ስድስተኛ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ የሆነች እንግሊዛዊት በአዲስ አበባ ተገኘች

ስድስተኛ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ የሆነች እንግሊዛዊት በአዲስ አበባ ተገኘች

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ስድስተኛ ሰው መገኘቱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ። የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአዲስ አበባ ውስጥ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከሆስፒታሎች እና ከሆቴሎች ጋር በቅንጅት እየሠራ ቢሆንም በየቀኑ በቫይረሱ የተጠቁ አዳዲስ ሰዎችን ማግኘት የተለመደ ተግባር ሆኗል።

መጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ የመጣች የ 59 ዓመት የብሪታኒያ ዜግነት ያላት ዲፕሎማት ከሆቴል በተደረገ ጥቆማ በምትገኝበት እራሷን አግልላ እንድትቆይ መደረጉን እና ዲፕሎማቷ በዛሬው ዕለት በተደረገላት የላቦራቶሪ ምርመራ በኮሮና ቫይረስ መያዟ መረጋገጡን ዶክተር ሊያ አስታውቋል። ከግለሰቧ ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች የመለየትና የክትትል ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም  ሓላፊዋ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት ግለሰቧ በለይቶ የህክምና መስጫ ማዕከል የቅርብ የሕክምና ክትትል እየተደረገላት እንደሚገኝ ከመግለጫው መረዳት ተችሏል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የኢትዮጰያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠርና በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በፍጥነት ለይቶ እርምጃ ለመውሰድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ዶክተር ሊያ የገለጹ ሲሆን፤ ህብረተሰቡም ይህንን አውቆ በሁኔታዎች ሳይደናገጥ በተረጋጋ መንፈስ የበሽታውን ስርጭት በመግታት የሚቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ ደጋግመው ተማጽነዋል::

LEAVE A REPLY