥ ጠቅላይ ማኒስትሩና ጥቂት አጋሮቻቸው የአዴፓ አላማ ተጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኦዴፓ ውስጥ ተሸናፊ ናቸው። በድርጅቱ ላይ የመሪነት ሚና መጫዎት አልቻሉም።
አዴፓ በሙሉ ቁመናው መንቀሳቀስ ከጀመረ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአቅም ክፍተት መሙላት ይችላል። ይኸንን መድረግ የሚችለው ግን ከተከታይነት ወጥቶ የመሪነት ሚና መጫዎት ከጀመረ ብቻ ነው። አዴፓ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተስፋ አድርጎ እርሳቸውን ከመከተል ወጥቶ የራሱን የፓለቲካ ታክቲክ ሰርቶ ወደፊት ወጥቶ የመሪነት ሚና መጫወት መጀመር አለበት።
አዴፓ የመሪነት ሚና መጫወት ሲጀመር ከጎኑ የሚቆሙት በአክራሪው የጃዋር ሀይል የተጠቁት በሙሉ ናቸው። ይህ ማለት ከህውሃትና በጃዋር ከሚመሩት የኦዴፓ ክፍሎች ውጭ ለዘብተኛው ኦዴፓ; ደኢህዴግና ሁሉም የኢህዓዴግ አጋሮች በሙሉ የዚህ ጥምረት አካል ይሆናሉ።
አክራሪው የኦነግ/ ጃዋር ቡድን እያጠቃ ያለው አማራን ብቻ አይደለም። በእምነት ክርስትያኑን በሙሉ እያጠቁ ነው። በብሄር ካየነው ደግሞ ከአማራው ሌላ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥቂቶች በቀር: ጋሞው:, ጉራጌው: ሶማሌው ወዘተ ወዘተ የዚህ አክራሪ ቡድን የጥቃት ሰለባ ነው። ይህ አክራሪ ቡድን አዲስ አበባን ጠቅልሎ በኦሮሚያ ክልል አድርጎ ኦሮሞ ያልሆነውን ሌላውን ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ ከአዲስ አበባ ማባረር ነው እቅዱ።
የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይም ሆነ የእኩልነትና የፍትህ ጥያቄ የአማራ ብቻ ሳይሆን የአፋሩ; የሶማሌው; የጉራጌው; የወላይታው; የጋምቤላው; የከፋው; የጋሞው; የዶርዜው ወዘተ ወዘተ የጋራ ጉዳይ ነው። የትኛውም ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ ከአዲስ አበባም ሆነ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ሀብት ሲገለል ዝም ብሎ ጥቅሙን አሳልፎ አይሰጥም።
ይኸ ሁሉ ህዝብ ልባም አስተባባሪ ካገኘ ከነጃዋር በተጻጻሪ ቁሞ ለትግል ሲነሳ ጊዜ አይፈጅበትም። ይኸንን ሀይል አስተባብሮ ለመውጣት ደግሞ ከአዴፓ የተሻለ ሀይል የለም።
አዴፓ እንደ ትልቅ ሕዝብ መሪነቱ ይኸንን ሀይል በማስተባበር የመሪነት ሚናውን ሊወጣ ይገባል።
ስለሆነም አዴፓ ኢህዓዴግ ውስጥ የመሪነት ሚና መጫወት መጀመር አለበት። አብዛኛው የደቡብ ኢትዮጵያ ማህበረሰቦች የአክራሪው ኦሮሞ ብሄርተኛ የጥቃት ሰለባ ስለሆኑ ደኢህዴግ ከአዴፓ ጋር የማይሰለፍበት ምክንያት የለም። አዴፓና ደኢህዴግ ይዘውት የተነሱት የለውጥ ራዕይ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በደስታ የሚቀበለው ስለሆነ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች ከጎናቸው ናቸው። አዴፓና ደኢህዴግ አንድ ላይ ሁነው ከኦዴፓ ለዘብተኛው ክፍልን (ምንም እንኳ ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም) እና አጋር ድርጅቶችን ከጎናቸው አሰልፈው ከተነሱ አክራሪው የጃዋር ኦዴፓምና ህዎሃት ሊቋቋሟቸው አይችሉም።
ይኸን ለማድረግ ያለው ብቸኛ ችግር አዴፓ የመሪነት ራዕይ የለውም። አዴፓ አሁንም እየተጫወተ ያለው ሚና የተከታይነት ነው። አዴፓ ተስፋውን ሁሉ በጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ላይ ጥሎ የእሳቸውን ሀሳብ እየተከተለ ነው።
በእኔ ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከአዴፓ ጋር አሁንም በአንድነት እየተጓዙ እንደሆነ እምነቴ ነው። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ኦዴፓን ተቆጣጥረው በአግባቡ እየመሩት ቢሆን ኑሮ የአዴፓ ተከታይነት ችግር ላይኖረው ይችላል። ኦዴፓ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ሲወጣ ግን ጠቅላዩ ድርጅታዊ ስልጣናቸው ዜሮ ይሆናል። በዚህም ምክንያት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩን እጆች ሽባ ያደረጉ ሀይሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ወገኖቻችንን ሲጨፈጨፉ: የእምነት ተቋማቱን ሲያወድሙ ተው የሚላቸው ሀይል የለም። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የሾሟቸው የኦሮሚያ ባለስልጣናት ሳይቀር የሚታዘዙት በጃዋር ነው።
በግልጽ እየታየ ያለው ኦሮሚያ ክልል ከዶ/ር አብይ አቅም በላይ ነው። ዶ/ር አብይም የአቅማቸውን ማነስ ተረድተው ሕግ የማስከበር ሀላፊነታቸውን ትተው በእነ ጃዋር እግር ስር ተነጥፈው እየተለማመጡ ነው።
አዴፓ አሁንም ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይን ሙሴ አድርጎ እሳቸው በሆነ ተዓምር ከዚህ ሁሉ ችግር ያወጡናል ብሎ መከተሉን ከቀጠለ ሁለቱም ተያይዘው ነው የሚወድቁት። እኔን የሚያሳስበኝ የእነሱ መውደቅ ሳይሆን አገሬንም ይዘዋት መውደቃቸው ነው።
አዴፓ ከዚህ ይልቅ የጠቅላይ ሚኒስቴሩን አለመቻል ተረድቶ ክፍተቱን ለመሙላት በፍጥነት ከተንቀሳቀሰ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስቴሩንም ይታደጋቸዋል። የአማራን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብንም ከአደጋ ይታደጋል።
በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ከዚህ ችግር ማውጣት የሚችለው አዴፓ ብቻ ነው። አዴፓ ጠቅላዩን መከተል አቁመህ ጠቅላዩን የመታደግ ስራ ስራ። አሁን ስትራቴጅው መሆን ያለበት ጠቅላዩን መከተል ሳይሆን ከፊት ሁኖ ራሳቸው ጠቅላዩንም እየመሩ ከችግራቸው ማውጣት ነው።
አዴፓዎች ከፊት ሁናችሁ ፓለቲካውን በመምራት ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይን ከህዎሃት እና ጃዋር ሰይፍ ታደጓቸው። ኢትዮጵያንም ታደጓት። ትዕግስት ምናምን የምትሉትን ማላዘን አቁሙ። ትዕግስትንና ፍርሃትን ለዩ። አቅም ካነሳችሁ ደግሞ በግልጽ ውጡና እርዳታ ጠይቁ።
አዴፓ ሆይ ሰው ሁን። “ሰው ማለት ሰው የሚሆን ነው ሰው የጠፋለት”።