አኖሌ ካልፈረሰ እያልህ ሀገር ይያዝልኝ የምትለው አማራ ግን ምን ነክቶህ ነው? ተው እረፍ ትጣላኛለህ!!! አከልገባህም እንዴ? አኖሌ እኮ የአንተ ሐውልት ነው።
ታሪክህ የማይመሰክረውን ባሕርይህ የማይፈቅደውን… ተረት ተረት ተጽፎ የቆመልህ የበቀል ሐውልት ይፍረስ ስትል ግን በጤናህ ነው? አኖሌማ አይፈርስም። በፍጹም አይፈርስም!!! አኖሌን ለማፍረስ የሚንቀሳቀስ አካል መጀመሪያ የሚጣላው ከእኔ ጋር ነው፡፡ ይህ በአንድ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር አንዲት ሀገርን ለመመሥረት የሚደክመው መንግሥት ያቆመው ‹‹የማስተሳሰሪያ›› ሐውልት ይፍረስ ማለት የለየለት ዕብደት ነው፡፡ እስኪ አንዳዴ ገልብጠህ ማሰብ ጀመርማ፡፡ ይህ እኮ ለአንተ ሀገራዊ ውለታ ሌላው እንዴት እንደሚመልስልህ ማሳያህ ነው፡፡
…
ቆይ መሠረታዊ ስጋትህ ምንድነው? ኦሮሞው ለበቀል ይነሳብኛል ከሆነ… በመጀመሪያ ታላቁን የኦሮሞ ሕዝብ በበቀል ስሌት ማሰቡን ተወው፡፡ ሲቀጥል… በቀል ታቦ ከሆነም… በቀሉን የምታስቀረው አኖሌን በማፍረስ አይደለም፡፡ ማንኛውንም የበቀልም ሆነ ሌላ ተጽዕኖ ለመመከት በሚያስችል ቁመና ላይ ስትገኝ ብቻ ሕልውናህ ተረጋጦ ትኖራለህ። በቀሉን የመመከት በራስ የመቆም ሕልውና ከሌለህ የይፍረስልኝ ሙሾህ ትርጉም የለውም። እናም አኖሌን ረስተህ ራስህን አስብ፡፡
አኖሌ የኦሮሞ ሕዝብ ጉዳይ ነው፡፡ ሐውልቱን ማፍረስም ሆነ ማደስ ያንተ ጉዳይ አይደለም፡፡ አሮሞው ‹‹ከወንድም ሕዝባችን ከአማራ ጋር ለሚኖረን የጋራ ጉዞና አንድነት…›› ብሎ የሐውልቱን መቆም ሳይቃወም አንተ ምን ቤት ነህ? ለፍቅር ሲል… ከአንተ ጋር ለመኖር ሲል… ለጋራ ሀገር ዘላቂ አንድነት ሲል ላፍርሰው ያላለውን አንተ ምነው አኖሌ አኖሌ አስባለህ? ካልፈለጉ ግድ ነው? አንወድህም ሲሉህ በግድ ውደዱኝ ነው? ‹‹የራሷ ሲያርባት የሰው ታማስላለች›› አሉ፡፡ መጀመሪያ በራስህ ክልል የቆሙ የክፍፍል ሐውልቶችን ነቅለህ ጣልና በአንድነት ቁም፡፡ በራስህ ሳትቆም… የመኖር ሕልውናህን ሳታረጋግጥ ስለቆመልህ ሐውልት ትጨነቃለህ እንዴ? ምን ነክቶህ ይሆን?
…
ማመን ያለብህ አንድና አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ማንም ለበቀል ይጭህ… አንተ በፍቅር ለመጋባት ብቻ ተዘጋጅ፡፡ ይቅር ባይ ልብ ያዝ፡፡ በበቀለኞች ልክ የሚያስብ ልብ አይኑርህ፡፡ ይህ ማለት ይቅር እያልህ ብቻ ተቀመጥ ማለት አይደለም፡፡ አትበቀል ማለት ጥፋ ማለት አይደለም፡፡ ሕልውናህን በራስህ ብቻ አረጋግጥ፡፡ አንተ ያላረጋገጥኸውን ሕልውና ማንም ሊያረጋግጥልህ አትጠብቅ፡፡ በራስ መተማመን እስከቆምህ ድረስ የሌላው አንተን መበቀልም ሆነ ማቀፍ አያሳስብህ፡፡ የሚያቅፍህን ትስመዋለህ፡፡ ሊበቀልህ እጁን የሚዘረጋን ደግሞ እጁን… ከተቻለ በፍቅርና በምክር ካተቻለም ‹‹ቆንጥጠህ›› ታሳርፈዋለህ፡፡ ከፍ ብለህ በፍቅርና በአንድነት ቁም፡፡ ፍቅንና አንድነትን ያለ ሁሉ አብሮህ ይጓዛል፡፡ ሌላው ሁሉ ጉዳይህ አይሁን፡፡ በግድ ስሙኝ ብለህ በመጮህ ጉልበትህን አትጨርስ፡፡ ጩኸትህ ወደራህ ይሁን፡፡ ወደ ውስጥህ….