/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የማረሚያ ቤት አስተዳደር ህገ መንግስታዊ ግዴታውን በተገቢው ሁኔታ መወጣት ባለመቻሉና ሰብዓዊ መብቶችን ከማክበር አንጻር ሰፊ ክፍተት በመኖሩ፤ ለውጥ መደረጉን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ለኢቲቪ ተናግረዋል።
በታራሚዎች ላይ ከሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘም የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተርና አራት ምክትል ዳይሬክተሮች ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል። አዳዲስ ተሿሚዎችም መተካታቸውን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጨምሮ አስታውቋል።
በዚህም መሰረት ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ለአምስት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ሹመት ሸጥተዋል።
- ጀማል አባሶ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር
- ረዳት ኮሚሽነር ያረጋል አደመ ምክትል ዋና ዳሬክተር የፋይናንስና የሰው ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ
- ኮማንደር ደስታ አስመላሽ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የተሃድሶ ልማት ዘርፍ ኃላፊ
- ኮማንደር ሙላት አለሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የጥበቃና የደህንነት ዘርፍ ኃላፊ
- ኮማንደር ወንድሙ ጫማ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የመሰረታዊ ፍላጎት ዘርፍ ኃላፊ ሆነው እንዲመሩ ከሰኔ 25 ፣2010 ጀምሮ ተሹመዋል፡፡
አዲስ የተሾሙት የፌድራል ማረሚያ ቤቶች ዋና ዳሬክተር አቶ ጀማል ከዚህ በፊት የአዳማ ከተማ ከንቲባ እንዲሁም የኦሮሚያ ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ በመሆን ማገልገላቸው ታውቋል።
አቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ እንዳሉት አዲስ የተመደቡት የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አመራሮች ዋና ትኩረቱ በዜጎች የሚነሱ ቅሬታዎችን መፍታትና በህገ መንግስቱ የሰፈሩትን የሰብአዊ መብቶችና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ህጎች ባከበረ መልኩ መፈፀም አለትበትም ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት ህግ የጣሱ የማረሚያ ቤት አካላት ማጣራት እየተረገባቸው መሆኑንና በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተገልጿል።
ከማዕከላዊ ጀምሮ በቃሊቲ፣ ቂሊንጦ፣ ሸዋ ሮቢትና በሌሎች የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ዜጎችን የፖለቲካ አመለካከታቸውና የመጡበትን ዘር ሳይቀር መሰረት በማድረግ ባለፉት በርካታ ዓመታት ከፍተኛ ሰቆቃ ሲደርስባቸው መቆየቱ ይታወቃል።