የኢንጂነር ስመኘው በቀለ አሟሟት (?) – /ዳዊት ከበደ ወየሳ/

የኢንጂነር ስመኘው በቀለ አሟሟት (?) – /ዳዊት ከበደ ወየሳ/

በኢትዮጵያ ውስጥ በባለስልጣናት ላይ የተደረጉትን የግድያ ሙከራዎች ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት፤ በመገናኛ ሚንስትሩ ዶ/ር አብዱል መጂድ ሁሴን እና በግብጹ ፕሬዘዳንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ የተደረጉት የግድያ ሙከራዎች የቅርብ ግዜ ትዝታዎቻችን ናቸው። ዶ/ር አብዱልመጂድ ያን ሁሉ የግድያ ሙለራ አልፈው፤ አምላክ በፈቀደ ግዜ አረፉ።

ሆስኒ ሙባረክ ላይ የግድያ ሙከራ ያደረጉት ሰዎች በማዕከላዊ እስር ቤት ውስጥ ለብዙ አመታት የታሰሩ ይመስለኛል። ምክንያቱም በፕሬስ ጉዳይ ማዕከላዊ ታስረን በነበረበት ወቅት፤ ምሽት ላይ ከርቀት የሚመጣ የሳል ድምጽ ይረብሸን ነበር። “ለመሆኑ እዚያ ማዶ የታሰሩት እነማናቸው?” ስንል፤ “በሆስኒ ሙባረክ ላይ የመግደል ሙከራ ያደረጉት ግብጻውያን…” ከሚል መልስ ውጪ እነማን እንደሆኑ ሳናውቃቸው፤ እኛም ከእስር ቤት ወጣን። ማዕከላዊም ግዜውን ጠብቆ ተዘጋ። አሁን የኢንጂነር ስመኘውን አሟሟት ስንመለከት፤ ወደ ኋላ ተመልሰን በጠራራ ጸሃይ የተገደሉት እነአሰፋ ማሩ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያንንም በማስታወስ ጭምር ነው።

አቶ አሰፋ ማሩ የስርአቱ ተቃዋሚ ስለሆኑ ብቻ፤ በጠራራ ጸሃይ ከገደሏቸው በኋላ ቦንብ ከጎናቸው አድርገው ፎቶ እና ቪዲዮ በማንሳት፤ ምሽቱን በቴሌቪዥን መስኮት… “ለሽብር ተግባር ሲንቀሳቀሱ ተገኝተው ተገደሉ” ብለውን ነበር። አሁን ያ ዘመን አልፏል። መግደል ቢቻልም፤ ይህንን ህዝብ “አይንህን ጨፍን ላሞኝህ” ማለት ግን አይቻልም። አቶ አሰፋ ማሩ በተቀበሩበት እለት ፕሮፌሰር መስፍን ንግግር ሲያደርጉ፤ “ሰውን በግፍ መግደል አንድ ቀን ይቆማል፤ ገዳዮችም ለፍርድ ይቀርባሉ። እንደ አቶ አሰፋ ማሩ አይነት ንጹሃኖችንም ሁሌም እናስታውሳቸዋለን።” ሲሉ ለቅሷችንን ትተን አጨብጭበናልና ቃላችንን ለመጠበቅ፤ ትላንት ያጨበጨበው እጃችን ዛሬ ንጹሃን እና ግፉአንን በማስታወስ ይዘክራቸዋል… መልካም ንባብ።

የኢንጂነር ስመኘው በቀለ አሟሟት (?)

(ዳዊት ከበደ ወየሳ)

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በጎንደር ክፍለ ሃገር፣ ልዩ ስሙ ማክሰኝት የተባለ ቦታ ነው፤ እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1957 ዓ.ም የተወለዱት። በ1989 ዓ.ም. አዲስ አበባ ክሚገኘው አምስት ኪሎ የምህንድስና ኮሌጅ፤ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ተመርቀዋል። ከዚያም በመብራት ሃይል የኮተቤ ኤሌክትሪክ ኮሌጅ ውስጥ መምህር ሆነው ሰርተዋል። ቀጥሎም በጊቤ ሁለቱም ግድቦች ላይ የምህንድስና አሻራቸውን አኑረዋል። ከ2003 ጀምሮ ደግሞ በህዳሴ ግድብ ዋና መሃንዲስና ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲሰሩ ቆይተው፤ ሃምሌ 19 ቀን ጠዋት ላይ መስቀል አደባባይ ላይ ሞተው ተገኝተዋል።

የአሟሟታቸውን ሁኔታ እንደተከታተልነው ከሆነ፤ ምናልባት ድርጊቱን የፈጸሙት ሰዎች… አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ባለው ለውጥ ቅር የተሰኙ፤ ወይም ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ጥቅም ያላቸው ወይም ጥቅም የቀረባቸው ሰዎች ወይም ቡድኖች ሊሆኑ እንደሚችሉ አንዳንድ ፍንጮች እያመላከቱ ነው።

ከዚህ ውጪ ግን በግልጸብ ምክንያት ኢንጂነሩን ለመግደል የሚጋበዝ ሰው ሊኖር እንደማይችል የቅርብ ጓደኞቹ ምስክሮች ናቸው። ለዚህ ደግሞ አንደኛውና ዋናው ምክንያት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በግል ባህሪው ከሰው ጋር የሚጋጭ እና በራሱ ላይ ጠላት የሚያፈራ ግለሰብ አይደለም።

ይልቁንም ከግድያው አንድ ቀን ቀደም ብሎ፤ ወደ ጉባ ለመሄድ እቅድ አድርገው እንደነበር፤ ይህንኑም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው በነበረበት ወቅት መናገራቸውን እናስታውሳለን። ጠዋት ከቤት ከመውጣታቸው በፊት ቡና ብቻ መጠጣት እንደሚፈልጉ፤ ለልጆቻቸው ሞግዚት ገልጸው ቁርስ ሳይበሉ ነበር የወጡት።

ጠዋት ላይ መኪናቸውን እያሽከረከሩ፤ መስቀል አደባባይ ሲደርሱ ግን ያልተጠበቀ ነገር ሆነ። በአካባቢው የተኩስ ድምጽ ተሰማ። በመስቀል አደባባይ ማለዳ ወጥተው ስፖርት የሚሰሩ ወጣቶች በሰሙት የተኩስ ድምጽ ተረብሸው፤ ለፖሊስ በመደወል ጉዳዩን አሳወቁ። ፖሊስ በስፍራው ሲደርስ ግን ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ወደ አንድ ጎን አዘንብለው… ሞተው አገኟቸው። ይህ ያልተጠበቀ ሞት በድንገት ሲሰማ፤ ከልጅ እስከአዋቂ ድረስ ተደናገጠ። ቤተሰብ እና የስራ ባልደረቦቻቸው፤ የኢትዮጵያ ሚንስትር መስሪያ ቤቶች እና ፕሬዘዳንቱ ጭምር በሁኔታው በማዘን የሃዘን መግለጫ ለቤተሰቦቻቸው ላኩ።

እለቱን አሜሪካ የገቡት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ፤ በተፈጠረው ድንገተኛ ሞት ምክንያት እጅግ ማዘናቸውን ከአሜሪካ አሳውቀዋል። ሌሎች በልዩ ልዩ አለማት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም የእለቱ መነጋገሪያቸው ሆኖ ነበር የቆየው – የኢንጂነሩ አሟሟት።   ብዙዎች በተፈጠረው ሁኔታ ያዘኑ እና የተበሳጩ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ “ህዝቡ በትዕግስት የአስከሬን ምርመራ እና የፖሊስን ፎረንሲክ  ውጤት መጠበቅ አለበት” ሲሉ መክረዋል።

ይህ እንዳለ ሆኖ እኛ ከውጭ ሆነን ስንመለከት የታዘብናቸውን ነገር በማንሳት የራሳችንን መላምት ብናቀርብ መልካም ይሆናል ብለን በማሰብ፤ አንዳንድ እውነታዎች ላይ እናስምርባቸው። ለምሳሌ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በተገኙበት ወቅት፤ በቀኝ በኩል ደግሞ ኮልት ሽጉጥ መገኘቱ ታውቋል። ከዚህ ተነስተን ሶስት ነገሮችን በትኩረት ማየት አለብን። በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ሽጉጥ የራሳቸው የኢንጂነር ስመኘው በቀለ መሆኑን ፖሊስ ማረጋገጥ አለበት። ሽጉጡ የራሳቸው ካልሆነ፤ ገዳዮቹ ድርጊቱን ከፈጸሙ በኋላ…  “ኢንጂነሩ ራሳቸውን ነው ያጠፉት” የሚል መላምት እንዲኖር ሆን ብለው ያደረጉት ሊሆን ይችላል።

በሁለተኛ ደረጃ… እንደተባለው ራሳቸውን ለማስጠፋት የሚያስችል ሁኔታ አለ ቢባል እንኳን፤ ሰው ራሱን ለማጥፋት መኪና አስነስቶ ሄዶ አደባባይ ላይ ድርጊቱን ይፈጽማል ብሎ ለማመን አስቸጋሪ ነው። በዚያ ላይ ኢንጂነር ስመኘው፤ “ከትላንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ ይሻላል።” ብሎ የሚያምን ሰው ነው። ከአንድ ቀን በፊት በኢቲቪ ቀርቦ መግለጫ ሰጥቷል። በንጋታው የሚወደውን የምህንድስና ስራ ለማከናወን ወደ ጉባ እንደሚሄድ ገልጿል። ጠዋት በሰላም ከቤቱ የወጣ ሰው ራሱን ይገድላል ለማለት በቂ የሆኑ ምክንያቶች አይኖሩም።

በዚያ ላይ… የኢንጂነር ስመኘውን አወዳደቅ ካየን፤ ወደ ቀኝ አዘንብለው ነው የወደቁት። ሽጉጡ ያለው በቀኝ እጃቸው ከሆነ እና ራሳቸው ላይ ከተኮሱ፤ ጥይቱ በቀኝ በኩል ገብቶ በግራ ሲወጣ ትልቅ ቀዳዳ ሰርቶ ነው መውጣት ያለበት። በግራ በኩል ግን ምንም አይነት የጎላ ጉዳት አላየንም። ስለዚህ “በቀኝ እጃቸው ራሳቸው ላይ ተኩሰዋል” የሚለው መላምት ውድቅ ይሆናል።

ይልቅስ “ሰው ገድሎት ነው” የሚለው ሶስተኛው መላምት አሳማኝ ይመስላል። በሰው መገደሉን ከተስማማን… አገዳደሉም ቢሆን በሰለጠኑ ወይም ልምድ ባላቸው ሰዎች የተከናወነ ነው የሚመስለው። በቀኝ በኩል የተገኘውም ሽጉጥ ራሱን ለመከላከል ሲል የያዘው – ሊሆን የሚችለው። ስለዚህ ገዳዮቹ ይከታተሉት ከነበረ ምናልባት ማለዳም ቢሆን ስፖርተኞች ወደማይጠፉበት መስቀል አደባባይ የሄደው፤ እርዳታ ወይም የአይን እማኞችን ለመግኘት ሊሆን ይችላል። ከዚያም ከፊቱ መኪና በማቆም፤ ቀጥሎም እሱም በማናገር እና በማደናገር ሙከራ ሲደረግ፤ የኋላውን መኪና መስታወት እንደሰበሩት ፍንጮች ያመለክታሉ።

በእርግጥም መኪናውን እንደተመለከትነው ከሆነ፤ የኋለኛ መቀመጫ ያለበት አንደኛው መስታወት በሃይል ተሰብሯል። ከዚያም በዚያ የመስኮት ቀዳዳ በመጠቀም፤ የመኪናውን የኋላ በር ለመክፈት እንደተቻለ – ጥሩ የሆነ መላ ምት ማስቀመጥ ይቻላል። ከዚያ በኋላ ሊፈጠር የሚችለውን ነገር መገመት ቀላል ነው። ግድያውን የፈጸሙት ሰዎች ባስቸኳይ ከአካባቢው ተሰውረዋል። ለፖሊስ የተደወለውም ይህ የተኩስ ድምጽ ከተሰማ በኋላ፤ ምናልባትም ገዳዮቹ ከተሰወሩ በኋላ ነው። ፖሊስ በስፍራው ሲደርስ… የመኪናው ሞተር ገና አልጠፋም፤ የኢንጂነሩ የግል ንብረቶች አልተነኩም። ድርጊቱን በጥልቀት ከመረመርነው…. ይህ ተራ የውንብድና ወይም የሌብነት ወንጀል እንዳልሆነ መገመት እንችላለን።  

በዚሁ ሶስተኛው መላምት ላይ እያለን … ሌላ አስገራሚ ነገር ደግሞ እናክልበት። መስቀል አደባባይ ላይ ፖሊስ፣ ጸረ ሽብር ሃይል እና ኢንሳ በጋራ የሚጠቀሙበት ካሜራ አለ። ይህ ካሜራ በአካባቢው ያለውን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ነው። ሆኖም በእለቱ የተከናወነውን ወንጀል አልቀረጸም። የዚህ ዋና ምክንያት ተብሎ ተገለጸ ሲባል የሰማነው፤ ካሜራዎቹ ምሽቱን ለድሳት ተብለው ስራ ማቋረጣቸውን ነው። ይህ ነገር አንዳች ነገር ሹክ ሊለን ይችላል። “እነዚህ ካሜራዎች እንዲነሱ ትዕዛዝ የሰጠው ማነው? በቂ ምክንያት አለው? ወይም ነገሩ የአጋጣሚ ግጥምጥሞሽ ነው?”

ፖሊስ ምርመራ ሲያደርግ ነገሮችን በተለያየ መልኩ ያያል። “ለምን?” የሚለው ጥያቄ ግን… ሁሌም ምላሽ ማግኘት ያለበት ጥያቄ ነው። እናም አዲስ አበባ ሳሚት ወደሚገኘው የኢንጂነር ስመኘው በቀለ መኖሪያ ቤት ለአንድ አፍታ እናምራ። ወደመኖሪያ ቤቱ ስንገባ፤ በሳሎኑ ውስጥ ከተሰቀለው ከኢንጂነሩ ፎቶግራፍ ቀጥሎ፤ በትልቁ የጥያቄ ምልክት (?) ብቻ ያለበት ስዕል ግድግዳው ላይ ይታያል። “ምን ማለት ይሆን?” ወደ ኢንጂነሩ መኝታ ክፍል ስንገባ አልጋቸው ተነጥፎ ሻንጣቸው ተቆልፎ፤ ለጉዞ መዘጋጀቱ ያስታውቃል። ስለዚህ ኢንጂነሩ ከቤት የወጡት በቀጥታ ወደ ጉባ ለመሄድ ሳይሆን፤ ምናልባት ከሰው ጋር ቀጠሮ ኖሯቸው ሊሆን ይችል ይሆናል። እንደዚያ ከሆነ ደግሞ “ምሽቱን ለማን ጋር በስልክ አውርተዋል? ቀጠሮስ ነበራቸው ወይ? ቀጠሮ ከነበራቸው ከማን ጋር? በማለዳ የወጡት ቀጠሮ ኖሯቸው ካልሆነ… ለምን በማለዳ ወጡ?” እነዚህ ሁሉ ነገሮች ምላሽ ማግኘት አለባቸው።

በዚያም ተባለ በዚህ… ግድያው የተፈጸመው በሌላ አካል ከሆነ ምርመራው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። የግድያው መነሻ ግን… በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው ሰላማዊ ለውጥ በማያስደስታቸው ሰዎች ከሆነ፤ ጉዳዩን እና ትግሉን ውስብስብ ያደርገዋል። እርግጥ ነው። የዶ/ር አብይ እና የደጋፊዎቻቸውን አካሄድ የማይደግፉ፤ ምናልባትም በተደራጀ መልኩ እርምጃ ለመውሰድ የተዘጋጁ ሃይሎች ይኖሩ ይሆናል። ግምታችን ትክክል ከሆነ… ደህንነት እና ፖሊስ የዚህ አይነት ድርጊት ፈጻሚዎችን ከምንጫቸው ማድረቅ አለበት። ፖሊስ ይህን ማድረግ ከተሳነው፤ በህዝብ ዘንድ እምነት ማጣት ብቻ ሳይሆን፤ ነገ እና ከነገ ወዲያ ግድያው በሌሎች የወቅቱ ባለስልጣናት ላይ ተመሳሳይ ተግባር ይፈጸም ይሆናል።

ነገሩ እንዲህ እንዲህ እያለ በዚሁ ከቀጠለ፤ ህዝብ በስጋት ሳይሆን፤ በኩራት የሚንቀሳቀስበት ከተማ እና አገር ከሌለን፤ እየተገኘ ያለው ሰላም ሊደፈርስ ይችላል። የዚህ ድርጊት ፈጻሚዎች ዋና አላማ ቂም በቀልነት ሊሆን ይችላል፤ ከዚሁ ጋር አያይዘው በዶ/ር አብይ አህመድ ምክንያት አገር እየታመሰ መሆኑን ለማሳየት ብለው ያደረጉት ሊሆን ይችላል።

ከምንም በላይ ግን መንግስት አጥብቆ ሊሰራበት የሚገባ ሌላ ጉዳይ አለ። አዲስ አበባ ከነዋሪዎቿ በተጨማሪ ከሌላ ክልልም ሆነ ከውጭ አገር በሚመጡ ሰዎች እየተጨናነቀች ናት። ‘ኢትዮጵያውያን ከሌላ ክልል ወደ አዲስ አበባ ለምን ይመጣሉ?’ የሚል ሙግት ማንሳት አንሻም። ነገር ግን ነዋሪው የሚለይበት አዲስ እና ዘመናዊ የመታወቂያ ካርድ ሊዘጋጅ ይገባል። ይህ ደግሞ ለአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ክልሎች የሚሰራ መሆን አለበት። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የሚሰጠው የነዋሪነት ካርድ፤ ዘመኑን የሚመጥን፣ ጥራቱን የጠበቀ ወይም ዲጂታል ባዮ ዳታ ያለው አይደለም። እዚያ ደረጃ ባንደርስም፤ ቢያንስ ከሌላ ክልል መጥተው ወንጀል ከፈጸሙ በኋላ አዲስ አበባን ለቀው በመሄድ የሚመሽጉ ሰዎችን ለመከላከል – የአዲስ አበባ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ሊያስብበት ይገባል።

እንዲህ ነው። አሸባሪዎች ሰውን የሚገድሉት ሌላውን በማሸበር ራሳቸውን ለማንገስ ሲሉ ነው። በመሆኑም በተሸበርንላቸው መጠን፤ የዚህ አይነቱን ግድያ አጠናክረውና ተጠናክረው ይቀጥሉበታል። ስለዚህ ለአሸባሪዎች መሸበር የለብንም። አንድ ሰው “ሞተ” የሚባለው በህይወት ዘመኑ ከግብ ለማድረስ ያሰበው አላማ ግቡን ሳይመታ ሲቀር ነው። ስለሆነም የኢንጂነር ስመኘው አላማ ግብ እንዳለው ለማሳየት በማልቀስ ሳይሆን፤ በመጠንከር ጠላትን ማሳፈር ያስፈልጋል።

ሆኖም ይህን ድርጊት ከአገር በቀል አሸባሪዎች ጋር ብቻ ማያያዝ ላይኖርብን ይችል ይሆናል። ምክንያቱም የአባይ ግድብ የሚያበሳጫቸው ግብጻውያን መኖራቸውን አልዘነጋንም። ሆኖም በዚህ ጉዳይ የሚያተርፉት ነገር ባለመኖሩ “የነሱ እጅ አለበት” የሚለውን መላምት እናልፈዋለን። ከዚያ በተጨማሪ ራሱ የህዳሴው ጉዳይ በተባለው ወቅት አለማለቁ አወዛጋቢ ነው። በተባለው ወቅት አለማለቁ ብቻ ሳይሆን፤ በአብዛኛው በህወሃት ሰዎች ይመራ የነበረው የሜቴክ ብረታብረት የስራ ተቋራጭ እየወሰደ፤ ያልሰራቸው ስራዎች ብዙ ናቸው። በዚህም ምክንያት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በሜቴክ ምክንያት ባክኗል። ለዚህ ብክነት ተጠያቂው ደግሞ ሜቴክ ድርጅት ነው።

አሁን በሜቴክ ላይ ጠንከር ያለ ምርመራ እየተካሄደ ይገኛል። ምናልባት እንዲወጣባቸው ያልፈለጉት ሚስጥር ካለ፤ አንደኛው አማራጭ የህዳሴ ግድቡን የበላይ ሃላፊ ማጥፋት እንደአማራጭ ተወስዶ ሊሆን ይችል ይሆናል። በዚያም ተባለ በዚህ ግን ኮሽ እና ጦሽ ባለ ቁጥር የምንበረግግ ከሆንን ለገዳዮቹም የልብ ልብ መስጠት ይሆናልና ጠንክረን እንጂ ደንግጠን መታየት የለብንም።

ይህን ያህል ካልን በኋላ… አንዳንድ ምክረ ሃሳቦች ሳንሰነዝር መለያየት የለብንም።

የኢንጂነር ስመኘው ወላጅ አባት

ያለጧሪ የቀሩትን የስመኘውን ወላጅ አባት የክልሉ ወይም የፌዴራል መንግስት “አለሁላቹህ” ሊላቸው ይገባል። የኢንጂነሩ ልጆች ለቁም ነገር እስከሚበቁ ድረስ፤ ህዝቡ ገንዘብ አሰባስቦ፣ መንግስትም የራሱን አክሎበት… እስከዩኒቨርስቲ ደረጃ የሚያግዛቸውን በቂ ገንዘብ ልናስቀምጥላቸው ይገባል። ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በተወለደበት ማክሰኝት ላይ፤ ወይም በተማረበት ወልድያ ውስጥ በስሙ ትምህርት ቤት እና ሆስፒታል መክፈት ሌላው ነገር ነው። ከዚህም በተጨማሪ… ስራውን እንጂ ስሙን ብዙም ለማንወደው “ህዳሴ ግድብ” ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ብዙ ደክሟል።

ኢንጂነር ስመኘው የለፋበት እና የደከመበትን ግድብ መጨረሻውን ለማየት ሳይበቃ ነው ህይወቱ ያለፈው። ግድቡ በስሙ ይሰየምለት ባንልም እንኳን፤ በዚህ ግድብ አማካኝነት የሚፈጠረው ሃይቅ ገና ስም አልተሰጠውም… ስለሆነም ይህንን ሃይቅ – “ስመኘው ሃይቅ” ብንለው ወይም በስሙ ቢሰየምለት… ገዳይ እና አስገዳዮች ቅስማቸው እንዲሰበር ይረዳናል። ስለዚህ የገደሉን ሲመስላቸው… ስጋችን እንጂ ስራችን አለመሞቱን ልናረጋግጥላቸው ይገባል።

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ባለትዳር እና የሶስት ልጆች አባት ነበሩ። ባለቤታቸው ለትምህርት ውጭ አገር ሲሆኑ፤ ለቀብር ስነ ስርአታቸው በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው። በመሆኑም ነገ በቅድስተ ስላሴ ሊደረግ የነበረው የቀብር ስነ-ስርአት እስከሚቀጥለው ሳምንት ተላልፏል።

…እስከዚያው የአስከሬን እና የፎረንሲክ ውጤቱን እንሰማለን።

LEAVE A REPLY