/እንዲያነቡት እንመክራለን/ የቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎና የዛሬ የፍርድ ቤት ውሎ

/እንዲያነቡት እንመክራለን/ የቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎና የዛሬ የፍርድ ቤት ውሎ

/ጦማሪት ማህሌት ፋንታሁን/

የቂሊንጦ ቃጠሎን አቀነባብራችኋል፤ ለጠፋው ንብረት እና የሰው ህይወትም ተጠያቂ ናችሁ ተብለው የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው 38ቱ እስረኞች በምርመራ ወቅት የደረሰባቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለፍርድ ቤት በተደጋጋሚ አቤቱታ አቅርበው ፍርድ ቤቱም የማረሚያ ቤቱ ሃላፊዎች ምላሽ እንዲሰጡበት አዞ ነበር።

የማረሚያ ቤቱ ሃላፊዎችም እስረኞቹ ተከሳሾቹ ምንም አይነት የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳልደረሰባቸው ክደው አስረድተዋል። በመጨረሻም ጉዳዩን በገለልተኛ ወገን ይታይ በሚል ፍርድ ቤቱ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን (የመንግስት) በቂሊንጦ ቃጠሎ ተጠያቂ ናችሁ ተብለው የተከሰሱ 38 እስረኞች ላይ ሸዋሮቢት ለምርመራ በሄዱበት ወቅት የደረሰባቸውን ሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲያጣራ ባዘዘው መሰረት አጣርቶ ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን ፤ 16 ተከሳሾች ላይ ወደ ቂሊንጦ ሲገቡ ከነበረባቸው የአካል ጉዳት ውጪ የምርመራው ቡድን የተመለከተውን ጉዳት በዝርዝር አስቀምጧል።

👉ከበደ ጨመዳ― ቀኝ እጅ ላይ ትንሽ ጠባሳ ፤ ቀኝ እግር አውራ ጣት ስብራት
👉 ኢብራሂም ካሚል― ቀኝ እግር ላይ ጠባሳ ፣ ግራ እጅ ላይ ጠባሳ፣ የካቴና እስር ምልክቶች
👉 አግባው ሰጠኝ – ግራ ታፋ ላይ ሰፊ ጠባሳ፣ ቀኝ እግር ላይ ጠባሳ፣ ግራ እግር ላይ በሚስማር የተመታ ምልክት፣ ጀርባ ላይ የግርፋት የሚመስሉ ምልክቶች፣
👉 ቶፊቅ ሽኩር – ቀኝ እጅ ላይ ጠባሳ፣ የሁለት እግር አውራ ጣት ጥፍር መነሳት፣ ግራ እጅ ጠባሳ፣
👉 ሸምሱ ሰይድ – የጀርባ ግርፋት የሚመስሉ ምልክቶች፣
👉 ሚስባህ ከድር – የካቴና የእስር ምልክቶች፣ ቀኝ እጅ ላይ ሰፊ ጠባሳ፣ ግራ እጅ ላይ አነስተኛ ጠባሳ፣ ቀኝ እና ግራ ታፋ ላይ ጠባሳ፣ የግራ እጅ ጠቋሚ ጣት ስብራት፣
👉 ፍፁም ጌታቸው – የቀኝ እጅ ጉዳት፣
👉 ተመስገን ማርቆስ – የቀኝ እጅ ስብራት እና ጠባሳ፣ ሁለቱም እግሮች ሰፋፊ ጠባሳዎች፣
👉 አሸናፊ መለሰ – የቀኝ እና ግራ ታፋ ላይ ጠባሳዎች፣ የግራ እጅ የቀለበት ጣት ስብራት፣
👉 ካሳ መሐመድ – ቀኝ እጅ ጥልቅ ጠባሳ፣ ጭንቅላት ላይ የመፈንከት ምልክት፣
👉 ሲሳይ ባቱ – ቀኝ እጅ ላይ ጠባሳ እና የጠቆረ ምልክት፣
👉 አብዱልደፋር አስራት – ቀኝ እና ግራ እግር አውራ ጣት ጥፍር መነቀል፣
👉 ደረጄ መርጋ – ግራ እግር ላይ ስድስት ጠባሳዎች፣ ሁለቱም እግር ላይ የካቴና እስር የጠቆሩ ምልክቶች፣
👉 ቶፊቅ ፈርሀ – ግራ እጅ ላይ ጠባሳ፣ የካቴና እስር የጠቆሩ ምልክቶች፣
👉 ሰይፉ ግርማ – ከጀርባ ትከሻ በግራ በኩል ሚስማር የተመታ ጠባሳ፣ ሁለቱም እግሮች ላይ ጠባሳ፣

ኮሚሽኑ እነዚህን አስቀምጦ ሲጨርስ በምክረ ሃሳብነት ማረሚያ ቤቱ ለወደፊቱ እስረኞች የሚደርስባቸውን የመብት ጥሰት በመመዝገብ እና መርማሪዎቹ (ደብዳቢዎቹ) ማንነታቸውን የሚያሳይ ባጅ ማድረጋቸውን እንዲያረጋግጡ፤ እንዲሁም አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው እስረኞች የደረሰባቸውን የመብት ጥሰት መንስኤ እና ንብረታቸውን በተመለከተ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ክፍል እና የህክምና ባለሞያዎች አጣርቶ ለኮሚሽኑ እንዲያቀርብ የሚል ነው።

አስደናቂውን ምክረ ሃሳብ እንተወው እና ተከሳሾቹ በሪፖርቱ የቀረበው የመብት ጥሰት “አባይን በጭልፋ” ነው ብለውታል።

ቃጠሎው ከደረሰበት ከነሃሴ ወር 2008 ጀምሮ እስከ ታህሳስ ወር 2009 በዝዋይ እና በሸዋሮቢት ኢሰብአዊ ተግባር ተፈፅሞባቸው ከሞት ለመትረፍ በሚል ከሳሽ ወገን በሚፈልገው መልኩ የሰጡት ቃል እንደማስረጃ ተይዞባቸዋል። በተጨማሪ የአቃቤ ህግ ምስክር ሆነው የቀረቡት የማረሚያ ቤቱ ሃላፊዎች [የማረሚያ ቤቱን/ሃላፊዎችን ጥፋት ለማድበስበስ] እንዲሁም እስረኞች (አንዳንዶቹ እንፈታለን በሚል ተስፋ አንዳንዶቹ ደግሞ ለተከሳሾቹ ባላቸው ጥላቻ) ናቸው። እንግዲህ ይህ “ማስረጃ” ተመዝኖ ነው ለነገ ሚያዚያ 16/2010 ብይን ይነበባል ተብሎ (በነፃ ይሰናበቱ ወይም ይከላከሉ) የተቀጠሩት።

LEAVE A REPLY