ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የግንባሩ የረጅም ጊዜ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዳውድ ኢብሳን ከፓርቲው ኃላፊነት ማገዱን የገለጸበትን ደብዳቤ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁን ቦርዱ አረጋገጠ።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቃል አቀባይ ሶሊያና ሽመልስ፤ የግንባሩ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለቦርዱ በላከው ደብዳቤ ላይ ባካሄደው ስብሰባ መሰረት “አቶ ዳውድ ኢብሳ የሥነ ምግባር ጥሰት ፈፅመዋል” ብሎ ከግንባሩ አመራርነት መታገዳቸውን እንደተረዱ ገልጸዋል።
ጉዳዩን በተመለከተም የፓርቲው የሥነ ሥርዓትና ቁጥጥር ኮሚቴ ደብዳቤውን እንደላከ የገለጹት ቃል አቀባይዋ፤ ለምርጫ ቦርድ የደረሰው ደብዳቤ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር ምክትል ሊቀመንበር አቶ አራርሶ ቢቂላ የተፈረመ መሆኑንም ገልጸዋል።
በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው እገዳ ሲያደርግ ለሥነ ሥርዓትና ቁጥጥር ኮሚቴ እንደሚልክ ያስታወሱት ሶልያና፤ በደብዳቤው ላይ ለኮሚቴውን ማሳወቃቸውን ከመግለጹ ውጪ ከቦርዱ የጠየቁት ምንም ዓይነት ውሳኔ አለመኖሩንም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ከኦነግ ሊቀመንበርነት ታግደዋል ከተባሉት ከአቶ ዳውድ ኢብሳ በኩልም ሌላ ደብዳቤ እንደደረሳቸው የገለጹት የምርጫ ቦርድ ቃል አቀባይ፤ ነገር ግን ደብዳቤው ከዚህ በፊት በነበረው የሥነ ሥርዓትና ቁጥጥር ኮሚቴ የተጻፈ ከመሆኑ ባሻገር፤ ቀደም ሲል የተካሄዱ የፓርቲውን ስብሰባዎች የተመለከተ እንጂ ከእገዳው ጋር የተያያዘ አለመሆኑንም አብራርተዋል።
ይህን ተከትሎ ቦርዱ ከሁለቱም ወገኖች የሚመጡ ደብዳቤዎችን፣ መተዳዳሪያ ደንባቸውን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች መተዳዳሪያ አዋጅን መሰረት አድርጎ እንደሚመረምርና ውሳኔ እንደሚሰጥ ተሰምቷል።