/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ታራሚዎች ከፍተኛ የሠብአዊ መብት ጥሠቶች እንደሚፈፀምባቸው ለቴሌቪዥን ጋዜጠኞች በምሬት መግለፃቸውን ተከትሎ ሰሞኑን የቃሊቲ፣ ቂሊንጦ፣ ሸዋ ሮቢትና ድሬዳዋ ማረሚያ ቤቶች አስተዳዳሪዎች ከሃላፊነታቸው መነሳታቸው ታውቋል፡፡
የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አዲሱ ጴጥሮስ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ የከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት (ቃሊቲ) ዳይሬክተር ገብረኢየሱስ ገብረ እግዚአብሄር፣ የቀጠሮ ማረሚያ ቤት (ቂሊንጦ) አስተዳደር ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አሰፋ ኪዳኔ፣ የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ሃላፊ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት የማነ አስፋው እንዲሁም የድሬድዋ ማረሚያ ቤት ዳይሬክተር መኮንን ደለሣ ከስልጣን ተነስተው በአዳዲስ አመራሮች መተካታቸውን አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘግቧል።
በማረሚያ ቤቶቹ የሚገኙ ታራሚዎች ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እየተፈፀመባቸው መሆኑን ለደብደባ፣ ለእንግልትና ለአካል መጉደል መዳረጋቸውንም በተከታታይ ለቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ሲገልፁ መሰንበታቸው ይታወቃል፡፡
በሌላ በኩል የምህረት አዋጅ ዝርዝር አፈፃፀም ይፋ መደረጉን ተከትሎ “ለምን እኛን አያካትትም” የሚል ጥያቄ ያላቸው ታራሚዎች፤ በተለያዩ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ተቃውሞ ሲያሰሙ የሰነበቱ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ጀምሮ መረጋጋት መፈጠሩን አቶ አዲሱ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
ተቃውሞ ከተቀሰቀሰባቸው የፌደራል ማረሚያ ቤቶች መካከል ቂሊንጦ፣ ቃሊቲና እና ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ከታራሚዎች ጋር ውይይት በማድረግ ችግሩ መፈታቱን የጠቆሙት አቶ አዲሱ፤ ማረሚያ ቤቶቹ ወደነበሩበት ሁኔታ ተመልሠው ከሃሙስ ጀምሮ ቤተሠብም ታራሚዎችን መጠየቅ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ተመሳሳይ ተቃውሞ በክልል አስተዳደሮች ስር በሚገኙ የመቐለ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ደብረማርቆስና ወልዲያ ማረሚያ ቤቶችም ተቀስቅሶ የነበረ ሲሆን ማረሚያ ቤቶቹ ላይም የእሣት ቃጠሎ ተከስቶ የሠው ህይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙ ተጠቁሟል፡፡
በመቐሌና በፍኖተ ሠላም ማረሚያ ቤቶች ከተከሠተው ቃጠሎ ጋር በተገናኘ ሁለት ታራሚዎች መሞታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሣሁን ጎፌ ሰሞኑን በሠጡት መግለጫ፤ ታራሚዎች በዚህ መልኩ የሚያቀርቡት ከእስር የመፈታ ጥያቄ በህግ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል፡፡