የ‹‹ እኛ›› ኢትዮጵያ || በወቅቱ ስዩም

የ‹‹ እኛ›› ኢትዮጵያ || በወቅቱ ስዩም

ካንድ ከ‹‹እኛ›› ጉብል
‹‹ኢትዮጵያዊ ነኝ›› ባይ
ከዚህም ከሌለ
ከዚያም ያጣ መሳይ
ጅዋጅዌ ዜጋ
ዚ Diaspora guy
ተያየን አንድ ቀን
በነጭ ባቡር ላይ፡፡
እንደ’ባት ሀገር ወግ
መርቄ ፈገግታ
አንገቴን ሰብሬ
ስሰጠዉ ሠላምታ…
እንደጆኒ ቶኒ
እንደጂሚ ጌታ
ድፍጥጥ አፍንጫዬን
ጥቁር መልኬን ሳለ…
‹‹ዋትስ አፕ ሜን ›› አለና
በሰዉ አፍ ፎለለ፡፡
ጉዱን ልየዉ ብዬ
‹‹ ጤና ይስጥልኝ›› ስለዉ
የተዉሶ አፉን
ወዲያ ጥግ ጣለዉ፡፡
አላለቀም ገና
ጉዱ መች ለቀቀኝ…
‹‹ኢትዮጵያዊ ነህ እንዴ?
አትመስልም›› አለኝ
እኔስ ምኔ ሞኛ
ምላሽ መች ቸገረኝ፡፡

‹‹ ምንም ልሁን ማንም
የትም ልቁም የት ጋ
መምሰል ምን ሊረባ
ምን ሊያወጣ ዋጋ?
መሆን ያህል ነገር
ተሸክሜ ፀጋ››
አልኩታ በሀሴት
ኩራት ቀላቅዬ
ቢገባዉ ባይገባዉ
የት አባቱ ብዬ፡፡
ዋልኩኝ አደርኩና
ሰኞ በሰልስቱ
የጥያቄዉ ሰበብ
‹‹ ነህ እንዴ?›› ማለቱ
ለምንታ እንዴቱ
ታየኝ ምክንያቱ፡፡
የእሱ ኢትዮጵያ
ቀይ ሰልካኪቱ
እናቱን እህቱን
ሚስቱን መሳይቱ
የኔይቱ ደግሞ
ጉራማይሌይቱ፡፡

LEAVE A REPLY