ለዳኞች እረፍት ሲባል የፌደራል ፍርድ ቤቶች በመስከረም ወር በከፊል ይዘጋሉ ተባለ

ለዳኞች እረፍት ሲባል የፌደራል ፍርድ ቤቶች በመስከረም ወር በከፊል ይዘጋሉ ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም በከፊል ዝግ ሆነው ይቆያሉ ተባለ።

ፍርድ ቤቶች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ከመጋቢት 10 – እስከ ሐምሌ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በከፊል ዝግ ሆነው ከቆዩበት ሁኔታ ለመውጣትና ተቋርጦው የነበሩት አገልግሎቶችን ደረጃ በደረጃ ለማስጀመር ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ባወጣው መመሪያ መሰረት ዳኞች በመስከረም ወር እረፍት አንዲያደርጉ በመወሰኑ ምክንያት አገልግሎቱ እንደሚቋረጥ ታውቋል።
ቀደም ሲል በነበረው አሠራር ዳኞች ዓመታዊ እረፍታቸውን በነሃሴ እና በመስከረም ወር የሚወስዱ በመሆኑ ፤ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አስቸኳይነት ያላቸውን ጉዳዮች ብቻ በተረኛ ችሎቶች በማስተናገድ በከፊል ዝግ ይሆኑ እንደነበር  ያስታወሰው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፤ በዚህ ዓመት ዳኞች አጭር የእረፍት ጊዜ እንደሚኖራቸውም አስታውቋል።
የፌደራል ፍርድ ቤቶቹ በከፊል ዝግ ሆነው በሚቆዩባቸው የመስከረም ወር 20 የሥራ ቀናት አስቸኳይና ጊዜ የማይሰጡ፣ ከዜጎች መሰረታዊ መብቶች እንዲሁም ከሃገር ሰላምና ፀጥታ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ጉዳዮች ግን እንደሚታዮ ከወጣው መግለጫ መረዳት ችለናል።
የጊዜ ቀጠሮ፣ የዋስትናና የዕግድ ጥያቄዎች፣ የመያዣና የብርበራ ትዕዛዞች፣ በተፋጠነ ስነ-ስርዓት የሚታዩ የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች፣ እንዲሁም ከቤተሰብና ከሕፃናት ቀለብና አስተዳደግ ጋር የተያያዙ አጣዳፊ መሰረታዊ ጉዳዮች በተረኛ ችሎቶች ይስተናገዳሉ ተብሏል።

LEAVE A REPLY