ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተለይም በበዓሉ ሰሞን በሐሰተኛ የብር ኖቶች እንዳይጭበረበሩ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አሳሰበ።
ኅብረተሰቡ ባዕድ ነገር ተቀላቅሎባቸው ከሚሸጡ ምግብና መጠጦች እንዳይታለል ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ያስጠነቀቀው ኮሚሽኑ፤ የዘመን መለወጫ በዓል ከወንጀል የጸዳና ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ዝግጅት አድርጊያለሁ ብሏል።
ኅብረተሰቡ ከወንጀል ድርጊቶች ራሱን እንዲጠበቅ መልዕክት እያስተላለፈ የሚገኘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፤ በተለይም በበዓላት ወቅት የሚፈጸም ወንጀል ቀድሞ ለመከላከልና መቆጣጠር ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት እንዳደረገም አስታውቋል።
በኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት የሚዲያ ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ ፤ የከተማዋ ነዋሪዎች ግብይት በሚፈጸምበት ወቅት በሐሰተኛ የብር ኖቶች እንዳይጭበርበሩ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁሞ፤
ኅብረተሰቡ በገበያ ቦታዎች ላይ የሀሰተኛ የብር ኖቶች ዝውውር ከተመለከተም ለፖሊስ በፍጥነት መጠቆም ይገባዋል ብሏል።
በመዝናኛ ቦታዎች የሚፈጠሩ ጸቦችን ፣ በየመንገዱ የሚደረጉ ዝርፊያና ቅሚያዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዝግጅት መደረጉን ያስታወሱት ሓላፊው፤ በበዓል ወቅት የሚጨምረውን የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ አደጋ በሚበዛባቸው ቦታዎች የትራፊክ ፖሊሶች መሠማራታቸውንም ገልጸዋል።
የኮቪድ-19ን ወረርሽኝ ለመከላከል በመዝናኛ ቦታዎች፣ በትራንስፖርት አገልግሎትና ሌሎች ሕዝብ በሚበዛባቸው ስፍራዎች ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር እንደሚጠናከርም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ይፋ አድርጓል።