የኤ.ኤን.ሲ. እንክርዳድ ትውልድ /ታሪኩ ደሳለኝ (ሚኪ)/

የኤ.ኤን.ሲ. እንክርዳድ ትውልድ /ታሪኩ ደሳለኝ (ሚኪ)/

በአዲስ አበባ “ኮሪያ ሠፈር ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወልዶ የጀግኖች አርበኞችን ታሪክ እየሰማ ያደገው ገዛህኝ (ነብሩ) የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በህብረት ፍሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በኮኮበ ጽብህ እንደተከታተለ ከአብሮ አደግ ጒደኞቹ ሰምቻለሁ።

በሰሜን ኢትዮጵያ ሀገር ለማፍረስና ለመገንጠል የሽምቅ ውጊያ የሚያደርጉትን ወንበዴዎች ለመደምሰስ የቀረበውን የእናት ሀገር ጥሪ ተቀብሎ (በ1978 ዓም) የኢትዮጵያን ጦር ከተቀላቀለ በኋላ ለአየር ወለድ ስልጠና ደብረዘይት ገብቶ ስልጠና ወስዷል። በተጨማሪም ሻሸመኔ በሚገኘው የኮማንዶ ማሰልጠኛ ወንዶ ጢቃ ተገቢውን የኮማንዶ ትምህርት ካገኘ በኋላም ኤርትራ የነበረውን ሁለተኛው አብዬታዊ ሠራዊት ተቀላቅሎ በናቅፋ ተራራዎች የቀይ ባሕርን ድንበርነት ለማስቀጠል መስዋዕትነትን ከፍሏል።

ባሳየውም ታላቅ ተጋድሎ ወታደራዊ ማአረግና የክብር ኒሻን ተሸለሚ እንደነበር የታሪክ ማህደሩ ያትታል። ወደ ወሎም በመዝመት ከወያኔ ተለጣፊው (ክሹፍ ኢህአፓ) ኢህዴን ጋር በተካሄደው ሀገር የመታደግ ዋጊያም ተሳትፎ የተቻለውን ያህል አድርጓል። ወደኋላ ላይም የአየር ወለድና የኮማንዶ አሰልጣኝ ሆኖ የኢትዮጵያን ሠራዊት አገልግሏል።

በአሰልጣኝነት ዘመኑም ደቡብ አፍሪካውያን ከአፖርታይድ የጭቆና አገዛዝ ለመላቀቅ የሚያደርጉትን ትግል የሚመራው የANC ወታደራዊ ክንፍ አባለቱን ለስልጠና ወደ ኢትዮጵያ በላከበት ወቅት ግዳጁን ተቀብለው በሚገባ ከተወጡት አሰልጣኞች መካከልም አንዱ ገዛሀኝ እንደ ነበረ ይታወሳል።

ከደርግ ውድቀት በኃላም በተለያዩ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ምክንያቶች በሀገሩ መኖር ስላልቻለ፣ ነፃ አውጪዎቿን በማሰልጠን ውላታ ወደ ዋለላት ደቡብ አፍሪካ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1991 ተሰድዷል።
በደቡብ አፍሪካም ምድርም የሀገሩን ጉዳይ በግንባር ቀደምትነት እየነሳ ስለኢትዮጵያ ሲቆረቆር የነበረ ብርቱ ታጋይ ነበር።

የገዛሀኝ ድምፅ ጆሀንስበርግ ካለው የኢትየጵያ ኢምባሲ ሺ እጥፍ ቀድሞ ኢትዮጵያ ላይ ይሰማ እንደነበር አንዘነጋም።
ዛሬ በጆሀንስበርግ ጉዳና ላይ በደቡብ አፍሪካ ቅጥረኛ ዜጋ ገዛሀኝ ነብሩ ሲገደል ውለታ የዋለላቸው ደቡብ አፍሪካውያን፣ በተለይም ገዥው ፓርቲ ANC የባለውለታቸውን እና የጀግናችንን ገዳይንም ሆነ ከአሰቃቂው ወንጀል ጀርባ ያለውን ስውር እጅ አድኖ በመያዝ ለፍርድ ያቀርቡ ዘንድ የሕግም የሞራልም ግዴታቸው ነውና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እናሳስባለን።

በዋናነትም በምድራቸው ላይ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን በተቃውሞ ሰልፍ ጭምር ጫና በማሳደር ትወተውቱ ዘንድ አደራ እላለሁ ። እስከዛው ግን በኤኤንሲው እንክርዳድ እና በቀጣሪዎች ጥርሳችንን እየነከስን እናዘግማለን።

ሚያዛያ 14/2010 ዓም

LEAVE A REPLY