ሊያነቡት የሚገባ-ታዳሚን እንባ ያራጨው የችሎት ውሎ /በጌታቸው ሺፈራው/

ሊያነቡት የሚገባ-ታዳሚን እንባ ያራጨው የችሎት ውሎ /በጌታቸው ሺፈራው/

ዛሬ በጠዋት ሰብሰብ ብለን የገባነው ወደ 4ኛ ወንጀል ችሎት ነበር። ከ4ኛ ወንጀልችሎት ስወጣ 19ኛ ወንጀል ችሎት ታዳሚውን ያስለቀሰ፣ ዳኞቹን ሳይቀር ያሳዘነ ትዕይን እንደነበር ሰማሁ። 19ኛ ወንጀል ችሎት የነበረ አንድ ጓደኛዬን ማስታወሻውን እንዳየው ጠየኩት። የተጀመሩ ዐረፍተ ነገሮች፣ ያልተቋጩ ሀረጎችን አነበብኩ። በእርግጥ እንባ በሚያራጭ ትዕይንት ውስጥ መፃፍ ከባድ ነው። እኔንም ብዙ ቀን አጋጥሞኛል።የጓደኛዬ ማስታወሻ ላይ የሰፈሩ የተቆራረጡትን ዐረፍተ ነገሮች መዝግቤ፣ ጓደኛዬ በችሎት ያየውን እንዲያብራራልኝ ጠየኩት።

በአማራ ክልል በነበረው ህዝባዊ ንቅናቄ ሰበብ የታሰሩትና በእነ ታደሰ መሸሻ አሰጌ ክስ መዝገብ ከተከሰሱት መካከል 3ኛ ተከሳሽ የሆነው ዮናስ ጋሻው ደመቀ በሌሎች የአማራ ወጣቶች የሚፈፀመው ጭካኔ ተፈፅሞበታል። አስቻለው ደሴና ሌሎች አማራ ወጣቶች እንዳደረጉት ሱሪውን በችሎት አውልቆ “ህዝብ ይፍረደኝ” ብሏል። ሃይላንድ ያንጠለጠሉበትን ብልቱን አሳይቷል። በዚህ ወቅት ታዳሚው አልቅሷል። ጓደኛዬ ይህን ሰቆቃ እያየ በደንብ መፃፍ አልቻለም። ዳኞች እንኳ አንገት ደፍተዋል። በጠዋቱ ችሎት በተከሳሹ ሰቆቃ ያለቀሱትን ታዳሚዎችም አነጋግሬያቸው ነበር። ከሰዓትም ሀዘኑ ሳይለቃቸው ስለ ሰቆቃው ነግረውኛል።

ዮናስ ማዕከላዊ በነበረበት ወቅት ሀይላንድ አንጠልጥለውበታል። በፒብሳ ከታትፈውታል። እግሩ ተጎድቷል። ማዕከላዊ በተፈፀመበት ሰቆቃ የነርቭ በሽተኛ ሆኗል። ይህን ሲናገር ሰቆቃውን ያደረሱበት ሁለት የማዕከላዊ ገራፊዎች ችሎት ውስጥ ተቀምጠው ነበር።

የጓደኛዬ ማስታወሻ አገላበጥኩ። ዮናስ የተበደለው ማዕከላዊ ብቻ አይደለም። ከመታሰሩ በፊትም በቤተሰቡ ላይ በደል ደርሶበታል። ” ወንድሜን ሆን ብለው በኦራል(መኪና) ገጭተው ገደሉት፣ እናቴንም በተመሳሳይ መልኩ ገድለውብኛል። በማዕከላዊ አማራና ኦሮሞ ዘር እንዳይተካ ለምን ይደረጋል? የተማርነው ጥላቻ ነው። የእኛ ትውልድ ከእኛ ምን ይማራል? ሀይላንድ ተንጠልጥሎብኛል። በፒንሳ…… ሁላችንም ጉዳት ደርሶብናል” ብሎ በችሎት ምሬቱን ተናግሯል።

የዮናስ ስቃይ ከማዕከላዊ በኋላም አላበቃም። በማዕከላዊ የደረሰበትን ጉዳት ለመታከም ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል ተወስዶ፣ ከአቅማችን በላይ ነው ብለውታል። ጳውሎስ ሄዶ የአጥንት ስብራት እንዳለበት ማረጋገጫ ቢሰጠውም ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ውጤቱን አጥፍቶበታል። በድብደባው ምክንያት የቀኝ እግሩ ሽባ ወደመሆን ደርሷል። ለዚህም ሽፍን ጫማ ያስፈልጋል። ሆኖም ሽፍን ጫማውን ገብረእግዚ የተባለ የገዥዎች ወገን ቀዶ ጥሎበታል። “ሽፍን ጫማ ለማድረግ እንኳ ብሔር መቀየር አለብን” ሲልም ገዥዎቹ እያደረሱበት ያለው በደልና ጭካኔ ቅጥ ጠይቋል።

ጠዋት ቀጠሮ የነበራቸው ተከሳሾች ጉዳይ ከሰዓትም ይቀጥላል ስለተባልን ከማህሌት ፋንታሁን ጋር ከሰዓት ወደ 19ኛ ወንጀል ችሎት አቀናን።ተከሳሾቹ ወደ ቂሊንጦ ሄደው ስለነበር ችሎት ስራ ይጀምራል ከተባለው ሰዓት ዘግይተው ደረሱ። ከሌሎች ተከሳሾች ቀደም ብሎ አንድ ተከሳሽ እያዘገመ ነው። በቀኝ ጎኑ በኩል ሌላ ተከሳሽ ደግፎታል። ወዲያውኑ ከኋላው የነበሩት ተከሳሾች አለፉትና ተደግፎ ከኋላ ማዝገም ጀመረ። በጠዋቱ የችሎት ጊዜ ሱሪውን አውልቆ የተፈፀመበትን በደል የተናገረው ተከሳሽ እንደሆነ መገመት ችያለሁ። ተከሳሾች ወደ ችሎት ከገቡ በኋላ እኛም ለመታደም ገባን። ተደግፎ ፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ ወዳለው ጊዜያዊ ማቆያ ያቀናው ተከሳሽ ፊት ወንበር ላይ ተቀምጧል። የቀኝ እግሩ ለሚያየውና የደረሰበትን በደል ለሚገምት በሚሰቀጥጥ መልኩ ይንቀጠቀጣል። ተቀምጦ እንኳን በቀኝ እግሩ አይረግጥበትም። የቀኝ የሰውነት ክፍሉ እስከ ትክሻው ድረስ ይንዘፈዘፋል።ችሎቱ ስራ ላይ በነበረበት ሰዓት ለሽንት ተደግፎ ሲወጣ የቀኝ እግሩን በደንብ አይረግጥበትም። ይጎትተዋል ማለት ይቀላል።

የማዕከላዊ ምስክሮች

ከሰዓት በነበረው የፍርድ ቤቱ ሰዓት ሁለት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ተሰምተዋል። በቀዳሚነት የተመሰከረበት ደግሞ ሰቆቃ የተፈፀመበት ዮናስ ነው። ምስክሩ ባህርዳር ከተማ ይኖር የነበር ደላላ እና የሆቴል ባለቤት ነኝ አለ። አሁን ተፈትቼ ባህርዳር እገኛለሁ ብሎ ቃሉን ሰጠ። እውነታው ግን ሌላ ነው። ዮናስ ጋሻው ወደ ግንቦት 7 እንድልከው ጠይቆኝ ነበር ብሎ መሰከረ። ቆይቶ ደግሞ የአማራ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ (አሕነን) የተባለ፣ የግንቦት 7 ቅርንጫፍ ነው ያሉት ቡድን እንዲቀላቀል በአንድ ስብሰባ እንደተነገረው፣ ከምሽቱ 12 ሰዓት ተሰብስው ማታው መንግስትን ለመገልበጥ ጦርነት ሊያደርጉ፣ ምስክሩም አባል እንዲሆን በተነገረው በነጋታው በተነገረው ጦር አደራጅቶ አባይን ሊያስዘጋ ተልዕኮ እንደተሰጠው መሰከረ። ምስክሩ መረጋጋት አይስተዋልበትም። የሚሰጠው መልስ ይበቃል እየተባለ እንኳን ማብራሪያውን ይቀጥላል። ዐቃቤ ሕግ፣ ፍርድ ቤቱም፣ የተከሳሾች ጠበቃም “በቃ” እያሉት አይበቃውም።

ፍርድ ቤቱ በመሃል እየገባ “ወደ ግንቦት 7 ለመሄድ የሚጠየቁት ምን ሰለሆኑ ነው? ወደ ግንቦት 7 እንዲልኩት ሲጠይቅ የነበረ ሰው እንዴት የግንቦት 7 ቅርንጫፍ ነው የተባለ ቡድን መስርቶ እንዲቀላቀሉ ይጠይቅዎታል? በአንድ ቀን ዝግጅት እንዴት ጦርነት ይደረጋል? አንድ ቀን ተነግሮዎት ያለ ዝግጅት እንዴት አባይን ያስዘጋሉ? ማን ጋር ሆነው አገኙት?……” ብዙ ብዙ ጥያቄ አነሳ። 19ኛ ወንጀል ችሎት ዳኞች አንድ ቀን በማጣሪያ ጥያቄ ምስክርን አጥብቀው ሲጠይቁ አይቻለሁ። ዶ/ር መረራ ጉዲና ሲመሰከርባቸው። እንደዛሬው ምስክርነት ግን ግራ ሲጋቡ፣ ግራ የተጋቡበትን የምስክርነት ቃል ለተከሳሽ የሚጠቅም በሚመስል መልኩ ሲጠይቁ አይቼ አላውቅም። ምን አልባት፣ ጠዋቱ የፍርድ ቤቱ ሰዓት የተነገረው ተፅዕኖ ፈጥሮ ይሆናል።

ተከሳሾች በጠበቃ አለልኝ ምህረቱ በኩል ምስክሮቹ ማዕከላዊ ታስረው እንደነበር፣ ተገደው እንደመሰከሩ፣ በድብደባ ብዛት “ልንመሰክርባችሁ ነው” ብለው ለተከሳሾች እንደነገሯቸው ጠየቁ፣ ዳኞችም አጣሩ። አንደኛው ምስክር “ሁላችንም ከምንታሰር የተወሰንነው ለቤተሰብ እንድረስ ብያቸዋለሁ” ብሎ አመነ። በጠበቃና በዳኞች ጥያቄ ብዛት ሌላኛው ምስክርም “መንግስት ምህረት ያደረገልኝ በእነሱ ላይ እመሰክራለሁ ስላልኩ ነው” ብሎ የማዕከላዊ ምስክር መሆኑን ተናገረ። ስልክ ስለመደዋወል ሲመሰክር የነበረው አንድ ምስክር “አሁን ስልክ የት አለ?” ሲባል “አልጋ የያዝኩበት ሆቴል አስቀምጨቃለሁ” ብሎ ተናገረ። ስልክ ቁጥሩን ሲጠየቅም “092 352 9019” ብሎ ተናገረ። ከችሎት እንደወጣሁ በዚህ ቁጥር ላይ ደወልኩ። ከቴሌ የድምፅ መልዕክት “ይህ ቁጥር አይታወቅም……” የሚል መልስ አገኘሁ። እኔ ስታሰር የተወሰደብኝ ስልክ ቁጥር አልተመለሰልኝም። ሁ በእኔ ቁጥር ላይም ስደውል የሚሰጠኝ መልስ ተመሳሳይ ስለሆነ ይህ ምስክር አሁን እጠቀምበታለሁ ያለው ስልክ ሲታሰር ተወስዶበት ቴሌ ቁጥሩን እንዳልለመለሰለት ግልፅ ሆነልኝ። እሱ ግን እጠቀምበታለሁ ብሎ መስክሯል። የማዕከላዊ ምስክር ከዚህ ውጭ ይላል ተብሎ አይጠበቅም።

ምስክሮቹ በዳኞችና በጠበቃ አለልኝ ምህረቱ ሲጠየቁ ” በምህረት ተፈትተናል” ብለዋል። የተፈቱበትን ቀን፣ ወርም ሲጠየቁ መልሳቸው “አናስታውስም” ነው። አልተፈቱምና የተፈቱበትን ቀን ሊያስታውሱ አይችሉም!

ተከሳሾቹም ምስክሮቹ ማዕከላዊ ታስረው እንደሚገኙ፣በእነሱ ላይ በሀሰት መስክረው እንደሚለቀቁ ቃል ተገብቶላቸው በሀሰት እንደሚመሰክሩባቸው ተናግረዋል። ሰቆቃ ደርሶበት ሱሪውን በችሎት አውልቆ ሀይላንድ የተንጠለጠለበትን ብልቱን ያሳየው ዮናስም በጠዋቱ ችሎት ምስክሮቹ ማዕከላዊ ታስረው፣ በግድ መስክሩ እየተባሉ እንደሆነ ተናግሮ ነበር። እውነታውም ይሄው ነው!

ሁለቱ ምስክሮች መስክረው ችሎት ተጠናቅቆ ስንወጣ የገቡት ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ መኪና ነበር። እስረኞች ወደሚመላለሱበት፣ እኔም በአንድ ወቅት የማዕከላዊ እስረኛ ሆኜ ወደተመላለስኩበት መኩና እንጅ አልጋ ወደያዙበት ሆቴል የሚያደርሳቸው መኪና ውስጥ አልገቡም። ጉዟቸው ጓደኞቻቸው ወደተሰቃዩበት፣ እነሱም ተሰቃይተው በሀሰት እንዲመሰክሩ ወደተገደዱበት ወደ ማዕከላዊ ነው። ዮናስ አካሉን ወዳጣበት፣ ብልቱ ላይ ውሃ ወደተንጠለጠለበት፣ ኢህአዴግ ደርግ ሲጠቀምበት ነበር ብሎ 26 አመት ሙሉ አማራ እና ኦሮሞ ወጣቶችን ወደሚያሰቃይበት ማዕከላዊ! ምስክሮች የሄዱት ተፈትተን እንኖርበታለን ወዳሉት አማራ ክልል ሳይሆን ትህነግ/ህወሓት የአማራ ወጣቶችን ብልት ወደሚሰልብበት፣ የትህነግ የጥላቻ ጥግ ወደሚታይበት ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ!

LEAVE A REPLY