ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የብር ኖቶች መቀየር በኢትዮጵያ የተጀመረው የኢኮኖሚ ሪፎርም አካል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።
በኢትዮጵያ በሥራ ላይ ያሉት የብር ኖቶች የተቀየሩ ሲሆን፤ ካሉት የብር ኖቶች በተጨማሪ የ200 ብር ኖት በስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል። በቀለም ደረጃም 200 ብር ሃምራዊ፤ 100 ብር ውሃ ሰማያዊ፤ 50 ብር ቀይ ብርቱካናማ፤ 10 ብር ደግሞ አረንጓዴ ቀለም እንዲይዙ ተደርጓል።
አሁን ያለው የ5 ብር ኖት በሥራ ላይ እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን፤ ይህ የብር ኖት ቀስ በቀስ በሳንቲም እንደሚቀየር ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ተፈጥሮ የነበረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት ችግር ለመፍታት ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ሥራች ሢሠሩ ቆይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህም አሁን ላይ ኢኮኖሚው ከነበረበት የቁልቁለት ጉዞ ተላቆ በማንሰራራት ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ ይሁን እንጂ የዋጋ ንረትን የመቆጣጠሩ ሥራ በሚፈለገው ልክ ማከናወን አልተቻለም ብለዋል።
ከባንክ ውጭ የሚንቀሳቀስ ከፍተኛ ገንዘብ መኖሩ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ እንዳባበሰው የጠቀሱት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ የብር ኖት መቀየር አይነተኛ መፍትኄ መሆኑንም ተናግረዋል።
የገንዘብ ኖቶቹ ለአጠቃቀም ምቹና ረዥም ጊዜያትን እንዲያገለግሉ ተደርገው መሠራታቸውንም ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኖቶቹን በመቀየሩ ሥራ ለህትመት ብቻ በአጠቃላይ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገም ይፋ አድርገዋል።
ከዚህ ቀደም የወጣውና ከ1ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በቤት ውስጥ አስቀምጦ መገኘትን የሚከለክለው ህግም አሁንም ይተገበራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤
ከተጠቀሰው ብር በላይ ገንዘብ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ስር እንደሚውል ጠቁመው፤ በቁጥጥር ስር የዋለው ገንዘብም የጸጥታ ተቋማትን ለማጠናከር እንደሚውል አረጋግጠዋል።
ገንዘቡን በመቀየር ረገድ በህገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ባንኮችና ማናቸውም አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድም ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሰጡት ዶክተር ዐቢይ፤ በተለይም ባንኮች የብር ኖቶቹን በመቀየር ረገድ በህገ-ወጥ ሥራ ላይ ተሰማርተው ከተገኙ ጠንካራ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
በተያያዘ ዜና የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ውጭ በጎረቤት ሀገራት ጭምር ከፍተኛ የኢትዮጵያ ብር ተከማችቶ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህ ብር ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የገለጹት የባንክ ገዢው የብር ኖቶችን በሦስት ወር ውስጥ መለወጥ እንደሚቻልም ገልጸዋል።