/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደማይቀበልና መንግስትን እንደሚከስ አስታወቀ
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) በቅርቡ የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀበት መንገድ ህጋዊነት የጎደለው በመሆኑ መንግስትን ሊከስ እየተዘጋጀ እንደሆነ አስታወቀ።ፓርቲው ዛሬ ባወጣው ባለ 4 ነጥብ የአቋም መግለጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥልና አዋጁንም እንዳይቀበል ጠይቋል።
በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታውጆ አርብ እለት በፓርላማ ጸደቀ የተባለው አዋጅ የቁጥር ስህተት እንዳለበትና የምክር ቤቱ አባላት ከወጡ በኋላ የተሰጠው ድምፅ ሁለት ሶስተኛ እንደማይሞላ በመረዳት ማስተካከያ የተደረገበት በመሆኑ ፓርቲው እንደማይቀበለው እንዲሁም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
የአለም ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ወደ ውስብስብና አሳሳቢ ችግር ውስጥ እየገባች ስለሆነ ከጎናቸው እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል።