ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከባለቤቱ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ 4 ግለሰቦችን በመሳሪያ ተኩሶ የገደለው የፖሊስ አባል በቁጥጥር ስር ዋለ።
ትናንት መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡30 በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ጨርጨር ጊርጊሮስ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ አደጋው መድረሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
ረዳት ሳጅን መልህቁ መኪ የተባለው ይህ ተጠርጣሪ የፖሊስ አባል ፤ ከባለቤቱ ጋር በትዳር ለሁለት ዓመት አብረው የኖሩ ቢሆንም በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት፣ ከ15 ቀን በፊት ባለቤቱ ወደ ቤተሰቦቿ ቤት መሄዷን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጄላን አብዲ አስረድተዋል።
ይህንን ከባለቤቱና ከቤተሰቦቿ ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ምክንያት በማድረግ ተጠርጣሪው የፖሊስ አባል ለሥራ የታጠቀውን መሳሪያ ይዞ ወደ ባለቤቱ ቤተሰቦች ቤት በመሄድ የሚስቱን እናት ፣ የእንጀራ አባቷን፣ የእህቷን ባል እና የቤት ሠራተኛዋን በአጠቃላይም 4 ግለሰቦችን ተኩሶ በመምታቱ ህይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ይፋ አድርጓል።
አደጋው ከደረሰ በኋላ ግለሰቡ ወዲያውኑ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን፤ የተለያዩ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ የምርመራ ሂደቱ የተጀመረ መሆኑን እና ምርመራውንም በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ለሚመለከተው የፍትህ አካል ይላካል ተብሏል።