በአማራ ክልል በጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክት ውስጥ በትግራይ ተወላጆች ላይ የተፈፀመው ጥቃት የዜጎች ሕገ መንግስታዊ መብትና ነፃነት የሚፃረር ተግባር በመሆኑ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በፅኑ ያወግዛል፡፡
ሓሳብን በሰላማዊ እና በሰከነ አኳኋን መግለፅና ልዩነቶች ካሉም ልዩነቶቹን መያዝና መግለጽ በሚቻልበት ሀገር ውስጥ ማንነትን መሰት አድርጎ የሚፈፀም ማናኛውም ዓይነት ጥቃት በየትኛውም ዓይነት መለኪያ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው፡፡
በአማራ ክልል በጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክት ውስጥ በትግራይ ተወላጆች ህይወትና ንብረት ላይ በተፈፀመው ጥቃት በእስካሁኑ ሶስት የትግራይ ተወላጆች መሞታቸውን ተረጋግጧል፡፡ የትግራይ ህዝብ እና የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በእነዚህ ሶስተ ሰዎች ሞት በጥልቅ ማዘናቸውን እየገለፁ የጉዳቱ ሰለባ ለሆኑ ቤተሰቦችና ወዳጆችም መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡
የትግራይ ህዝብ እና የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ማንነት ላይ ያተኮረ ማንኛውም ዓይነት ጥቃት በፅናት እያወገዙ፣ በፅናት እንደሚታገሉትም ለመግለፅ ይወዳሉ፡፡ የፌዴራል መንግስት እና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም በድርጊቱ የተሳተፉ አካላት ወደ ሕግ በማቅረብ በጥፋተኞቹ ላይ አስተማሪ የሆነ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ደግሞ ሁኔታውን በዝርዝር የሚያጣራ ኮሚቴ በማቋቋም በቅርብ አንድ ቡድን ወደቦታው በመላክ ዝርዝር መረጃውን በማጣራት ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ በዚህ አጋጣሚ ይገለፃል፡፡
የትግራይ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
ሐምለ 23 ቀን 2010ዓ.ም
መቐለ