ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆነው እስክንድር ነጋ ከታሰረበት እስር ቤት ወጥቶ ወዴት እንደተወሰደ አለመታወቁን ቤተሰቦቹ ገለጹ።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ ጉዳዮን አስመልክቶ ቤተሰቦቹን ባነጋገረበት ወቅት፤ የእስክንድር ነጋ ቤተሰቦች እስከ ምሽቱ አስራ ሁለት ሰዐት ድረስ የተለያዮ ቦታዎች ቢዘዋወሩም “እዚህ አለ” የሚል ምላሽ አለማግኘታቸውንና በስጋት ውስጥ መሆናቸውን መረዳት መቻሉን አስታውቋል።
የእስክንድር ነጋ ቤተሰቦች እንደተለመደው ዛሬ ማለዳ ስንቅ በመያዝ ታስሮበት የነበረው የቀድሞ የፌደራል ጉዳዮች ቢሮ ቢደርሱም ጠባቂዎቹ እዛ እንደሌለና ወዴት እንደተወሰደም እንደማያውቁ መናገራቸውን ለኢትዮጵያ ነገ ገልጸዋል።
እስክንድርን ፖሊስ ባለፈው ሳምንት ያለ ቀጠሮ ከእስር ቤት ድንገት ፍርድ ቤት ወስዶ ክስ የመሠረተበት ከመሆኑ ጋር ታያይዞ በወቅቱ በቀጣዮቹ ሳምንታት ወደ ቃሊቲ ሊወርድ ይችላል መባሉን ተከትሎ ቤተሰቦቹ ወደ ቃሊቲና ቂሊንጦ በመሄድ ስለመኖሩ ጠይቀው ነበር።