ምርጫው በመካሄዱ ደስተኛ ነኝ ያለው ሳልሳዊ ወያኔ ህወሓት ከፍተኛ ጫና አድርጎብኛል አለ

ምርጫው በመካሄዱ ደስተኛ ነኝ ያለው ሳልሳዊ ወያኔ ህወሓት ከፍተኛ ጫና አድርጎብኛል አለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የትግራዩ ተቃዋሚ ፓርቲ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ  ዛሬ ሰኞ በሰጠው መግለጫ፣ በምርጫው ሂደት በተወዳዳሪዎቹና በታዛቢዎቹ ላይ ማስፈራሪያ እና ጫና ይደርስብን ነበር ሲል ገለፀ።

ተገቢ ያልሆኑ ነገሮች ከምርጫው ቀን በፊት አንስቶ ይስተዋሉ ነበር ያለው በህወሓት ተለጣፊነት የሚታማው ሳልሳዊ ወያኔ፤  የገዢው ፓርቲ አባላት ከምርጫው በፊት ቤት ለቤት እየዞሩ የህወሓት የምርጫ አርማ ላይ ምልክት እንዲያደርጉ  በመራጮች ላይ ጫና ሲያሳድሩ ነበር ሲል የነበረውን አካሄድ ተችቷል።
“የወረዳና የቀበሌ መዋቅሮችን በመጠቀም፣ በእጩ ተመራጮቻችን እና ቤተሰቦቻቸው ላይ ማስፈራርያ ይደርስ ነበር፤ በሕዝብ እንደ ጠላት እንዲታዩና እንዲሸማቀቁም ሲደረግ ነበር” የሚለው ሳልሳዊ ወያኔ ፤ ከዚህ በተጨማሪም ህወሓት በሚድያና በሰነድ የተደገፈ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ አካሂዶብናል ብሏል።
ድምጽ በሚቆጠርበት ወቅት፣ ታዛቢዎቹን ከምርጫ ጣብያው ለማራቅ የተደረጉ ጫናዎች ነበሩ ያለው በክልላዊ ምርጫው የተሳተፈው ሳልሳዊ ወያኔ፤ ምርጫው በመካሄዱም ደስተኛ መሆኑን ጠቁሞ፤ የትግራይ ሕዝብ በመስዋዕትነቱና በድሉ ያረጋገጠውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰንን መብት ለድርድር እንደማያቀርብ ለዓለም ያስመሰከረበት በመሆኑ ኩራት ይሰማኛል ሲል ገልጿል።
በአቋም ረገድ የህወሓትን ራዕይና ፍላጎት ያንፀባረቀው ሳልሳዊ ወያነ፤ ይሁን እንጂ ከምርጫው በፊትና በምርጫው ወቅት ነበሩ ያላቸውን እጥረቶችና እንቅፋቶችን በተቃዋሚ ስም ለመጥቀስ ሞክሯል።
በትግራይ ክልላዊ ምርጫ ህወሓትን ጨምሮ አምስት ፓርቲዎች በምርጫው ላይ መሳተፋቸው ይታወሳል።
የፌደራሉ መንግሥት ሕገወጥና ተቀባይነት የለውም ባለው፤ በትግራይ ክልል ጳጉሜ አራት በተካሄደው በዚህ ክልላዊ ምርጫ ህወሓት በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፉ ይታወቃል።

LEAVE A REPLY