“የዲሞክራሲ ጥማት የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ መድረሱን ተመልክቻለሁ” እስክንድር ነጋ

“የዲሞክራሲ ጥማት የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ መድረሱን ተመልክቻለሁ” እስክንድር ነጋ

ከስድስት ዓመት ተኩል የእስር ቆይታ በኋላ ባለፈው የካቲት የተፈታው ጋዜጠኛ እና የዲሞክራሲ አቀንቃኝ እስክንድር ነጋ፤ ቀጣዮቹን ሳምንታት በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመዘዋወርና በልዩ ልዩ የማህበረሰብ አካላት ጋር በመገናኘት አሳልፏል።

እስክንድር ህገ ወጥ ሰንደቅ ዓላማን መጠቀም እና ያለፈቃድ መሰብሰብ በሚሉ ምክንያቶች ዳግመኛ ከሌሎች የሙያ አጋሮቹ እና ፖለቲከኞች ጋር ለእስር የተዳረገው ከተለቀቀ ሁለት ወራት እንኳ ሳይደፍን ነበር።
አስራ ሁለት ቀናትን በዳግመኛ እስር አሳልፎ ከተፈታ በኋላም የተለያዩ የማህብረሰብ ክፍል አባላት መጎብኘቱን ቀጥሏል።

በስራ ላይ ባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ጉዞዎችን በማድርግበት ጊዜ የተለየ ጥንቃቄ እንዳደረግ ግድ ብሎኛል የሚለው እስክንድር፤ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ በተዘዋወረባቸው ስፍራዎች ሁሉ ከሰባት ዓመታት በፊት ከሚያውቀው በተለየ መልኩ የዲሞክራሲ ፍላጎት በሕዝብ ዘንድ ሰርፆ መመልከቱን ይገልፃል።

“ህዝቡ ተለውጧል፤ ለነፃነቱ ብሎ ግንባሩን ለጥይት ለመስጠት የቆረጠው ሕዝብ ቁጥር የበለጠ ጨምሯል” ሲል እስክንድር ከታሰረበት የዛሬ ሰባት ዓመት ግድም የነበረውን ሕዝባዊ ስሜት በቅርቡ ካስተዋለው ስሜት ጋር ያነፃፅራል።

“አሁን የዲሞክራሲ ፍላጎቱ ሕዝብዊ መልክ ይዟል፤ ምሁሩ አካባቢ ያለ ስሜት ብቻ መሆኑ ቀርቶ ታች ድረስ ወርዷል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢህአዴግ ራሱም ተለውጧል። በለውጥ ሂደት ውስጥ ነው ያለነው። ጥያቄው ይህ ሂደት በሰላማዊ መልኩ ይቀጥላል ወይንስ ወደብጥብጥ ያመራል የሚል ሲሆን ይህም በቀጥታ ገዥው ፓርቲ ከሚያደርገው ነገር ጋር የሚያያዝ ነው” ሲል እስክንድር ለቢቢሲ ገልጿል።

ዳግም እስር
በወርሃ የካቲት መጀመሪያ በርካታ የተቃውሞ ፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች እና የመብት ተሟጋቾች ከእስር ሲለቀቁ ከተፈችዎቹ መካከል አንዱ የነበረው እስክንድር ከሳምንታት ቆይታ በኋላ ዳግም መታሰሩ “በማንኛውም ሰዓት ልንታሰር እንደምንችል መልዕክት ለማስተላለፍ ተፈልጎ ነው” በማለት ይከራከራል።

“ከዚህ የተረዳነው ነገር በማናቸውም ደቂቃ ዳግም ልንታሰር እንደምንችል ነው። ነገ ላልኖር እችላለሁ። በሚቀጥለው ሳምንት ወይንም በሚቀጥለው ወር ላልኖር እችላለሁ። ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መግባት እስካልቻልን ድረስ ማለት ነው። ዲሞክራሲ እስከሌለ ድረስ የእኛ ነፃነት በጥያቄ ውስጥ ነው ያለው” ይላል እስክንድር።

“ይሄ ደግሞ ሊሆን የሚችለው፤ መንግሥት እንደፈለገ ማድረግ የሚችለው ዲሞክራሲ በሌለበት ድባብ ውስጥ ብቻ ነው። ከህግ ውጭ ነው የታሰርነው። ከማናቸውም ጊዜ በላይ አሁን ለዲሞክራሲ ያለኝ ጥማት ጨምሯል ጭራሽ።”
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
ጋዜጠኛ እስክንድር አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያደርጓቸውን ተስፋ ሰጪ ንግግሮች እንደሚያደንቅ፥ በበርካቶችም ዘንድ ጠንከር ያለ የጊዜ ይሰጣቸው አስተያየት መኖሩን ልብ እንዳለ ይናገራል።

“ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሩ [ይናገራሉ] ነገር ግን በተግባር ካልተገለፀ ዋጋ የለውም” የሚለው እስክንድር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከልባቸውም ለውጥ ቢፈልጉም እንኳ ያሉበት ፓርቲ ኢህአዴግ ለውጥ ይፈልጋል ወይ የሚለው ጥያቄ ገና እንዳልተመለሰ እንደሚያምን አይሸሽግም።

“የኢትዮጵያ ሕዝብ የታገለው ኢህአዴግ እንዲታደስ ወይንም በኢህአዴግ ውስጥ የአመራር ለውጥ እንዲመጣ ብቻ አይደለም። የአመራር ለውጡ ትርጉም የሚኖረው አገሪቱን ወደ ዲሞክራሲ ካስገባት ብቻ ነው” ብሏል ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ስኬት ሥራ ላይ በሚቆዩባቸው ቀዳሚ ወራት በሚያከናውኗቸው ተግባራት እንደሚመዘን የሚገልፀው እስክንድር ይህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማስነሳትን እና ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያሳትፍ ጉባዔ መጥራትን እንደሚያካትት ያስረሳል።

ማዕከላዊ
በበርካታ የመብት ተሟጋቾች እና የቀድሞ ታሳሪዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይከናወንበታል እየተባለ የሚብጠለጠለውና ማዕከላዊ ተብሎ በሰፊው የሚታወቀው የምርመራ ክፍል እንዲዘጋ መወሰኑ መንግስት ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመግባት ፍላጎት እንዳለው መገለጫ ተደርጎ የሚታይ ካልሆነ በስተቀር በራሱ የረባ ፋይዳ የለውም ባይ ነው ጋዜጠኛ እስክንድር።

“ማዕከላዊ ስለተዘጋ ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይቆማሉ ማለት አይደለም። ትልቁ ትርጉም እንደ ሀገር ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ገብተናል አልገባንም የሚለው ነው። የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚቆመው፥ ሙሉ በሙሉ የሚደርቀው ሃገራችን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ስትገባ ብቻ ነው።”

LEAVE A REPLY