በኢትዮጵያ ያሉ ቻይናውያን ኮሮናን በመስጋት ቪዛ እያራዘሙ ነው

በኢትዮጵያ ያሉ ቻይናውያን ኮሮናን በመስጋት ቪዛ እያራዘሙ ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት በርካታ ቁጥር ያላቸው ቻይናዊያን ወደ አገራቸው ላለመመለስ በኢትዮጵያ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ቪዛ እያራዘሙ መሆኑ ተሰማ።

ቻይናዊያኑ ለተለያዩ ሥራዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ቆይተው በአሁኑ ወቅት የተሰጣቸው የመቆያ ቪዛ ስላበቃ ነው ወረርሽኙን በመፍራት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ፈቃድ እየጠየቁ ያሉት።

በቦሌ ዓለም ዐቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ የኢሚግሬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ አይክፋው ጎሳዬ ጥቂት የማይባሉ ቻይናዊያን በኢትዮጵያ ለመቆየት የሚያስችላቸውን የቪዛ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እያገኙ መሆናቸውን ጠቁመው፤ “ቻይናዊያኑ በአገራቸው ያጋጠመውን ወረርሽኝ በመስጋት ነው በኢትዮጵያ ለመቆየት ጥያቄ እያቀረቡ ያሉት” ብለዋል። ይህንን ከግንዛቤ በማስገባትም መንግሥት ጥያቄ እያቀረቡ ላሉ ቻይናዊያንም ሆነ የሌሎች አገራት ዜጎች የመቆያ ጊዜያቸው እንዲራዘም እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሕገ ወጥነትን ለመከላከል ቀደም ሲል ቻይናዊያን የመቆያ ጊዜያቸውን ሲያጠናቅቁ እንዲራዘምላቸው በሚጠይቁ ጊዜ ለ10 ቀናት የሚቆይ ማራዘሚያ ይፈቀድላቸው እንደነበር የጠቀሱት አቶ አይክፋው፤ አሁን ግን በአገራቸው የተከሰተውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት ለአንድ ወር የሚቆይ ቪዛ እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአንዳንድ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ በርካታ ጣሊያናዊያን ቱሪስቶች በኢትዮጵያ መቆየት የሚያስችላቸው ቪዛ ቢያበቃም በአገራቸው ያለውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋትን በመፍራት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየት ጠይቀዋል ለሚለው ወሬ ማረጋጫ አልተገኘም።

ቢቢሲ ይህንኑ ለማጣርት አዲስ አበባ የሚገኘውን የጣሊያን ኤምባሲን የጠየቀ ሲሆን፤ በተሰጠው ምላሽ መሠረት እንዲህ አይነት ጥያቄ አለመቅረቡንና የተባለው ነገር ሐሰተኛ ወሬ መሆኑን አረጋግጧል።

አቶ አይክፋው ጎሳዬም ይህንን መረጃ ሰምተው ለማጣራት መሞከራቸውንና እንደተባለው ከተጠቀሱት ጣሊያናዊያን ቱሪስቶች በኩል ቪዛ የማራዘም ምንም አይነት ጥያቄ ለመሥሪያ ቤታቸው እንዳልቀረበ ገልጸዋል።

LEAVE A REPLY