የልደቱ ወቅታዊ ትንታኔ || ሙሼ ሰሙ

የልደቱ ወቅታዊ ትንታኔ || ሙሼ ሰሙ

የልደቱ ወቅታዊ ትንታኔ ከወጣ ሁለት ቀኑ ነው። የራሴ የተለዩ አቋሞች ቢኖሩኝም፣ ገንቢ ምዘናዎችና አድናቆቶችን ከየቦታወ እያነበብኩ ነው። ያበረታታል። ልደቱ ሰነዱን ለውይይት ስላቀረበው፣ ገንቢ ትችቶችንም በስፋት እንደሚጠብቅ እርግጠኛ ነኝ። የመማማር ዑደታችንም እንዲህ፣ እንዲህ እያለ ይቀጥላል፣ አንዱ ይጀምራል ሌላው ይቀበላል፣ ቀጣዩ ያዳብራል፣ ቀሪው ይተቻል፣ ያበለጽጋል። በሂደቱ ሃገራችን ታድጋለች። ከዚህ የተረፈው ደግሞ በራሱ ሌላ ታሪክ ነው።

በተቃራኒው ደግሞ መለስ ብለን ስናጤን በሚኒሊክ ጊዜ የደነቆረ እንዲሉ፣ የተለመደውን ሙሾ፣ ለቅሶና ዋይታ መሰማታችን የሚጠበቅ ነው። እየሰማንም ነው። እንግዲህ በአንድ ሃገር ወስጥ ተፈጥረን የለ፣ እነሱ እንዳለቀሱና እንዳላዘኑ ልደቱና መሰሎቹ ደግሞ ነባራዊ ሁኔታውን እንደተጋፈጡና እንደተነተኑ ሕይወትና እድሜ ያልፋሉ፣ ምንም ማድረግ አይቻልም።

ፈርዶብን፣ የሃገራችን ፈተና ፈርጀ ብዙና ወፈ ሰማይ ነው። የበሽታው ዓይነትና ብዛትም ልክ የለውም። ካልጠፋ የድሃ ሃገር አጀንዳ፣ በዚህች ቅጽበት እንኳን አለቆቻችን ሊታመሙ ይችላሉ በሚል ስጋት የልደቱን ሃሳብ ለማሳነስ ሲሉ ቀድመው የሚታመሙና ሃሳብን ለመሞገት ሳይሆን ግለሰቡን ለመፈረጅና ለማጥላላት፣ በንቃት ዓዕምሯቸውን አጥበውና አጽድተው የሚጠብቁ ወገኖች አሉ። እነዚህ ወገኖች፣ ዛሬም ልደቱ ለምን ጻፈ ብለው በገሃድ ሲወራጩ ማየት የሚያሳዝን ድራማ ነው።
የልደቱ ሃሳብ እንደወረደ ገዢ ሃሳብ ሊሆን ይችላል። ሃሳቡ ታርሞ ታድሶ አቅጣጫ ሰጭ ሆኖ ሊገነባ ይችላል። እስከነ አካቴውም በሃሳብ ትግል ተሸንፎ ተቀባይነት ሊያጣ ይችላል። ይህም ሆኖ፣ ገና ከጅምሩ መጣብን በሚል ቀቢጸ ተስፋ ተሰንገን፣ ሃሳብን በአሉባልታ ለማሰናከል መትጋት ግን እንደ ሃገር ሁላችንንም ሊያሳሰብ የሚገባ ጉዳይ ነው።
Obsessive Compulsive የሚባል ሰርክ በሌላው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲኖረን በማድረግ፣ የራስን በማስረሳትና ቀላዋጭ በማድረግ ማጥላላትና ምቀኝነት የሚያሰፍንብን ሳይንሳዊ የስነ ልቦና ቀውስ አለ።

ከሞላ ጎደል የልክፍቱ መገለጫዎች በግለሰቦች ላይ፣ በሰው ሃብትና ንብረት ወይም ሃሳብ ላይ ከመጠን ያለፈ ትኩረት በመስጠት የግል ለማድረግ ከመመኘት ካልተሳካ ደግሞ ለማጥቃትና ለማጥላለት ከመቋመጥ የሚመነጭ ነው።

በኛ አገር ዐውድ ውስጥ ሲተነተን ደግሞ፣ የልክፍቱ መነሻ የሚሆነው ወጥመድ ውስጥ ያስገባነውን ግለሰብ መሻሻል ካለመመኘትና ከመበለጥ፣ በተለይ ደግሞ ከነጠላና ተራ ክፋት፣ እንዲሁም ከማይሽር ቅናትና ምቀኝነት የሚመነጭ ነው። ይህ ደግሞ መገለጫችን ሆኗል። ይህንን ልክፍት ላለፉት 20 ዓመታት ያህል አድምጠነዋል ።

ጊዜ ቢፈጅም ልክፍቱ ያሻራቸው በርካቶች አሉ። የዛን ያህል፣ ልዩነታቸውን ጠብቀው በመከባበር በሃሳብ እየሞገቱ የቀጠሉም አሉ። ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላም ከጥላቻና ተራ ምቀኝነት መላቀቅ አቅቷቸው የገፉበት ደግሞ በልዩ ሁኔታ የሚታዮ አሉ። የነዚህ ሃይሎች ችግር ሌላ ሳይሆን ያለ ምንም ጥርጥር የ “Obsessive compulsive Disorder ” ተጠቂ መሆናቸው እንደሆነ እገምታለሁ።

ሃገራችን ፈተና ላይ ነች፣ በቂ ጉልበት የላትም። እንኳን አቅም ያላቸውን አቅም የሌላቸውንም ዜጎቿን ጥሬ ጉልበት ትሻለች። ወገኖች፣ ብትችሉ ለሀገራችን ስትሉ፣ በራሳችሁ ጊዜ ከራሳችሁ ጋር ተማክራችሁ ከበሽታችሁ ተፈወሱ ወይም ንቁ፣ ካልቻላችሁ ደግሞ ልክፍቱ ስር የሰደደ በሽታ ስለሆነ ለናንተም አደጋ ስለሚሆን ሕክምና ተከታተሉ። እድሜ አጭር ነው። መጨረሻችን እንደ ተረቱ ውሾቹ ይጮሃሉ፣ ግመሎቹ ግን ጉዟቸውን ቀጥለዋል እንዳይሆን እሰጋለሁ።

LEAVE A REPLY