ትውልደ ኢትዮጵያዊዋ መዓዛ መንግሥቴ ለዓለም ዐቀፍ ሽልማት ታጨች

ትውልደ ኢትዮጵያዊዋ መዓዛ መንግሥቴ ለዓለም ዐቀፍ ሽልማት ታጨች

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ዓለም ዐቀፉ የሽልማት ድርጅት በየዓመቱ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፉ እና በዩናይትድ ኪንግደም ወይም በአየርላንድ የታተሙ ወጥ የልብ-ወለድ መጽሐፍትን በሚያወዳድረበት የስነ ጽሑፍ ዘርፍ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ  መዓዛ መንግሥቴ የመጨረሻዎቹ ሁለት እጩዎች ውስጥ መግባቷ ተሰማ።
በጎርጎሮሳዊያኑ 1969 የተቋመውና በዚያው ዓመት የመጀመሪያውን ሽልማት የሰጠው ተቋሙ፤ ከሀምሳ ዓመታት በላይም ይህንን ሲያደርግ በቆየበት መንገድ፣ ዘንድሮም ሁለት ሴት አፍሪካዊያን ደራሲዎችን ለሽልማት ማጨቱን ገልጿል።
በትውልድ ኢትዮጵያዊ ፣ በዜግነት አሜሪካዊት የሆነችው መዓዛ መንግሥቴ ፤ ዘ ሻዶው ኪንግ The Shadow king በሚል ርዕስ በታተመው መጽሐፏ  ለሽልማት መታጨቷ ታውቋል።
መቼቱን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጅማሮ የሚባለውና ፋሽስት ጣልያን ኢትዯጵያን በወረረችበት ወቅት ላይ ያደረገው ይህ የመዓዛ መጽሐፍ፤  በጦርነቱ ውስጥ ሴት የነፃነት ታጋዮች ከፍተኛ ተጋድሎ ቢያደርጉም ምን ያህል ከታሪክ መዝገብ እንደተፋቁ የሚዘክርና የነበራቸውንም ግዙፍ ሚና አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑ ተነግሮለታል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ መዓዛ በጎርጎሮሳዊያኑ 2010 የወጣው ቢኒዝ ዘ ላየንስ ጌዝ Beneath the Lion’s Gaze የተሰኘው መጽሐፏን ጨምሮ በሌሎች ሥራዎቿም ትታወቃለች። ይህ ሥራዋ በወቅቱ የጋርዲያን የአፍሪካ ምርጥ 10 መጽሐፍት ተርታ መመደቡ አይዘነጋም።
ለሽልማቱ ከታጩት 6 መጽሐፍት መካከል ለሽልማቱ የታጨው ሁለተኛው መጽሐፍ በዚምባብዌያዊቷ ደራሲ የጺጺ ዳንጋሬምባ ፤ ዚስ ሞርነብር ቦዲThis Mournable Body የተሰኘው መጽሐፍ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

LEAVE A REPLY