ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በትግራይ እየተካሄደ ያለው ምርጫ ለሃገሪቱ ፌዴራሊዝም ጥንካሬ እንጂ ስጋት እንደማይሆን የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ።
ዛሬ እየተካሄደ ስላለው ምርጫ ለቢቢሲው ኒውስዴይ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ጌታቸው፤ ” ክልሎች ምርጫ ማድረግ ያለባቸው መብታችን ስለሆነ ነው። እኛ በዚህ ላይ አንደራደርም። ዋጋ ከፍለንበታል። ምርጫ እናድርግ ስንል አይቻልም የሚል ምላሽን ከአራት ኪሎ አንቀበልም” ሲሉም ተደምጠዋል።
ምርጫን የማራዘሙ ነገር በሁሉም ክልሎች ታምኖበት በቂ ምክንያት ኖሮ ቢሆን ኖሮ ነገሩን ለማጤን ህወሓት ይገደድ ነበር ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ “ነገር ግን ይህ ውሳኔ በማዕከላዊ መንግሥት የተወሰደ የተናጥል እርምጃ ነው። ውሳኔውም ፍላጎቱን በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ለመጫን የተደረገ ነውና አንቀበለውም” በማለት ፓርቲያቸው አሁንም ለሕግ ተገዢ እንደማይሆን ያሳዮበትን አስተያየት ሰጥተዋል።
“በጤናማ ሁኔታዎች ውስጥ ብንሆን መጠየቅ የነበረበት ጥያቄ ለምን ምርጫ አታካሄዱም? ነበር። ነፃ ገለልተኛና ተዓማኒ ምርጫዎች የትም መሆን ያለባቸው ነገሮች ናቸው” የሚሉት የህወሓት ከፍተኛ አመራር፤ ማዕከላዊው መንግሥት የሥልጣን ዘመኑን በግድ እያራዘመ መሆኑን ነው ሲሉም አብጠልጥለውታል።