ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከዚህ ቀደም የተካሄዱትን ውይይቶች በጋራ ለመገምገም የተምከረበት ውይይት ዛሬ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር አደረጉ።
በውይይቱ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ቀደም ሲል የተካሄዱት መድረኮች ውጤታማ እንደነበሩ በመግለጽ፣ ብሔራዊ ምክክር እና ውይይት እንዲካሄድ መንገድ ጠራጊ እንደሆኑ ገልጸዋል።
በመድረኮቹ ውይይቶቹ ከተካሄዱበት ዓላማ ባሻገር፣ ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮችም እንደተነሱ ታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እነዚህን ጉዳዮች አስመልክቶ የፖለቲካ ውይይት መድረኮቹን ዓላማ በሚገባ የመረዳትን አስፈላጊነት አንስተው፣ መድረኮቹ ወደ ጋራ መግባባት ለመድረስ እና የሀገሪቱን የፖለቲካ ትርክት ለማበጀት የተዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የዛሬው ውይይት ተጨማሪ የውይይት መድረኮችን በመጪው ሳምንታት ለማካሄድ በመስማማት መጠናቀቁን የጠቆመው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፤ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር በሐምሌ 22፣ 2012 ዓ.ም በተደረገው ስብሰባ የፖለቲካ ውይይት እንዲደረግ ስምምነት ላይ መደረሱንም አስታውሷል።
በቀጣይ ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግስታዊነት፣ ትልቁ ሀገራዊ ተቃርኖ ምንድን ነው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት እና ትክክለኛ ምርጫ እንዴት ማድረግ ይቻላል በሚሉ አራት ርእሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋል ተብሏል። የውይይት መነሻ የሚሆኑ ጽሁፎች የሚያቀርቡ አራት ሰዎችም መመረጣቸው ታውቋል።