ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በመቀለ ከተማ፣ በአይደር ክፍለ ከተማ “አዲሓ” ተብሎ በሚታወቀው ሰፈር አንዲት ሴትና ሁለት ወንድ ጓደኛሞች በአንድ ቤት ውስጥ ሞተው መገኘታቸው ታወቀ።
ወጣቶቹ ሞተው የተገኙት በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ መሆኑን የገለጸው በከተማዋ የሚገኘው የአይደር ክፍለ ከተማ ፖሊስ ፤ ህይወታቸው አልፎ የተገኙት ሦስቱ ወጣቶች ርዕሶም ገብረእግዚአብሔር፣ ግርማይ ኃብተሚካኤል እና መርሃዊት ሐድጉ የተባሉ እድሜያቸው በ20ዎቹ ውስጥ የሚገኝ መሆኑን አስታውቋል።
ሦስቱም ወጣቶች ባለፈው ቅዳሜ መስከረም ሁለት ቀን በጋራ ሲጫወቱ አምሽተው ወደ ቤታቸው እንደገቡ የተገለጸ ሲሆን፤ በማግስቱ እሁድ ከሰዐት ግን በአንደኛው ሟች ቤት ውስጥ ሞተው መገኘታቸው ነው የተነገረው።
በአይደር ክፍለ ከተማ የወንጀል ምርመራ ክፍል ባልደረባ የሆኑት ምክትል ኢንስፔክተር ገብረማርያም የማነ፤ የወጣቶቹ ሞት መንስዔ ለማወቅ ፖሊስ መርመራ እያካሄደ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እስካሁን ባገኘው መረጃ ፖሊስ ለወጣቶቹ ሞት መንስዔ ተብሎ የሚጠረጠር ፍንጭ የተገኘ ቢሆንም፤ በአይደር ሆስፒታል የአስከሬን ምርመራ ተደርጎ ውጤት እስኪመጣለት ድረስ እየተጠበቀ ነው ብለዋል።
የሟች ርዕሶም ገብረእግዚአብሔር ወንድም የሆነው ገብረ መድኅን ገብረእግዚአብሔር፤ ወጣቶቹ ተኝተውበት በነበረው ክፍል ውስጥ የነበረው ጀነሬተር ለሞታቸው መንስኤ ሊሆን ይችላል ሲል ግምቱን ከወዲሁ አስቀምጧል።
ቅዳሜ ዕለት ወጣቶቹ በሚኖሩበት አካባቢ መብራት ጠፍቶ ስለነበር ጀነሬተሩ አገልግሎት ሲሰጥ ነበረ ያለው የሟች ወንድም፤ ሆኖም ማታ ግን ተለኩሶ ስለመቆየቱ መረጃ እንደሌለው ገልጿል።