ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ብዙ ውዝግብ እያስነሳ በሚገኘው የኮንዶሚኒየም እደላ አዳዲስ መረጃዎች እየወጡ ነው። በዚህ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ሓላፊ በልማት ምክንያት የእርሻ መሬታቸውን ላጡ አርሶ አደሮች የጋራ መኖሪያ ቤቶች እያስተላልፍኩ ነው ሲልም ገልጿል።
ተፈናቃይ አርሶ አደሮች ከዚህ ቀደም በጉዳዮ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ “የተሰጠን የጋራ መኖሪያ ቤት የለም ” ሲሉ ደጋግመው መናገራቸውን ተከትሎ፣ በጊዜው የከተማው ቤቶች ልማት ሓላፊ ሰናይት ዳምጠው ቤቶቹ እየተላለፉ ናቸው የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር።
የአዲስ አበባ ከተማ የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ኮሚሽንም በዚህ አከራካሪ ጉዳይ ላይ በሰጠው ማብራሪያ የከተማው ካቢኔ ግንቦት 2011 ዓ.ም ላይ የእርሻ መሬታቸውን በልማት ምክንያት ላጡ አርሶ አደሮች ከ23 ሺኅ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤት ተላልፎ እንዲሰጥ ቢወስንም የጋራ መኖሪያ ቤቱ ተላልፎ አልተሰጣቸውም ማለቱም አይዘነጋም።
ኢዜማ በዚህ ዙሪያ ያቀረበውን የጥናት ውጤት ተከትሎ ታከለ ኡማ የጋራ መኖሪያ ቤቱን የሰጠሁት ከቦታቸው ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ናቸው ማለታቸው ደግሞ ነገሩን የበለጠ አወሳስቦታል ነው የተባለው።
ይህን ተከትሎ አሁን ላይ ዳግም በጉዳዮ ላይ ማብራሪያ የሰጠው የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ሓላፊ ሰናይት ዳምጠው ቢሮው ወደ 17 ሺኅ ለሚጠጉ አርሶ አደሮች የጋራ መኖሪያ ቤት ማስተላለፉን ጠቁሞ አሁንም ይህንን ቤቶችን ለአርሶ አደሮቹ እያከፋፈልኩ እገኛለሁ ብሏል።
ኤጀንሲው ከየአቅጣጫው ከትክክለኞቹ አርሶ አደሮች እየመጣ ያለውን ምትክ ቤት እየደረሰን አይደለም የሚለውን ጥቆማ ተከትሎ አሁን እንዲህ ዓይነት መግለጫ መስጠቱ አስገራሚ ቢሆንም ታከለ ኡማ ከሃያ ሺኅ በላይ ቤቶች ሰጠኋቸው የሚሏቸው አርሶ አደሮች የትኞቹ ናቸው? የሚል ጥያቄን ፈጥሯል።