• አሁን የሚያስፈልገን የአስቸኳይ ጊዜ አንድነትና ፍቅር ነው
• ማረሚያ ቤት መታረሚያ ቦታ እንጂ መሰቃያ መሆን የለበትም
• የጋዜጠኝነት ሙያ እዚህ የደረሰው በጋዜጠኛው ብርታት ነው
• የሽብርን አስከፊነት እኛ ኢትዮጵያውያን አሳምረን እናውቀዋለን
ከሰሞኑ ከእስር ከተፈቱት ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፤ለ7 ዓመት በእስር ቤት በነበረው ቆይታ፣ በጋዜጠኝነት ሙያው፣ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡
– በሽብር ወንጀል ተጠርጥረህ የታሰርክበት አጋጣሚ እንዴት ነበር?
የታሰርኩት ሰኔ 12 ቀን 2003 ዓ.ም ነው። ሁኔታዎች በጣም እየተወሳሰቡ የመጡበት ወቅት ነበር፡፡ ምናልባት በወቅቱ እፅፋቸው በነበሩ መጣጥፎች ላይ በስፋት ፀረ ሽብር ህጉን እተች ነበር፡፡ ፀረ ሽብር ህጉ በጣም ከባድ መሆኑንና አሳሳቢ መሆኑን ለማመላከት የአቅሜን እጥር ነበር። ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ደግሞ እየተካረሩ የመጡበት ሁኔታም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት እንዲሁ የሆነ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል እገምት ነበር፡፡
በኋላ ሰኔ 12 ቀን የጋዜጣ ኤዲቶሪያል ስብሰባ ነበረኝ፡፡ ወደ ቢሮ ስሄድ ብዙ ሰዎች ይከተሉኝ ነበር፡፡ በወቅቱ የሆነ ችግር እንዳለ ገምቼ፣ እኔም ሁኔታውን በጥንቃቄ እከታተል ነበር፡፡ በኋላ ወደ ኢንተርኔት ካፌ ገባሁና ሊሲፒጂኤ እና ለጋዜጠኛ ማህበራት ስለ ሁኔታው በኢ-ሜይል አሳወቅሁኝ፡፡ የጠረጠርኩት አልቀረም፣ እዚያው ኢንተርኔት ቤት እያለሁ፣ ብዙ የፌደራል ፖሊስ አባላትና ተሽከርካሪዎች መጥተው ያዙኝ፡፡ በወቅቱ በሁኔታው ተገርሜ ነበር፡፡ ምናልባት ሄሊኮፕተር ነው የቀረው እንጂ የተሽከርካሪና የፖሊሶችን ብዛት ላየ፣ አንድ በእጁ ብዕርና ወረቀት የያዘን ጋዜጠኛ ለመያዝ አይመስልም፡፡ እኔ በህይወቴ መሳሪያ የሚባል ነገር ነክቼ አላውቅም፡፡ ግን ሁኔታውን ለተመለከተ፣ መሳሪያ የያዝኩ ነበር የሚመስለው። በኋላም ቤቴ ተፈተሸ፡፡ በሽብር ተጠርጥረህ ነው ተባልኩ፡፡ ይሄን ሲሉኝ፣ ቀልድ ነበር የመሰለኝ፤ በኋላ ቤቴ ተፈትሾ፣ ከ4 በማያንሱ ፌስታሎች፣ ወረቀቶችና የተለያዩ መንፈሳዊ ፊልሞች እንዲሁም ካሴቶች በሙሉ ተወሰዱ፡፡ እኔ ቤት ውስጥ ከመዝሙርና ከመንፈሳዊ ፊልሞች ውጪ ምንም የለም፡፡
እነሱም በኋላ ይሄን ሲረዱ፣ የወሰዱትን በሙሉ ለባለቤቴ መልሰውላታል፡፡ ይሄን የቤት ውስጥ ብርበራ ሲያደርጉ፣ እስከ ዛሬ ከህሊናዬ የማይጠፋው፣ ሁለት እጆቼ በካቴና ታስረው፣ ልጄ ሊጠመጠምብኝ እየሮጠ ሲመጣ፣ በድንገት እጄ ላይ ያለውን ሰንሰለት አይቶ፣ የደነገጠው ድንጋጤና መሸማቀቅ ነው፡፡ ልጄ በወቅቱ ፊቴን አያይም ነበር።
ገና 2 ዓመቱ ነበር፡፡ ነገር ግን እጄን ነበር አተኩሮ ያይ የነበረው፡፡ ይሄ እስከ ዛሬ አዕምሮዬ ውስጥ የፈጠረው መጥፎ ጠባሳ አለ፡፡ ልጄ “ፍትህ”፤ በልጅነቱ ሳቂታና ተጫዋች ነበር፡፡ አሁን ግን ዝምተኛና ብዙ የማይናገር ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ እኔን ለመጠየቅ ሲመላለስም በዝምታ ይመለከተኛል እንጂ ብዙ አያናግረኝም ነበር፡፡
– ማዕከላዊ ከገባህ በኋላ የምርመራ ሂደቱ ምን ይመስል ነበር?
ማዕከላዊ በነበረው ምርመራ ሁሉም ነገር ከመጀመሪያው ነው የሚጀመረው፡፡ አስበሃል ወይ? እያሉ ነው የሚጠይቁት፡፡ እነሱ አስቧል ብለው ለያዙት ሰው እንኳ በቂ መረጃና ማስረጃ የላቸውም። እኔ ለውጭ ሚዲያዎች ስሰራ ሙያዬን ጠብቄ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ለ8 ወራት ተጠልፈዋል የተባሉትን የስልክ ንግግሮች ለየትኛውም በጉዳዩ ላይ ጥናት ለሚሰራ አካል ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፡፡ መደበኛ የመረጃ ልውውጥ፣ ንግግሮችን ነው ሳደርግ የነበረው፡፡ እነሱ መረጃ አምጣ እያሉ ድብደባ ፈፅመውብኛል፡፡ ብርሃን በሌለውና ሙቀት በሌለው ቤት ውስጥ ለ90 ቀናት እንድቆይ ተደርጌአለሁ፡፡
የኔ እንደውም በምርመራ ሂደት ዓይናቸውን ካጡት፣ የመራቢያ አካላቸውን ከተጎዱት የተሻለ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ እርግጥ ነው በድብደባ ብዛት ጆሮዬ ለረጅም ጊዜያት ደም ይፈሰው ነበር፡፡ ከዚያ በተረፈ ስነ ልቦናን የሚጎዱ፣ በብሄር ማንነት ላይ ያተኮሩ ዘለፋዎች ነበሩ፡፡ እኔ የማውቀው ሰው መሆኔን ነው፤ ግን ዘለፋው አዕምሮ ይጎዳ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ እንግዲህ በኋላ ላይ የሰጠውን ፍርድ ሰጥቷል፡፡
– በአንተ የክስ ክርክር ላይ “ኦፕሬሽን” የሚል ቃል እንደ ማስረጃ ቀርቦ ነበር፡፡ እስቲ ስለሱ ንገረን?
ጉዳዩ እንግዲህ አባታችን ታመው እኛ ጋ መጥተው ነበር፡፡ ሃገር ውስጥ ያለሁት ወንድ የቤተሰባችን አባል እኔ ብቻ ስለነበርኩ፣ ህክምናቸውን የምከታተለው እኔ ነበርኩ፡፡ በወቅቱ እሳቸው ኦፕራሲዮን ተደርገው ከውጪ ወንድሜ ይደውልልኝና፤ ”አባታችን እንዴት ናቸው?” ይለኛል። እኔም፤ “አይ አሁን በቃ አታስብ፣ ኦፕሬሽኑን አድርጓል” አልኩት፡፡ ይሄ ቃል የሆነ ኦፕሬሽን ነው ተብሎ ነው፣ የምርመራው አካል ሆኖ የቀረበው፡፡ ሁኔታው ይሄን ይመስላል፡፡ አባታችንም እኔ እስር ቤት ሆኜ፣ ህይወታቸው አልፏል፡፡ ሌሎችም በጣም የተዛቡ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ለዚህ ነው በጉዳዩ ላይ ጥናት ማድረግ ለሚፈልግ መረጃ መስጠት እችላለሁ ያልኩት፡፡ ሌሎች እንደ ማስረጃ የቀረቡብኝ ፅሁፎች ደግሞ አምኜባቸው፣ ሃሳቤን ይገልፁልኛል ብዬ የፃፍኳቸው፣ የምወዳቸው ፅሁፎች ናቸው፡፡ በወቅቱ ምንም ማድረግ ስለማይቻል፣ ፍ/ቤቱ በኛ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ በአክብሮት ተቀብለነዋል፡፡
– በወቅቱ የ14 ዓመት እስራት ይፈረድብኛል ብለህ ጠብቀህ ነበር?
መሬት ላይ ያለውን ሃቅ እንገምግም ከተባለ፣ ሊከሰስ ይገባል ብባል እንኳ መከሰስ የነበረብኝ በሚዲያ አዋጁ መሰረት ነበር፡፡ በመረጃ ልውውጡ ወቅት ሀገሪቱን የሚጎዳ ነገር ተፈጽሟል ከተባለ እንኳ በሚዲያ አዋጁ ነበር ሊታይ የሚገባው። ነገሩን ለጥጠው በሽብር አዋጁ ነው የከሰሱኝ። የሽብርን አስከፊነት እኛ ኢትዮጵያውያን እናውቀዋለን፡፡ በሃይማኖትና በግብረ ገብ ተቀርፀን፣ በእዝነት እንድናድግ ሆነን ነው እኛ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦችን የሚያሳድጉን፡፡ ይሄ ስነ ልቦና ለሽብር ያውም በገዛ ሀገር ላይ ሽብር ለመፈጸም በእጅጉ ሩቅ ነው፡፡ እኔም በወቅቱ በሽብር ተከሰሃል ስባል፣ ከፍተኛ ቅጣት ነው የጠበቅሁት፡፡ እርግጥ አንድም ምስክር አልቀረበብኝም ነበር፡፡ ተከላከል ስባልም ተከላክያለሁ፡፡ ግን ያው 14 ዓመት እስራት ተፈረደ። ፍርዱ ሲሰጥ አስገርሞኛል እንጂ አላስደነገጠኝም ነበር፡፡
– የማረሚያ ቤት ቆይታህስ ምን ይመስላል?
እንግዲህ ማረሚያ ቤት የቆየሁት ለ7 አመታት ያህል ነው፡፡ በማረሚያ ቤት መቆየት ብዙ ነገር ለማሰላሰል፣ የጥሞና ጊዜ ለማግኘት ይረዳል። መከራዎች፣ እንግልቶችና መገፋቶች መልካም ነገር ነው የሚያወጡት፡፡ ወተት ሲናጥ ነው ቅቤ የሚወጣው፤ አበባ ሲረግፍ ነው ዛፍ ፍሬ ማፍራት የሚጀምረው፡፡ የማረሚያ ቤት ቆይታዬን በዚህ ነው የምገልፀው፡፡ አብዛኛውን ጊዜዬን ዝዋይ ነው ያሳለፍኩት፡፡ በወቅቱ ጉዳያችን በመላው ህዝብ ዘንድ ትኩረት ማግኘቱ፣ ብዙ ወገን ከጎናችን መቆሙን ስንሰማ፣ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ስለኛ እየተሟገተ መሆኑን ስንረዳ ተስፋችን ይለመልም ነበር፡፡ በአሉታዊ ጎኑ ደግሞ ምናልባት እኔ ጠንካራ ባለቤት ስላለችኝ ቤተሰቤ እንደነበረ ጠበቀኝ እንጂ በርካታ ቤተሰብ በዚህ ምክንያት ፈርሷል፡፡ እኔም ወላጅ አባቴን ማገዝ ስችል በመታሰሬ ሳላግዘው አጥቼዋለሁ፡፡
በማረሚያ ቤት ህክምና አናገኝም ነበር። በአንድ ወቅት እንደውም የኩላሊት ጠጠር ያመኝ ስለነበር እንድታከም ወደ ሆስፒታል ሪፈር ተፅፎልኝ፣ በማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ተከልክያለሁ። ብዙ አስነዋሪ ነገሮች አሉ፡፡ በማረሚያ ቤት የብዙ ሰዎችን መከራ መመልከት ይቻላል፡፡ ድብደባዎች ይፈፀማሉ፡፡ እውነቱን ለመናገር የሚሰማ አካል ካለ፣ ይሄ መመርመር አለበት፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በዘፈቀደ የሚቀጠቀጡበት ቦታ እስር ቤት ነው። ማረሚያ ቤት ማለት እኮ መታረሚያ ቦታ እንጂ መሰቃያ መሆን የለበትም፡፡ በድብደባ ብዛት የሞቱ ሰዎች አሉ፡፡ እኔ በመፅሐፌ በዝርዝር ፅፌዋለሁ፡፡ ግን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የተባለው ተቋም፣ ይሄን እንኳ ለማጣራት ጥረት ሲያደርግ አንመለከተውም፡፡ ራሳቸውን አጥፍተው ሞቱ የሚባሉ የኦነግ ተከሳሹን ኢ/ር ካሳሁን ጨመዳን ጨምሮ በርካቶች አሉ፡፡ ለምን ይሄ ጉዳይ አይጣራም? መጣራት አለበት፡፡ እኔ በብዛት ከእነ ጀነራል አሳምነው ፅጌ ጋር ከሌሎች እስረኞች ተገልለን ነው ታስረን የቆየነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አንችልም፣ የካፌ አገልግሎት አናገኝም። ከሌሎች እስረኞች ጋር እንድንገናኝ አይፈለግም ነበር፡፡
– ለምንድን ነው እንደዚያ የሚደረገው?
ያው እኛን ለመጉዳት ነው፡፡ የማግለል ስራ ነው የሚሰራው፡፡ ስለ ምግቡ እንኳ ባናነሳው ነው የሚሻለው፡፡፡ እንጀራውና ወጡ ከምን እንደሚሰራ እንኳ አናውቅም፡፡ በጣም አቅምን የሚያዳክም ምግብ ነው፡፡ በአብዛኛው ያለ ምግብ ነው የኖርነው ማለት ይቻላል፡፡
– እዚያው እስር ቤት ሆነህ ሁለት መፅሐፍትን አሳትመሃል፡፡ እንዴት ነው የተሳካልህ?
የሰው ልጅ አካሉ ቢታሰርም አዕምሮው ማሰብ አያቆምም፡፡ በተቻለኝ አቅም ተደብቄ ነበር የምፅፈው፡፡ የምፅፋቸውን ደግሞ ፖሊሶች የማያገኙት ቦታ እደብቃለሁ፡፡ አወጣጡ የራሱ መንገድ አለው፡፡ ያን መንገድ አሁን መግለፁ ብዙም አስፈላጊ አይሆንም፡፡ ሌሎችም ያንን መንገድ ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ በዚህ መልኩ ነው፣ መፅሐፎቼ ወጥተው የታተሙት፡፡
– በማረሚያ ቤት ሳለህ፣ አብዛኛውን ጊዜህን እንዴት ነበር የምታሳልፈው?
በብዛት መፅሐፍት አነባለሁ፡፡ በሳምንት አንድ ቀን ወደ ቤተ መፅሐፍት በጥበቃ ታጅበን እንሄዳለን፤ 5 ደቂቃ ይሰጠናል፡፡ በ5 ደቂቃ ውስጥ አንድ የምንፈልገውን መፅሐፍ መርጠን፣ ተመልሰን እንገባለን፡፡ ከዚያ ውጪ የምንፈልጋቸውን መጽሐፍት፣ ከውጪ በተለያየ መንገድ እናስገባለን። ሌላው ስፖርት በብዛት እንሰራለን፤ የፀሎት ጊዜም አለን፤ ስለተለያዩ ጉዳዮችም እንወያያለን፡፡ እስር ቤቶች የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች መገኛ ናቸው። ከሁሉም ጋር እንወያያለን፡፡ እነዚህን በመሳሰሉ ነገሮች ነበር ጊዜያችንን የምናሳልፈው፡፡
– የትኞቹን ሚዲያዎች ትከታተሉ ነበር?
ያው ኢቲቪ አለ፡፡ ጋዜጦች አይገቡም፡፡ በመጨረሻ አካባቢ ደግሞ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (OBN) እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ በተለያየ መንገድ ግን መረጃዎችን ለማግኘት እንሞክር ነበር። እነ ኦሮማይን የመሳሰሉ መጻህፍት እኮ መግባት አይችሉም፡፡ ምናልባት ማስገባት የሚቻለው የተረት መጻህፍት ይመስለኛል፡፡
– እስር ቤት ሆነህ ሁለት ዓለማቀፍ ሽልማቶችን አግኝተሃል፡፡ በሽልማቶቹ ምን ነበር የተሰማህ?
እንግዲህ አንደኛው ሂውማን ራይትስ ዎች ያበረከተልኝ ሽልማት ሲሆን ሁለተኛው የሲኤንኤን መልቲ ቾይዝ አፍሪካ ዓመታዊ ሽልማት ላይ “የዓመቱ ጋዜጠኛ” በሚል የተሸለምኩት ነው፡፡ እነዚህ ሽልማቶች እኔ ከሌላው የበለጠ ስለሰራሁ የተሰጡኝ አይመስለኝም፡፡ ሽልማቶቹ ተምሳሌታዊ ናቸው፡፡ ሌላው አለም እየተከታተለን እንደሆነ ለማሳየት የተደረጉ ሽልማቶች ይመስሉኛል፡፡ ሽልማት ይሰጥ ከተባለ ኢትዮጵያ ውስጥ 30 እና 40 ዓመት በጋዜጠኝነት የሰሩ የምናከብራቸው ጋዜጠኞች አሉ፡፡ እኔ በጋዜጠኝነት የቆየሁት ለ10 ዓመት ነው፡፡ ግን ሽልማቶቹን በአክብሮት እቀበላቸዋለሁ፡፡ ለኔ ከሁሉም በላይ ሽልማቴ፣ የኔን ጉዳይ ሲከታተሉ የነበሩ ሰዎች የሚለግሱኝ ፍቅር ነበር፡፡ አስታውሳለሁ፣ በፊት ቢሮዬ እየመጡ፣ ጋዜጣ በነፃ የምሰጣቸው አንድ ጡረተኛ ሽማግሌ ነበሩ፡፡ እሳቸው ለባለቤቴ 20 ብር ሰጥተዋት፣ “ሙዝ ገዝተሽለት ሂጂ” ያሏት ነገር፣ ዛሬም ከህሊናዬ አልወጣም፡፡ ከዚህ የሚበልጥ ሽልማት ለኔ የለም፡፡
– በይቅርታ ለመፈታት ያመለከትክበት አጋጣሚ እንደነበር ሰምቼአለሁ፡፡ በእርግጥ ይቅርታ ጠይቀህ ተከልክለሃል?
ሁላችንም እንደምናስታውሰው፤ ሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኞች፣ ርዕዮት ዓለሙና እኔን በወቅቱ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ህብረት ፕሬዚዳንት የነበረው አቶ አንተነህ አብርሃም፣ የአለማቀፍ የጋዜጠኝነት ህብረት ተወካይና ሌሎች ሰዎች መጥተው አነጋገሩን፡፡ እኛ እንድትፈቱ ነው የምንፈልገው፣ መንግስት ሊፈታችሁ ይፈልጋል። ለምን ነገሮችን እዚህ ጋ አንቋጭም የሚል ሃሳብ አቀረቡ፤ ሁለቱ ስዊድናዊያንና እኔ ይሄን ተቀብለን የይቅርታውን ሰነድ ሞላን፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ፣ ”የጥቁርና ነጭ ደም አይለያይም” ብለው ነበር፤ በኋላ ግን ነጮቹን በመፍታት እኔን በማቆየት እንደሚለያይ አሳይተውናል፡፡ ነጮቹን ወዲያው ለቀቋቸው፣ እኛን አቆዩን፡፡ አሁን ግን “ይቅርታ አድርገንላችኋል፣ ትቀበላላችሁ አትቀበሉም” የሚል አማራጭ ነው ያቀረቡልን፡፡ እንቀበለዋለን ብለን ወጥተናል፡፡
– በዚህ መንገድ ከእስር እፈታለሁ የሚል ግምት ነበረህ?
መቼ እና እንዴት የሚለውን መገመት ባልችልም በመሃል እንደምፈታ ተስፋ አደርግ ነበር፡፡ በኛ ጉዳይ ተመሳሳይ ፍርድ የተፈረደባቸው ሲፈቱ ሳይ፣ ተስፋ አደርግ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ሁኔታ ተገማች አይደለም፡፡ ተገማች አለመሆኑ ደግሞ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን አይነት የአፈታት መንገድ አልገመትኩም፡፡
– በእስር ላይ ሆናችሁ ሀገሪቱ ባለፉት 3 ዓመታት ያሳለፈችውን ፖለቲካዊ ቀውስ በተመለከተ ምን ያህል መረጃ ታገኙ ነበር?
መረጃዎችን በደንብ እንከታተል ነበር፡፡ በተለያየ አማራጭ እያንዳንዷን ነገር እናገኝ ነበር፡፡ ከፖሊሶችም ቢሆን መረጃ የምናገኝበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡
– እንደ ጋዜጠኝነትህ፣ የሀገራችንን የጋዜጠኝነት ሙያ እንዴት ትገልፀዋለህ?
የኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ በብዙ ጎታች ነገሮች ወደ ኋላ እየተጎተተ፣ ጥርሱን ነክሶ ወደፊት ለመግፋት የሚሞክር ነው፡፡ የሀገሪቱ የጋዜጠኝነት ሙያ እዚህ የደረሰው፣ አሰሪ ሁኔታዎች በመኖራቸው ሳይሆን በጋዜጠኛው ብርታት ነው፡፡ ሁሉም ጋዜጠኞች ብዙ ይጥራሉ፡፡ የግሉ ሚዲያ ደግሞ በመከራ ውስጥ ያለ ነው፤ ይሄን ተቋቁሞ ወደፊት ለመግፋት የሚውተረተር ነው፡፡ በጥቅሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን ጋዜጠኞች፣ ምስኪን ጋዜጠኞች ነን፡፡ በብዙ ፈተና እና ትግል ውስጥ ነው የምናልፈው። እኔ ለምሳሌ በሙያዬ ስንቀሳቀስ፣ ከ5 ጊዜያት በላይ ታስሬያለሁ፣ ታግቻለሁ፡፡ ሂደቱ እጅግ ፈታኝና በምስቅልቅሎሽ የተሞላ ነው፡፡ ወደ ኋላ በሚጎትቱ አሰራሮች፣ ደንቦችና ስልታዊ ደባዎች የተጠፈረ የሙያ መስክ ቢኖር ጋዜጠኝነት ነው፡፡ እስካሁን ያለፍንበት ሂደት የመገፋፋት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ የሚኖረውን ሂደት አላውቅም፡፡ የተሻለ ነገር እንዲመጣ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
– አሁን ሀገሪቱ ያለችበትን ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዴት ትገልጸዋለህ?
አሁን ብዙ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉ፡፡ ጫፍ ላይ ነው ያለነው፡፡ ሃይማኖታዊ በዓል ሲያከብሩ ሰዎች እየሞቱ ነው፡፡ ብዙ ምስቅልቅል ነገሮችን እንመለከታለን፡፡ በነዚህ መሃል ደግሞ የነበሩ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ነፃነት፣ ዲሞክራሲ ፈልጓል፡፡ አሁን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳይሆን አስቸኳይ ውይይት ነበር የሚያስፈልገን። የአስቸኳይ ጊዜ አንድነት፣ ፍቅር ነው የሚያስፈልገን። ሰራዊት ማሰማራት ሳያስፈልግ፣ ሁሉንም ነገር በፍቅር ማስተካከል ይቻላል፡፡ እውነተኛ የሀገር ሽማግሌዎች ስራቸውን መስራት አለባቸው፡፡ ኢህአዴግ በአውራ ጣቱ ቆሞ ሳይሆን ቁጭ ብሎ ነው መወያየት ያለበት፡፡ ዶ/ር መረራ እንዳሉት፤ ሁለቱም ወገኖች መቀራረብ አለባቸው። መፍትሄው ያለው ሁለቱም ጋ ነው፡፡ ነገር ግን ፈለግንም አልፈለግንም ከእንግዲህ ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ላይ ማበቡ አይቀርም፡፡
የዲሞክራሲ ፀሐይ መውጣቱ አይቀርም፡፡ ይሄ የብሄር ማንነት ላይ የሚደርስ ጥቃት መቆም አለበት፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ዝዋይ እያለሁ፣ ማረሚያ ቤት ድረስ እየመጡ የሚጠይቁኝ አደይ፣ ትርሃስ የሚባሉ እናቶች ነበሩ፡፡ ከልባቸው ጠይቀውኝ፣ መርቀውኝ ነበር የሚሄዱት፡፡ እኛን እነዚህ የፍቅር እናቶች ናቸው ዘር ሳይለዩ ያሳደጉን። ወንበር ላይ የተቀመጡ ሰዎች በሰሩት ስህተት፣ ሌሎች መጎዳታቸው ተገቢ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ የለውጥ ጊዜ ስለሆነ፣ ሁሉንም ነገር ቆም ብሎ ማሰብ የግድ ይላል፡፡
– የወደፊት እቅድህ ምንድን ነው?
እኔ በጋዜጠኝነት ሙያዬ የተሻለ ነገር ለማድረግ ነው የምጥረው፡፡ አንድ ሰው ባዳበረው ሙያ ነው መጓዝ ያለበት፡፡ አንድን በባህር ውስጥ የለመደ ዓሳ፣ በሰማይ ብረር ብንለው አይሆንም፡፡ የኔም እንደዚያው ነው፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያዬ ቀጥዬ፣ አስተዋፅኦ ማበርከት እፈልጋለሁ፡፡
በተረፈ ከጎኔ የቆሙ የሰው ዘሮችን በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼን ከልቤ አመሰግናለሁ፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያንም እግዚአብሔር እንዲባርካት፣ እንዲጠብቃት፣ ያጣነውን መደማመጥ እንዲሰጠን እመኛለሁ፡፡