ባሳለፍነው ዓመት 31 ተቋማት የሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንደነበሩ የደህንነት ቢሮ አስታወቀ

ባሳለፍነው ዓመት 31 ተቋማት የሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንደነበሩ የደህንነት ቢሮ አስታወቀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በ2012 በጀት ዓመት ባደረገው የሳይበር ደህንነት ኦዲት 31 የሚሆኑ ተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት መለየቱን እና እንዲታረሙ ማድረጉን ገለጸ።

በተቋሙ የሳይበር ደህንነት ኦዲት እና ኢቫልዌሽን ዲቪዥን ሀላፊ አቶ ደሳለኝ ወ/ጊዮርጊስ ፤ በተጠናቀቀዉ የ2012 በጀት ዓመት ኤጀንሲው በ31 የመንግሥት እና የግል ተቋማት ላይ ጥልቅ የደህንነት ፍተሻዎችን ማድረጉን ተከትሎ፣ ተቋማቱ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸው እንደተደረሰበት ተናግረዋል።
የደህንነት ኦዲት የተደረገላቸው ሁሉም ተቋማት ክፍተት እንደተገኘባቸዉ እና ክፍተት ያለበት ሲስተም ወይም የሳይበር መሰረተ-ልማት፣ የሰው ኃይል እና የሳይበር ደህንነት አስተዳደር ሂደት እንደነበረም ከሓላፊው ገለጻ መረዳት ተችሏል።
በተቋማቱ ላይ በስፋት ከተገኙት የሳይበር ደህንነት ክፍተቶች መካከል በሲስተሞች እና የሳይበር መሰረተ-ልማት ግንባታ ላይ የሚፈጠሩ ቴክኒካዊ ክፍተቶች፣ ተቋማት የራሳቸው የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ አለመኖር ፣ እንዲሁም ፖሊሲዉ ያላቸዉም በተገቢው መንገድ ተግባራዊ አለማድረግ እንደሆኑም በዝርዝር ተገልጿል።
የተቋማቱ የበላይ አመራሮች ለሳይበር ደህንነት የሚሰጡት ዝቅተኛ ግምትም ዋንኛ ምክንያቶች መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ደሳለኝ ፤ ከተለዩት የሳይበር የደህንነት ክፍተቶች መካከል 56 በመቶ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ ሲሆን፣ 35 በመቶ የሚሆኑት በመካከለኛ ደረጃ እንዲሁም 9 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳታቸው ዝቅተኛ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነቶቹን ለመቅረፍ ተቋማቱ የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች መውሰድ ይገባቸዋል የተባለ ሲሆን፤
ከእነዚህ የጥንቃቄ መንገዶች መካከልም በኤጀንሲዉ የተሰጣቸዉን ምክረ ሀሳብ መሰረት በማድረግ ክፍተቶቹን ማስተካከል፣ ማንኛውም ሲስተም ወይም የሳይበር መሰረተ-ልማት ከመተግበሩ በፊት የደህንነት ፍተሻ እንዲደረግለት ማድረግ በዋናነት መተግበር ያለባቸው ከመሆኑ ባሻገር፤ ከኤጀንሲው ጋር ተቀራርቦ መሥራት እና አስፈላጊውን እገዛ መጠየቅም ይገባል ተብሏል።

LEAVE A REPLY