ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል፣ እንዲሁም የብድር ውሎችን ሰነድ አረጋግጦ የመመዝገብ አገልግሎት ላይ የአሠራር ለውጥ አድርጊያለሁ አለ።
የተጠቀሱትን አገልግሎቶች ለማግኘት የሽያጭ ዋጋ ወይም የብድሩ ገንዘብ አከፋፈልን በተመለከተ ክፍያው መፈጸም ያለበት፦
*በሽያጭ ውል ጊዜ የሽያጭ ዋጋው ባንክ ከሚገኝ የገዢ ሂሳብ ተቀናሽ ሆኖ ወደ ሻጭ የባንክ ሂሳብ የተላለፈ (Transfer) መሆን አለበት፣
*በብድር ውል ጊዜ፤ የብድሩ ገንዘብ ባንክ ከሚገኝ የአበዳሪ ሂሳብ ተቀናሽ ሆኖ ወደ ተበዳሪ የባንክ ሂሳብ የተላለፈ (Transfer) መሆን አለበት ሲል የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ አዲስ አሠራር መተግበሩን ይፋ አድርጓል።
ይህ አሰራርም ከነገ መስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ይጀምራል የተባለ ሲሆን፤ ተቋሙ ይህን አዲስ የአሠራር መንገድ ለመተግበር የተገደደው የብር ለውጡን ተከትሎ፤ ከፍተኛ ገንዘብና ሀብት ያከማቹ ግለሰቦችና ቡድኖች ገንዘቡን በውክልናና ሽያጭ አማራጮች ወደ ሌላ የቅርብ ሰዎቻቸው እንዳያዟዙሩት በመስጋት እንደሆነ ተገምቷል።
ተቋሙ እንደገለጸው ከሆነ ህገወጥነትን ለመከላከል ሲባል የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረትን በስጦታ የማስተላለፍ ውልን አረጋግጦ የመመዝገብ አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ አይሰጥም።
የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ አሠራሩን የለወጠው ከባንክ ውጪ የሚንቀሳቀስ ጥሬ ገንዘብን ሥርዓት ለማስያዝ ፣ ህገወጥነትን ለመከላከል እና ዘመናዊ አሰራርን ለማስፈን መሆኑንም ጠቁሟል።