ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጲያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የፀረ ኤች. አይ. ቪ. መድኃኒቶችን ከ1 ሺኅ በላይ ለሆኑ የጤና ተቋማት ማከፋፈሉን አስታወቀ።
ኤጀንሲዉ በተገባደደው 2012 በጀት ዓመት ለ1 ሺኅ 364 የጤና ተቋማት የፀረ ኤች. አይ. ቪ. እና ተጓዳኝ በሽታ መድኃኒቶችን ማሰራጨቱን የኤጀንሲው የክምችትና ክትትል ባለሙያ አቶ በረከት ተዘራ ገልጸዋል።
ኤጀሲው ለፀረ HIV እና ተጓዳኝ በሽታ መድኃኒት ግዢ ከ2 ቢሊዮን 72 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ከሓላፊው ገለጻ መረዳት ተችሏል።
ስርጭቱንም አስመልክቶ የፀረ ኤች. አይ. ቪ. ሕክምናውን ለሚሰጡ በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ 1 ሺኅ 364 የጤና ተቋማት በኤጀንሲው ቅርንጫፎች አማካኝነት እንደተከፋፈለ ተገልጿል።
የተከፋፈሉት መድኃኒቶችም 480 ሺኅ 556 ሰዎች ለማከም የሚያስችሉ መሆኑ ታውቋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የፀረ ኤች አይ ቪ መከላከያ የሚጠቀሙ በርካታ ግለሰቦች ባለፉት ወራት ወደ ሆስፒታል እንዳይመጡ መደረጉን ተከትሎ ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ቅሬታ መኖሩን ኢትዮጵያ ነገ ቀደም ሲል መዘገቡ አይዘነጋም።