22 ፓርቲዎች የፕሮፌሰሩን ፓርቲ ጨምሮ ከወያኔ ጋር በወያኔ ጋባዥነት ድርድር ጀምረዋል የሚለውን ዜና እየሰማን ባለንበት መድረክ ከኢህአዴግ ጋር የብቻ ድርድር ይፈልጋል ምክንያቱም ዋንኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ስለሆነ የሚል ነገር በፕ/ር በየነ አንደበት ሲነገር ሰማን፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ እንመራለን የሚሉት እርስበርስ ስለሚተዋወቁ እናንተ 22ትም ሆናችሁ 102 አትረቡም ጠንካራው እኔ የምመራው መድረክ ነው ማለታቸው ተቀባይነት ባይኖረውም አያስገርምም፡፡ ህዝቡ መድረክን ርስተ ጉልት ስላደረጉት እርሳቸውም ሆነ ስለ መድረክ ምንም እንደማያውቅ ቆጥረው ይህን ማለታቸው ግን የድፍረታቸውን ልክ የንቀታቸውን መጠን ነው የሚያሳየው፡፡ በወያኔ መሪዎችም በተቀዋሚ ተብየዎችም አክብሮት የተነፈገው ህዝብ፡፡
የፕ/ር በየነን ንግግር እንደሰማሁ እኔ ከማውቀው በላይ ፈጥኖ በአእምሮየ የታወሰኝ አቶ አሰፋ ጫቦ በአንድ ጽሁፋቸው የገለጹዋቸው ነው፡፡ አንዲህ ይላሉ አቶ አሰፋ ፕ/ር በየነን ሲገልጹዋቸው፡፡ “በየነ ጴጥሮስ እላይ በጨረፈታ ለማሳየት ለሞከርኩት ስራው መላውን አለም ደጋግሞ ዞሯልኮ! በዚህ 25 አመት ሙሉ የድርጅቶች መሪነቱ ምን ፈየደ? ምንስ ተናገረ? ምንስ ጻፈ? የሚል ቢኖር ጉዱ ይፈላ ነበር። የሚል ሰው አለመኖሩ የበጀው መስለኝ። እንዳይኖሩ አድርጎ ይሆን? አሁን ግርማን ላከበት? አንዳንዴ ያኔ ከባንክ ገንዘብ ይዞ ጠፍቶ በኋላ የወያኔ አባል ሁኖ የገንዘብም ምክትል ሚንስቴር እንደሆነው ሰውዬ በየነ ጴጥሮስም የወያኔ አባል ይሆን? እላለሁ ይኸው ለ25 አመት ያሁሉ ሰው ወህኒ ሲወርድ በየነ አለምን ይዞራል” ነበር ያሉት፡፡ አዎ! ለምን አንዴት ወዘተ ብሎ የሚጠይቅ ጠፋና እኝህ ሰው ከማንም የበለጥሁ ከሁሉም የታመንሁ ዋንኛው ተቀዋሚ እኔ ነኝ ለማለት በቁ፡፡ ወይ ድፍረት ወይ ንቀት፡፡
ርሳቸውን ለዚህ ካበቃቸው ነገር አንዱ መድረክን ከፍት አድርገው ሳያዩ ዋንኛው ተቀዋሚ እያሉ የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ስራ ነው፡፡ ቢታይ ግን መድረክ ቢከፍቱ ተልባ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ያው ተልባውም በየነና በየነ ብቻ ነው ለማለት የሚያስችል ማስረጃ ማቅረብ ስለምችል በድፍረት እናገራለሁ፡፡
በየነ በሁለት ካርድ፤ ፕ/ር በየነ በ1993 ዓም ሀ ብለው ፖለቲካው ከጀመሩ ግዜ አንስቶ በሁለትና በሶስት ካርድ ነው ሲጫወቱ የኖሩት አሁንም የሚጫወቱት፡፡ በአንድ ግዜ የብሄርም ሀገራዊም ፓርቲ ሊቀመንበብር ሲሆኑ አይተን ርሳቸውን ብቻ ሳይሆን በዚህ ሁኔታ ምስክር ወረቀት የሰጣቸውን ም/ቦርድንም ታዝበናል፡፡የኋላውን ልተወውና አሁን እያደረጉ ያለውን እንይ፤ ለድርድር የተዘጋጁት 22 ፓርቲዎች ናቸው ሲባል እነማን ናቸው ብዬ ፍለጋ ገባሁ፣ ከአገኘሁት ዝርዝር ውስጥ አንድ ቀድሞ ሰምቼው የማላውቅ ፓርቲ ስም አገኘሁና ስጠይቅ ሳጠያይቅ የፕ/ር በየነ መሆኑን ሰማሁ፡፡(የሚመሩት ያላልኩበትን ምክንያት ተረድታችሁልኝ ይሆን!) በአንድ ወገን ፓርቲያቸው ከሌሎች ጋር በመሆን ለድርደር በሉት ለውይይት ተቀምጠዋል፣በሌላ በኩል ደግሞ በመድረክ ሰም ተናጠል ድርድር ይጠይቃሉ፡፡ ምን አልባት ይህ አንዱ የዋና ተቀዋሚነታቸው መግለጫና ማረጋገጫ ይሆን!
መድረክ ቢከፍቱ ተልባ፣በስምንት ፓርቲዎችና በሁለት ተዋቂ ግለሰቦች የተመሰረተ ተብሎ ዋንኛው ተቀዋሚ ፓርቲ እየተባለ ሲሞካሽ ውስጡን የምናውቀው ሰዎች መድረክ በጠንካራ መሰረት ላይ ያልቆመ ምንም የማይፈይድ የት ሊደርስም የማይችል አንደሆነ ተናግረናል ጽፈናል፣በዚህም ስድብ ፍረጃ ውንጀላ አስተናግደናል፡፡ዋንኛው ተቀዋሚ እያሉ የሚያሞግስቱም ሆኑ ዜና የሚሰሩት ወገኖች ግን ጠለቅ ብለው ለማወቅ ቀርቶ ትንሽ ገለጥ አድርገው ለማየት ፍላጎቱም የላቸውምና መድረክም እንደ ወያኔ በቁጥር ጨዋታ ቢከፍቱ ተልባነቱን ደብቆ ይኖራል፣
መቼም መድረክ ጠንካራ ነው ከተባለ ራሱ ፓርቲ አይደለምና በአባሎቹ ማንነትና ምንነት ነው የሚሆነው፡፡ይህ እንዳይታወቅ አንድም አባል ፓርቲዎቹ በሙሉ አይገለጹም ሁለትም በየግዜው የስም ለውጥ ይደረጋል፡፡ መድረክ ሲመሰረት ስማቸው የሰፈረውን ፓርቲዎች ይዛችሁ እነዛው በየግዜው ያደረጉትን ውህደት የስም ለውጥ ብትመለከቱ መድረክ ማነው የሚለው ይጠፋባችኋል፡፡ ይህ መለዋወጥ እንዳለ ሆኖ ከመስራቾቹ ወጣ የተባለ አልሰማንምና እዛ ላይ ተመልሰን ፓርዎቹን እንይና የመድረክን ጥንካሬ ወይ ድክመት እንመስክር፡፡
ከመነሻው በስምንት ፓርቲዎችና ሁለት ተዋቂ ግለሰቦች የሚለው አገላለጽ ተገቢም ትክክልም አልነበረም፣ የቱንም ያህል ቢገዝፍ ግለሰብ ግለሰብ ነው፡፡ወይ ሰዎቹ ዝና ካልፈለጉ ወይ ሌሎቹ በእነርሱ ስም የሆነ ነገር እናተርፋለን ብለው ካላሰቡ በስተቀር የሰዎቹ መጠራት አስፈላጊ አልነበረም፣ ሆኖም አልቀጠለምና አነጋጋሪነቱ አብቅቷል፡፡
ሁለተኛው ስህተት ህብረትና ግንባር አይደለም የተናጠል ፓርቲያቸውን መርተው አንድ ርምጃ ማስኬድ ያልቻሉ ሰው( ራሳቸውን ለምክትል ሚኒስትርነትና ለፓርላማ ወንበር ማብቃታቸው ርምጃ ነው ካልተባለ) ሰው ሊቀመንበር ማድረጉ ነው፡ይህን መሰረት አድርጎ እስካሁን የዘለቀው ነገር ደግሞ መድረክ መድረክ ከፕ/ር በየነ ይዞታ መላቀቅ አለመቻሉ ነው፡፡ እነርሱም አንደ ወያኔ ተጨፎኑ እናሞኛችሁ እያሉን ሊቀመንበርነት በዙር ነው ይሉናል እንጂ ፕ/ር በየነ የመድረክ ፑቲን ሆነው ነው የምናያቸው፡፡
የመድረክ አባል ፓርቲዎች፣
አንድነት-“ ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር አንዲሉ ሁሉም እንገፍ እንገፍ ሲል እናያለን እንጂ የፖለቲካ ትግል የጀመረው ደቡብ ህብረት ነው”ፕ/ የሚሉት ፕ/ር በየነ ባይቀበሉትም ከመድረክ አባላት የተሻለ አቅም የነበረው አንድነት ነበር፡፡ ግና ከመነሻውም የመድረክ አባል እንዲሆን የተፈለገው ገኖ መውጣት የጀመረውን ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ለማሽመድመድ ነበርና ይሄው ተሳክቶ ዛሬ አንድነት በመድረክ ውስጥ ስሙ እንጂ በአካል የለም፡፡ ይህን ያህል አባላት አሉት ለሚለው የቁጥሩ ጨዋታ ቢጠቅም እንጂ ከዚህ የሚዘል ፋይዳ የለውም፡፡
አረና ፣ ስለዚህ ፓርቲ በቂ መረጃ የለኝም፣ ቢሆንም ግን መድረክን ከበየነ ርስተ ጉልትነት ለማላቀቅ ባይችልም ከቁጥር መግለጫነት የዘለለ ፓርቲ እንደሆነ አስባለሁ፡፡
ኦፌኮ- የመድረክን መሰራቾች ቁጥር ሰምንት አድርሰውት የነበሩት በአንድ ብሄር ሰም የሚጠሩት የአቶ ቡልቻና የዶ/ር መረራ ፓርቲዎች ተዋህደው የፈጠሩት ነው ኦፌኮ፡፡ ፓርቲው በኦሮምያ አካባቢ ሰፊ መሰረትም ተቀባይነትም እንዳለው ቢታወቅም መድረክ ውስጥ ያለው በአቅሙ መጠን አይደለም፡፡ ሌላ ሌላው ቢቀር በኦሮምያ ከአንድ አመት በላይ ዜጎች ሲገደሉ ሲታሰሩ ኦፌኮ ያላባራ ጩኸት ሲያሰማ ከመድርክ በኩል የሰማነው ዋንኛ ተቀዋሚ ሊያሰኘው ቀርቶ የኦፌኮን አባልነት የሚመጥን አይደለም፡፡ በርካታ የኦፌኮ አመራሮች ሲታሰሩም የመድረክ ደምጽ ለስላሳ ነው፡፡ የም/ል ሊቀመንበሩን የዶ/ር መረራ እስር ደግሞ መድረክ አይደለም ዋንኛ ተቀዋሚ ተቀዋሚም አንዳልሆነ ያሳየ ነው፡፡ መሪው ታስሮ ዝም የሚል ነእደምን ፓር ሊባል ይበቃል፡፡ በአንጻሩ ደቡብ ውስጥ በተለይ ደግሞ ሀድያ አካባቢ አንድ ነገር ሆነ ከተባለ የመድረክ ጩኸት ነው ቀድሞም ገኖም የሚሰማው፡፡
የበየነ ፓርቲዎች፣ከሀብዴድ እስከ ኢማዴ-ዴህአፓ ድረስ ፕ/ር በየነ የተጠሩባቸው ወይንም ዪጠሩባቸው ፓርቲዎች ህብረቶች ግንባሮች ወዘተ ግራ ስለሚያጋቡኝ ነው ጠቅለል አድርጌ የበየነ ፓርቲዎች ማለቴ፡፡መድረክ ውስጥ እንኳን ደቡብ ህብረት፤ኢዴኃህ፣ሶሻል ዴሞክራሲ፣ማህበረ ዴሞክራሲ ደቡብ ህብረት፣የሚባሉ በርሳቸው የሚመሩ ፓርቲዎች ነበሩ ወይንም አሉ፡፡ መድረክ ሲመሰረት ኢዴኃህና ደቡብ ህብረት ነበሩ ከትንሽ ግዜ በኋላ ደግሞ ደቡብ ህብረትና ሶሻል ዴሞክራሲ ሆኑ፤አሁን ያሉት ሰንትና እነማን አንደሆኑ ባላውቅም (የምርጫ ቦርድ ድረ ገጽም አዲስ መረጃ አይሰጥም)አዲስ ፓርቲ መስረተው ይሁን ወይ አዋህደው ወይንም የአንዱን ሰም ለውጠው ባይታወቅም የኢትዮጵያ ማህበራዊ ዴሞክራቲክ -ደቡብ ህብረት አንድነት ፓርቲ በምህጻሩ ኢማዴ-ዴህአፓ የሚባል ፓርቲ አላቸው፡፡ በዚህ ፓርቲ አማካኝነትም ነው ከ 22ቱ አንዱ ሆነው ለድርድር የቀረቡት፡፡
ኢዴአን፣ይሄ ስሙም መሪዎቹም የማይታወቅ መድረክ የህን ያህል ፓርቲዎች ስብስብ እያሉ የሚዘግቡ ጋዜጠኞችም ሆኖ የሚያወድሱ አባል ደጋፊዎች ለማወቅ ጥረት ያላደረጉበት ከስም ማጀቢያነትና ከቁጥር ማብዣነት ያለፈ ታይቶ የማያውቅ አሁንም በድረክ የአባላት ዝርዝር ውስጥ ይኑር አይኑር የማይታወቅ ነው፡፡
ሶዲኃቅ- ስሙ እንደሚነግረን ቅንጅት ነው፤ግን እንኳን የተቀናጁት ፓርቲዎቸ ራሱ ቅንጅት ተብየው ከነመሪዎቹ አይታወቅም፡፡ ለቁጥር ማደሚቂያነት ግን ውሏል፡፡ አሁን በስም አንኳን መኖር አለመኖሩ አይታወቅም ፡፡
ይሄ ነው እንግዲህ ዋንኛው ተቀዋሚ ፓርቲ ተብሎ የሚነገርለት፣ ፕ/ር በየነንም ለድፍረትና ንቀት ንግግር ያበቃ፤አጀኢብ ነው፡፡ በምርጫ 2007 ከ200 የበለጠ እጩ ማቅረብ ያልቻለ መሆኑንም አክሉበት፡፡
በመጨረሻ ፕ/ር በየነ መድር በኢምፔሪያል ሆቴል ባዘጋጀው ሲፖዚየም ላይ ባቀረቡት የጥናት ወረቀት የአንድና ሁለት ሰው ፓርቲዎች ፓርቲ እየተባሉ የህብረት አባል እንዲሆኑ መደረጉ ላለፉት ህብረቶች መዳከም ዋና ምክንያት ነው ብለው ነበር፡፡ ከላይ ያየናቸው የመድረክ አባሎች ሰንቶቹ ከዚህ ነጻ ናቸው፣የፕ/ር በየነን ፓርቲዎች ጨምሮ?