በቤኒሻንጉል ጥቃት የሟቾችን አስከሬን ቤተሰብ መውሰድ አልቻለም፤ መከላከያም ወደ ጫካው አልገባም

በቤኒሻንጉል ጥቃት የሟቾችን አስከሬን ቤተሰብ መውሰድ አልቻለም፤ መከላከያም ወደ ጫካው አልገባም

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሰሞኑን ማንነታቸው ያልታወቀ የታጠቁ ኃይሎች በተለያዩ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢዎች በፈጸሟቸው ጥቃቶች በርካታ ሰዎች እንደተገደሉና ንብረት ላይም ጉዳት መድረሱ ተነገረ።

በዚህ ጥቃት ጉዳት ከደረሰባቸውና የቤተሰብ አባላቸው ከተገደለባቸው ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ኃይሉ አዲሱ አባታቸው በቡለን ወረዳ ውስጥ እንደተገደሉባቸው ይፋ አድርገዋል።
ግለሰቡ አባታቸው ከሳምንት በፊት ጳጉሜ 01/2012 ዓ.ም እሁድ ምሽት አንድ ሰዐት አካባቢ ነው በታጣቂዎቹ መገደላቸውን ጠቁመው፤ ከአንድ ሳምንት በኋላ እስካሁንም ድረስ የአባታቸውን አስከሬን አግኝተው ለመቅበር አለመቻላቸውን በምሬት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአባታቸውን አስከሬን ለማግኘት ከጸጥታ አካላት ትብብር ቢጠይቁም “ቆዩ ፣ ወደ ቦታው መግባት አልቻልንም” የሚል ምላሽ እየተሰጣቸው መሆኑንም የጉዳቱ ሰለባ አብራርተዋል።
ሟች ከብቶቻቸውን ከዱር ይዘው ሲመለሱ መንገድ ላይ በታጣቂዎቹ እንደተገደሉ የጠቆሙት አቶ ኃይሉ፤ ገዳዮቹ ለሚፈጽሙት ግድያ ምንም አይነት ምክንያት እንደሌላቸውና ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ አለመታወቁ ነዋሪዋን አስጨንቋል ብለዋል።
ጥቃት ፈጻሚዎቹ ሰዎችን ከመግደል በተጨማሪ መኖሪያ ቤታቸውንም እንደሚያቃጥሉና ዘረፋ እንደሚፈጽሙ የገለጹና ለደኅንነታቸው ሲሉ ስሜ አይጠቀስ ያሉ ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ፤ ለቀናት የዘለቀው ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት በነዋሪው ዘንድ ስጋቶች እንደነበሩ እና በዚሁ ምክንያትም ቀደም ብለው ቤተሰቦቻቸውን ወደ ሌላ ቦታ ልከው እርሳቸው ቤታቸውን እየጠበቁ መቆየታቸውን ይፋ አድርገዋል።
ሆኖም  እሁድ ጳጉሜ አንድ ግን የታጠቁ ኃይሎች አካባቢውን ማተራመሳቸውን እንደሰሙ ወደ ጫካ ሸሽተው ሕይወታቸውን ማትረፍ ቢችሉም፤ ነገር ግን ሲጠብቁት የነበረው የቤታቸው ንብረት ሙሉ ለሙሉ እንደተወሰደባቸው እና በአካባቢው የሚኖሩ የሌሎች ሰዎች ንብረትም በታጣቂዎቹ መዘረፉን ገልጸዋል።
እንደ ግለሰብ ገለጻ ከሆነ ነዋሪ እርሳቸው ከጥቃቱ ሸሽተው ይትረፉ እንጂ እንደ እሳቸው ዕድለኛ ያልነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች መገደላቸውን ጠቁመው፤ እርሳቸው እንዳሉትም የተገደሉ ሰዎችን ብዛት በትክክል ለመናገር ቢቸገሩም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በታጣቂዎቹ መገደላቸውን ተናግረዋል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች በተለያዩ ጊዜያት የሚያጋጥሙ ሲሆን፤ ባለፈው ሰሞን የተፈጸመው ጥቃት ግን በቀናት ውስጥ መደጋገሙን እና እስካሁንም መከላከያም ሆነ የክልሉ ልዮ ኃይል ታጣቂውቹ አሉበት ወደ ተባለው ጫካ ለመግባት እንዳልደፈሩ ነዋሪዎች በመግለጽ ላይ ናቸው።

LEAVE A REPLY