በመደመር ዘመን የመቀነስ ፖለቲካ – 2 – /ጋዜጠኛ አስማማው ሀ/ጊዮርጊስ/

በመደመር ዘመን የመቀነስ ፖለቲካ – 2 – /ጋዜጠኛ አስማማው ሀ/ጊዮርጊስ/

በተመሳሳይ ርዕስ በክፍል አንድ ባቀርብኩት ፁሁፍ በተለይ ለወትሮው ቀንደኛ የአገዛዙ ደጋፊ የነበሩ ሰዎች በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ ሚሊዮኖችን ተስፋ እንዲያሳድሩ ያደረገውን ለውጥ ተከትሎ በፅኑ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ አጥበቀው እየተቃወሙ መሆናቸውን፡፡

እንዲሁም የዶ/ር ዐብይ ወደ ሥልጣን የመጡበትን ሂደት ከስስ መፈንቅለ መንግስት (Soft coup) እስከ ቀለም አብዮት ድረስ በአገሪቱ በመካሄዱ መሆኑን የትህነግ ደጋፊዎች በይፋ ከትግራይ ቲቪ እስከ አይጋ ፎረም ማወጃቸውን፡፡ በዚህም እንደ መፍትሄ ከ‘ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት (መፈንቅለ መንግስት ማድረግን) ጨምሮ ሶማሌ እና አፍርን ይዞ እስከመገንጠል’ የሚደርስን መፍትሄ መሞከር ይገባል የሚል የመቀነስ ሐሳብን እያንፀባረቁ ስለመሆኑ የተለያዩ የትህነግ ደጋፊ ሚዲያዎችን እና አራማጆችን ሐሳብ በማጣቀስ ሊመጣ ያለውን ሥጋት መጠቆሜ ይታወሳል፡፡ በዚህ የመቋጫ ፁሁፌ ቀጣይ ወሳኝ የሆኑትን ነጥቦች በአጭሩ ለመመልከት ወድጄያለሁ፡፡ በቅድሚያ ግን የዚሁ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ፈጣን ውጤት የሆነውን የማህበራዊ ሚዲያ የአሰላለፉ ለውጡን የተመለከተ አጭር ነገር ላንሳ፡፡

የማህበራዊ ሚዲያ አዲሱ አሰላለፍ – ከኮ.ካ እስከ ተ.ካ

የአንድ ለውጥ መገለጫ የሆኑ ብዙ አዎንታዊ ሆነ አሉታዊ ነገሮች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ የአዲሱ ጠ/ሚኒስትር የመጀመሪያ የፓርላማ ንግግርን ተከትሎ በተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች ለብዙዎች ሕልም የሚመስሉ ነገሮች በተግባር ላይ ውለዋል፡፡ በግፍ የታሰሩ ወገኖች ከመፈታታቸው አንስቶ ተገፍተው ትግል የጀመሩ እና አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ የፖለቲካ ቡድኖች ፍረጃው ከመነሳቱ በተጨማሪ ለሠላማዊ ትግል መጋበዛቸው፡፡ ሥልጣን እንደ ግል ርስት ለአመታት ተቆናጠው የነበሩ የደህንነት እና ሌሎችም ሰዎች መነሳታቸው፣ የኢትዮ-ኤርትራ የ20 ዓመታት ቁርሾ መፍትሄ ለማግኘት አዲስ ምዕራፍ በመጀመሩ እና በሌሎችም በርካታ ማሻሻያዎች የተነሳ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ አዲስ አሰላለፍ ብቅ ብሏል፡፡ ለወትሮው ከሞላ ጎደል በፖለቲካ ጉዳይ ዝምተኛው ወገን እንዳለ ሆኖ የትህነግ /ኢህአዴግ መሩ አገዛዝ ቀንደኛ ደጋፊ በአጭሩ ኮ.ካ (ኮተታም ካድሬ) እና ሌላው በአገሪቱ ላይ በሚፈፀሙ በደሎች ምሬቱን የሚያሰማው ወገን ሁሌም እንደማኛውም ተቃራኒ ወገን የቃላት ጦርነት ማከናወናቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ የእርቅ እና የፍቅር ጉዞን መሰረት ያደረገውን ማሻሻያውን ተከትሎ አዲስ አሰላለፍ ብቅ ብሏል፡፡ የዚህ አዲሱ አሰላለፍ መጠሪያ ተስፈኛ ካድሬ (ተ.ካ) ሲሆን ከኮ.ካ የሚለየውም የተለያዩ ነገሮች አሉ፡፡ ቀዳሚው ኮ.ካ (ኮተታም ካድሬ) የሚባሉት ብዙም ራሳቸውን የአገዛዙ ደጋፊ እንደሆኑ ለመግለፅ ይቸገራሉ፡፡ ይልቁንም መሐል ላይ ያለ ሰው ለመምሰል ይሞክራሉ፡፡ አንዳንዶቹ ተከፋይ ጦማሪ (paid blogger) መሆናቸውም በተለያዩ አጋጣሚ መጋለጣቸው ይታወቃል፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ተስፈኛ ካድሬዎች ግን በኩራት ብዙዎቹ ራሳቸውን ተስፈኛ ካድሬ ብለው ለመግለፅ የማያፍሩ ሲሆን የማሻሻያውን ለውጥ ከመደገፍ ውጪ ማንም ምንም እንደማይቸራቸው፤ በተለይም ከኮተታም ካድሬዎች በተለየ ይለየናል ስለሚሉት ነገር ሲያወሱ “ተ.ካ ለጥቅም ተመልምሎ የተገዛ እና ራሱን መጠቀሚያ ቁስ ለማድረግ የሚፈቅድ አይደለም፡፡ የሚመራውም በመርህ ብቻ ነው ባይ ናቸው፡፡” ከዚሁ ጋ ተያይዞ ማዲ መንገሻ የተባለ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ተ.ካ (ተስፈኛ ካድሬ) ከኮ.ካ (ኮተታም ካድሬ) በተቃራኒው ከኢህአዴግ ውጪ መንገድ የለም የሚል ኮ.ካዊ አመለካከት የለውም፣ ተ.ካ ብዙ ቃል የገቡትን ጠ/ሚ ዐብይን ሲደግፍ ቃላቸውን ካልጠበቁ እና የተለመደ ኢህአዲጋዊ ባህሪ ካሳዩ እንደ ሃማደ ሊቆጥራቸው ምንም አያግደውም…” በማለት በተ.ካ ዙሪያ ያለውን አቋም ግልፅ አድርጓል፡፡

የአዲሱን አሰላለፍ ላስተዋለ አንዳንድ በተለየ ተጠቃሚ የነበሩትን ኮተታም ካድሬዎች ልክ ከሌላው እኩል ያደረገ መሆኑን መረዳቱ አይከብድም፡፡ ያም ሆነ ይህ አዲሱ አሰላለፍ የራሱን ገፅታ ይዞ እስከመቼ እንደሚቆይ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ ለጊዜው ግን የፖለቲካው ትኩሳት ግለት መለወጥን ተከትሎ የድር ዜጎች (netcitizen) አዳዲስ ቃላት ይወክሉዋቸዋል ለሚሉት ወገኖች መስጠታቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ ተደርጎ የሚወሳውም ዛሬም ድረስ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በጥርጣሬ ለሚመለከቱ ወይም ለሚቃወሙ ወገኖች የተቸራቸው ቋ.ተ (ቋሚ ተቃዋሚ) የተሰኘው ስያሜ ነው፡፡ የማህበራዊ ሚዲያ አዲሱን አሰላለፍ በመጠኑ ማውሳቱን የመረጥኩት ለቀጣዩ ነጥብ እንደ ዋንኛ ማሳያ ስለሚጠቅም በመሆነ ወደዛው እንዝለቅ፡፡

ለውጡን የመፈረጅ – የሴራ መላምት (conspiracy theory) ጋጋታ

የተቻላቸው ሁሉ አድርገው በጭራሽ የማይፈልጉት የዶ/ር ዐብይ ወደ መንበረ ሥልጣኑ መምጣቱን ተከትሎ ለቁጥር የሚታክቱ የሴራ መላምቶች ከትህነግ ደጋፊዎች በስፋት እየተሰነዘረ ነው፡፡ በተለይ ቀደም ሲል እንደተገለፀው የአገዛዙ ደጋፊ የሆኑ ቀንደኛ የኮ.ካ አባላት በተለየ የሚያገኙት መረጃ እንደ ልብ በመሆኑ ከአገሪቱ የመንግስት ሚዲያ ተቋማት እንኳ የበለጠ ልዩ መብት (priviliged) እንደነበሩ ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ነገር ግን ማሻሻያውም ተከትሎ ከሌላው ዜጋ የተለየ ምንም ልዩ መብት እንደሌላቸው በመደረጉ ከማህበራዊ ሚዲያው ይቅር እና ከአይጋ ፎረም እስከ ትግራይ ኦንላየን ለሰሚ እጅግ አስገራሚ የሆኑን የሴራ መላምት (conspiracy theory) ጋጋታ ማዝነቡን ቀጥለውበታል፡፡ ለዚህ እንደ አይነተኛ ማሳያ የሚሆነውም ከ ጋሽ አበራ ሞላ እስከ ገጣሚ ሜሮን ጌትነት፤ ከኮሜዲያን ክብበው ገዳ እስከ የግጥም በጃዝ ምሽቶች ሳይቀሩ በቀለም አብዮት አራማጅነት በአይጋው ፎረም ፀሐፊ መፈረጃቸው ነው፡፡

‹‹የቀለም አብዮት መደመር ህዝበኝነት›› ሚለው በሰላምወርቅ ሁሉአገር የቀረበው የፍረጃ ፕሮፓጋንዳ የመደመር ጉዞ (ለውጡ) በብዙ የቀለም አብዮት ሠራዊት ተሳትፎ በረዥም ጊዜ ጥናት በተለይም በCIA የተቀነባበረ አብዮት ስለመሆኑ በስፋት ያትት እና ‹‹ወደድነውም ጠላነውም ማወቅ ያለብን እውነታ ጋሼ አበራ ሞላ ገና ከመጀመርያው አዲስ አበባ አፀዳለሁ ብሎ ከውጭ መጥቶ ወጣቶችን እየሰበሰበ ፅዳት ሰርተዋል ብሎ ብር መክፈል ሲዘጅምር መጥረግያ ብቻ ይዞ አልመጣም። በአንዳንድ አገሮች ኮሜድያን የቀለም አብዮቱ መሳርያ አድርግው ሲጠቀምባቸው እናያለን።…በኛም አገር አብዛኛዎቹ የሞያ ሰዎች ሲሆኑ እንደ ክበበው ገዳና መስከረም የተባሉ በግላጭ ዋናውን የአብዮቱ ኮር ሃሳብ በማስረፅ የራሳቸው ሚና ነበራቸው። ሌሎቹ አሜሪካ ደርሰው ክትባቱ ወስደው ከተመለሱ በኃላ ጨዋታ የጨመሩ ሶስት ኮሜድያንም ብዙዎቻችን የታዘብናቸው ይመስለኛል።…›› በማለት ፍረጃውን በመቀጠልም ከአርቱ ሳንወጣ ፊልሞች፣ግጥሞች፣መነባንቦችና በጥቂቱም ቢሆን የስእል ስራዎች የቀለም አብዮት ማስፈፀምያ መሳርያ ሆነው ሌላ አለም አይተናል እኛም አገር እንዲሁ። ለዚህም በቅርብ አመታት በርካታ የዚህ ቅኝት ያላቸው ፊልሞች አይተናል፣ቁጥሩና አድማጭ ተሳታፊ እያበዛ የመጣው የግጥም ምሽትና የግጥም በጃዝ ወዘተ መድረኮች መብዛት ሁላችንም ታዝበናል። ብዙም የማይደፈሩ የፖለቲካ ቅኝት ያለው ነገር ሲነግሩን ስቀናል አጨብጭበናልም። ከአመታት በፊት ሜሮን ጌትነት አሜሪካ ደርሳ የተመለሰች ግዜ በአንድ የግጥም መድረክ ያቀረበችው ግጥም አስታወሳቹ?…” በማለትም አገሪቱን የኪነጥበብ ሥዎች በሙሉ ለቀለም አብዮቱ መዋላቸውን ያወሳል፡፡ ክሱ ግን በዚህ የሚበቃ አልሆነም፡፡ በተለይ ፈረንጆቹ grand fallacy (ታላቁ ህፀፅ) እንደ የሚሉት አይነት ፍረጃው ጭራሽ ወርዶ ወርዶ የመንግስት ሚዲያው ሆነ በፓርቲው ንብረትነት የሚታወቁት ሚዲያዎች ሳይቀር የቀለም አብዮት አራማጅ ስለመሆናቸው እንዲህ በማለት ይተረተራል፡፡ ‹‹እነ ዶክተር ዐብይ ወደ ስልጣን ያመጣ የአዲሱ አብዮት ሚድያ ለረጅም ግዜ ታስቦበት በስፋት የተሰራበት ነው። … ይህ ሲባል የመንግስት ሚድያው ጨምሮ በአገር ውስጥ ያሉ ሚድያዎችም ለዚህ ለቀለም አብዮቱ ጉዞ መሳለጥ የበኩላቸው በመወጣት ረገድ ብዙም እንዳልሰነፉ ከዚህ በፊት በነበሩ ፅሁፎቼ የገለፅኩት ስለሆነ ለዛሬ ብዙ አልልም። … ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለኔ በሚዛናዊነትና በአገር ግንባታ ተወዳዳሪ ያጣ ሚድያ የነበረ ሲሆን የአብዮቱ ግዜ እየደረሰ ሲሄድ … ለኔና ለአንዳንድ የተቋሙ ጋዜጠኞችም ጭምር በሚገርም ሁኔታ ልክ እንደ መሪ ቃሉ በደቂቃዎች ፍጥነት የዚህ አብዮት ማከናወኛ መሳርያ ሆኖ እየቀጠለ የሚገኝ መሆኑ ነው። ሌሎች ከመንግስት ሚድያ እየለቀቁ ለዚህ መሳርያ የመሆን ነገርም በተግባር እያየነው የከረምን ይመስለኛል። እዚህ ላይ ሳልጠቅሰው የማላልፈው የአለምነህ ዋሴ ጉዳይ ነው። ከሚሰራበት ተቋም የለቀቀበትና ወደ ውጭ አገር ወጥቶ ግልፅ የሚባል የቀለም አብዮት የማራመድ ስራ ሲሰራ ሳይ ከረጅም ግዜ ጀምሮ በራሱ የግዜ ሰሌዳ ይንቀሳቀስ የነበረ መሆኑ ነው የገባኝ።›› በማለት በቀለም አብዮቱ ያልተሳተፈ ሚዲያ እንደሌለ ያትታል፡፡ የዚህ አይነቱ ፍረጃ በተለይ ከቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አንስቶ እስከ ተራው ካድሬ ሳይቀር ተቃዋሚዎችን ለማሸማቀቅ ሲጠቀሙበት የቆየ ነው፡፡ ይኸኛውን ግን የተለየ የሚያደርገው የአገሪቱን ጠ/ሚኒስተር ራሳቸው የቀለም አብዮት ያመጣቸው አድርጎ መፈረጁ ነው፡፡ ይህ አይነቱ የጅምላ ፍረጃ (hasty generalization) ከምንም በላይ የትህነግ ደጋፊዎች ያሉበትን የቀቢፀ ተስፋ ከማሳየት የዘለለ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ነገር ግን የቆሰለ አውሬ የሚያደርገውን አይነት ያልተጠበቀ እርምጃ ቢወሰድ ሊከተል የሚችለውን ቀውስ በመገንዘብ በመንግስት በኩል ተገቢውን ማብራሪያ ከትህነግ አሊያም ከዚህ ሐሳብ በስተጀርባ ያሉትን ሰዎች መጠየቁ ተገቢ ነው፡፡ ይህን የምለው የተጀመረውን የይቅርታ እና የመደመር ዘመን ለውጥ ሙሉ በሙሉ የቀለም አብዮት ተደርጎ መቅረቡ በሂደት ለለውጡ ምንም አይነት ፍላጎት ሆነ አዎንታዊ አመለካከት የሌላቸው (hardliners) ሊወስዱት ላሰቡት እርምጃ ይህንኑ ውንጀላ እንደ ሁነኛ ምክንያት ሊጠቀሙበት የሚችሉበት ዕድል በመኖሩ ነው፡፡

ከዚሁ ጋ በተያያዘ የቀድሞው የኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደህንነት ዋና ኃላፊ ሜ/ጀነራል ተ/ብርሃን ወ/አረጋይ ከድምፂ ወያኔ ራዲዮ ጋ በነበራቸው ሰፋ ቃለ መጠየቅ በሀገሪቱ በታየው ለውጥ ደስተኛ አለመሆናቸውን በይፋ ከመግለፃቸው በላይ “በስልጣን ላይ የወጣው ሃይል ከኢህአዴግ ፕሮግራም ጋር የሚገናኝ ትንሽ የኢህአዴግ ሽታ እንኩዋን የለውም። ለእኔ ይህ የጠላት ሃይል ነው። እንደጠላት ሃይል እንውሰደው።” ማለታቸውን ማስታወሱ ይገባል፡፡ በተመሳሳይ ‹‹የጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ ንጉስ የመሆን ፍላጎት ከልብ ነው እንዴ?›› በሚል ርዕስ ከፍትህ ይንገስ በአይጋ ፎረም የቀረበው ሌላኛው መጣጥፉ ደግሞ ‹‹ከድርጂታቸው ይልቅ የራሳቸውን ስብዕና (Personality Cult) ገንብተው እርሳቸው እንዳሉት በረጂም ጊዜ ንጉስ ለመሆን የዳዱ ይመስላል። ህዝቡም በጉዳዩ ላይ የመደናገር ስሜት ዉስጥ ያለ ይመስላል። ›› በማለት ለሕዝቡ ተቆርቋሪ በመምሰል የቀረበው ፕሮፓጋንዳ ይቀጥል እና ‹‹የጠቅላይ ሚንስትሩን ንጉስ የመሆን ህልም የሚያሳየው ቁምነገር ደግሞ ለመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ሹመት የሰጡበት ሁኔታ ነው። እኝህ ሰው ልክ እንደንጉሳዉያን አገዛዞች ሁሉ ስልጣናቸውን ያለስጋት ለማስጠበቅና ለማስቀጠል በማሰብ ይመስላል ዋነኛ ተቋማት ናቸው ተብለው በሚገመቱ ቁልፍ ቁልፍ የአመራር ቦታዎች ለርሳቸው ቅርብ ናቸው ብለው የሚገምቷቸውን የኦህዴድ የስራ ሃላፊዎች መድበዋል። ›› በማለትም የለውጥ አራማጁ ፍላጎት በሂደት ንጉስ መሆን ነው የሚልን መከራከሪያ አቅርቧል፡፡

በትግራይ ኦን ላየን የሶስተኛ ዲግሪ እንዳላቸው (phd) በተነገረላቸው ሞገስ አብርሃም “Neoliberal Imperialism Creating a Fragile Ethiopian State” በሚል ርዕስ በቀረበ ተከታታይ ፅሁፍ በኒዮሊበራሎች ኢምፕራሊዝም እና በኢሳያስ አፈወርቄ መሳሪያነት ኢትዮጵያ ደካማ እና ወደ መፈራረስ የተቃረበች አገር እንድትሆን በደመቁ፣ ገዱ እና ጎዶቻቸው እየተሰራ መሆኑን በስፋት በማተት መለስ የቀየስው የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግስት በማንኛውም የውጭ ሆነ የአገር ውስጥ ሃይል ሊቀለበስ እንደማይችል ይዝታል፡፡

ኢትዮጵያ በመበተን ኣፋፍ ላይ? በሚል ርዕስ ገብረ ሥላሴ ኣርኣያ በአይ ፎረም ላይ “ኢትዮጵያን ካልበተናት ለኤርትራ ህልውናም ሆነ ዘላቂ ሰላም ትልቅ ፈተና ሆና ትቀጥላለች” የሚለውን የኢሳያስ ኣፈወርቂ መንግስት ህልም እየተሳካ ይመስላል። ያውም ኢትዮጵያውያንን ተጠቅሞ።›› በማለት የጠ/ሚንስትሩን የሠላም የማምጣት ሐሳብ ኢትዮጵያን ለመበታተን የተወጠነ በማስመሰል ውድቅ አድርገዋል፡፡

የመቀነስ ፖለቲካ – የተንሸዋረሩ የመፍትሔ ሐሳቦች

አይጋ ፎረም በበኩሉ አዲሱ አመራር ‹‹የኦህዴድ ዝቅጠት የወለደው ኣዲሱ ሃይል ቄሮ ኣደራጅቶ ወደ ኣመፅ በማስገባት ስልጣን የኦሮሞ ተወላጅ እስካልያዘ ደረስ ሰላም በዚህ ኣገር ኣይኖርም ብሎ በኣመፅና በተጠላለፈ ኔትዎርክ ወደ ስልጣን የመጣ ሃይል ነው።›› በማለት ‹‹መደመር ለሃገራዊ መግባባት መተካት ኣይችልም›› በሚል ርዕስ በኣባዲ ኣባይ ባቀረበው ፅሁፍ ‹‹ ኣሁን የወጣቱ መንፈስ የቀለም ኣብዮት በሚመስሉ መፎክሮች እያንቀሳቀሰ ያለው ሃይል 1997 ዓ/ም ቅንጅት የሚባለው ሃይል ፈጥሮት የነበረው መንፈስ በመፍጠር ሃገር ማፍረስ ካልሆነ በስተቀር ኣዲስ የተሃድሶ እንቅስቃሴ የሚመራበት በጋራ የሚያምንበት Synergy Create የሚያደርግበት Collective Decision and Shared Knowledge (የህብረት ውሳኔ ሆነ የጋራ እውቀት) የለውም። በኣጠቃላይ የኣሁን ያለው ኣመራር የኢህኣዴግ ብልሽት የወለደው በመሆኑ ውልደቱ እና እድገቱ የተዛባ ሓይል ነው። በማለት ካጣጣለ በኋላ ‹‹ ይህንን ኣካሄድ ኣንድነት ከመፍጠር ይልቅ ሃገሪትዋ እንደሚበታትናት ኣውቀን በግዜው ሃይ ሊባል ይገባል።›› ሲል ለውጡን ማስቆም እንደሚገባ ይጠይቃል፡፡

በትግራይ ኦንላየን የኢትዮ-ኤርትራ ሠላማዊ ግንኙነት ከተጀመረ ወዲህ Egypt Induced Riots and Instability Have Changed the Political Order of Ethiopia – What is next for Egypt? በሚል ርዕስ በኤርሚያስ ሃይሉ በቀረበ ሰፊ ሃተታ ልክ በርዕሱ ላይ እንደተመለከተው ግብፅ በኢትዮጵያ ረብሻ እና አለመረጋጋት እንዲፈጠር በማድረግ የአገሪቱን ፖለቲካ ሥርዓት ለውጣለች ቀጣዩ እርምጃዋስ ምን ይሆን ሲል ይጠይቃል፡፡ በተለይ ይህ መጣጥፍ ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴን ግንባታ መጀመሯን ተከትሎ ግብፅ የኢትዮጵያን ውስጣዊ ድክመት በሚገባ በማጥናት ታላቅ ኢትዮጵያን የማዳከሚያ ስልት (“Grand Ethiopian Destabilization Strategy”) በመንደፍ አገሪቷን በግብፅ ተላላኪዎች እንድትሞላ አድርገዋል፡፡ቀጣዩ ግባቸውም የግድቡን ግንባታ ማስቆም ነው፡፡ ይህን ጥያቄ አልቀበል ቢሉ ግብፅ በተላላኪዎቿ በኩል ብጥብጥ ታስነሳለች እያለ ይቀጥላል፡፡ የሚገርመው ይህ ለውጥ እንዲመጣ በፀሀፊው ገለፃ መሰረት ግብፅ በፕሬዜዳንት ኢሳያስ፣ በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ በዳውድ ኢብሳ እና ኢሳት፣ ኦኤምኤን፣ ቢኤንኤን የመሳሰሉ ሚዲያዎችን መጠቀሟን ያወሳል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ የትህነግ አመራሮችን በማግለል የግብፅን መንግስት የሚደግፍ አሰላለፍ መፍጠሩን በሰፊው በማውሳት በአጭሩ በርካቶች ከቤታቸው ወጥተው በቀረቡት፣ ቁጥራቸው ያልታወቀ አካላቸውን በገበሩበት፣ ሺዎች በስቃይ እና እንግልት ውስጥ አልፈው ያመጡትን የለውጥ ጅምር የግብፅ መንግስት ኢትዮጵያን ለማዳከም የወሰደው እርምጃ ነው በማለት ይህንኑ አካሄድ ለመቀልበስም ለጠ/ሚኒስትሩ ምመክራቸው ማናቸውም የለውጥ እርምጃን ከመውሰዳቸው በፊት ከትህነግ (TPLF) ጋ ሠላም ማውረድ ያለባቸው መሆኑን ነው በማለት ሐተታውን ይቀጥላል፡፡

የመቀሌው ዩንቨርስቲ መምህሩ እና የአረናው አመራር አብርሃ ደስታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበለጠ አወዛጋቢነቱ እንደቀጠለ ሲሆን ‹‹ ወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በህወሓት ሰበብ ተጋሩን ማዳከም ላይ ያለመ ነው። በ”መደመር” ስም ፍቅር ሳይሆን ጥላቻ ተሰብኳል። አንድነት ሳይሆን መለያየትን ተሰብኳል። ጅብ ገለመሌ እየተባለ የተጋሩን ሞራል ለመንካት ተሞክሯል። ተጋሩን ያገለለ ስምምነት ሊፈረም ነው። እንዲጠቃ የተፈለገው ህወሓት ሳይሆን ትግራይ ነው። ከሰኔ 16 በኋላ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች አንድነት የሚያጠናክሩ ሳይሆን የሚከፋፍሉ ናቸው። በዚህ አካሄድ ሰላም ሊሰፍን አይችልም። በኦሮምያ ክልል (ቄሮ) አለመረጋጋት ሊኖር ይችላል። በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መካከል ግጭት ሊከሰት ይችላል። ስለዚህ ተጋሩ በተቻለ መጠን ሀገራችሁ ግቡ።›› እስከ ማለት ደርሷል፡፡

በአንድ ወቅት የመለስ ዜናዊ ጓድ እና አማካሪ የነበረው የትህነግ (ሕወሓቱ) ፕሮፌሰር ተኮላ ሀጎስ በአይጋፎረም ላይ ዶ/ር ዐብይ የትግል ጓዶቹን እየዘነጋ ነው በሚል ከወቀሱ በኋላ በኢትዮጵያ ያለው ችግር ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊት መከላከያው ገብቶ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ በማድረግ እንደ ዶ/ር ዐቢይ አይነት ቀን ቀን በአደባባይ ትላልቅ ሃሳቦችን እየሰበከ ማታ ማታ ከቀይ ሽብር መሪዎች (ደርግ) እና የተገንጣይ ንቅናቄ አባላት ጋር በመረዳዳት የነፃነት ጓዶቹን ለማስወገድ የሚዘጋጅ መሪ አያስፈልግም። የአስቸኳይ ጊዜ ማወጅ አያስፈልግም፡፡ መከላከያው አገሪቱን በቁጥጥር ስር እንዲያውል ነው የምወተውተው በማለት በግልፅ መከላከያው ኢትዮጵያን በወታደራዊ ቁጥጥር ስር ያደርግ ዘንድ የአደባባይ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ያውም የትህነግ ሰዎች በሚያዘወትሩት አይጋ ፎረም በኩል፡፡

ግንቡን እናፈርሳለን፤ ድልድዩን እንገነባለን በሚል መርሕ በአሜሪካ በሚካሄደው የዶ/ር ዐብይ ከዲያስፖራ ጋ በሚያደርጉት ምክክር ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የነበረው የትህነግ ቀንደኛው ደጋፊ አሉላ ሰለሞን ዶ/ር ዐብይን Con Artist (አስመሳይ አጭበርባሪ) ከማለት በተጨማሪ ‹‹ ይሄ አገር ጭልጥ ወደ አለ አምልኮ ግለ ሰብዕ እያመራ ነው።›› በማለት ከወዲሁ በአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ዙሪያ ሰፊ ተቃውሞን እየሰነዘሩ ካሉ ኮ.ካዎች መካከል አንዱ ሲሆን በተለይ ምንጮች የአጋዛያን እንቅስቃሴ መሪው ተስፋፅዮን ትግራይ እንደሚገባ ነግረውኛል በማለትም በትግራይ እና በኤርትራ ያሉ የትግርኛ ተናጋሪዎች የጋራ መንግስትን ስለመመስረት ስለሚደረገው እንቅስቃሴ ሽፍን መስጠቱን መርጧል፡፡

Brief road map for Tigrai and TPLF, Tigrai First በሚል ርዕስ በትግራይ ኦንላየን በቀረበ ሌላኛው ሓተታ ብርሃኔ ካህሳይ የተባለው አፍቃሪ ትህነግ በአዲሱ ጠ/ሚኒስትር በርካታ የለውጥ እርምጃዎች እየተወሰዱ ቢሆንም ‹‹ራስ ወዳድ›› ብሎ በፈረጃቸው ዶ/ር ዐብይ ‹‹ለትህነግ ቅርበት ያላቸው ወታደራዊ ሰራተኞች እና ሲቪሎች

ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ ተባረዋል፡፡ አንዳንዶቹም በሸፍጥ ክሶች እንዲታሰሩ ተደርገዋል›› በማለት በለውጡ አመራር በተወሰዱ እርምጃዎች የተነሳ የትህነግ (TPLF) የኢህአዴግ አባል ሆኖ የመቀጠል ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል በማለት ወደ አማርኛ ሲመለስ ‹‹አጭር ፍኖተ ካርታ ለትግራይ እና ህወሀት፣ ትግራይ ትቅደም›› የሚል ትርጓሜ ባለው ፅሁፍ በስፋት በማተት ‹‹ ትህነግ ኢህአዴግን ለመልቀቅ ማሰብ ያለበት ጊዜ አሁን ነው፡፡›› ሲል በዚሁ ብቻ ሳይገታም ትህነግ ሙሉ ትኩረቱን ‹‹ትግራይ ትቅደም›› መርሕ በክልሉ ላይ እንዲያዞር ያሳስባል፡፡

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ‹‹የህዝብ ለውጥ ፍላጎትን ማንም አያቆመውም!›› በሚል ርዕስ በቅርቡ ይፋ አድርጎት በነበረው ሳምንታዊ የመንግስት የአቋም መግለጫ ‹‹ የህዝብን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ የተጀመረው ፈጣን ለውጥ ተጨባጭ ስኬቶችን ማስመዝገብ በመቻሉ አሁን ላይ ለውጡን ማንም ሊያቆመው በማይችለው ደረጃ ላይ ደርሷል። ባለፉት ጥቂት ወራት መንግስት አገራዊና ከባቢያዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ እየወሰዳቸው ባሉ እርምጃዎች ፈጣንና ተጨባጭ ውጤቶች በመመዝገብ ላይ ናቸው።›› ሲል በማተት ለውጡ በህዝብ ጥያቄ መምጣቱን ያትታል፡፡ ነገር ግን ለውትሮ መንግስት ያለውን ሁሉ እመኑ እያሉ እንደበቀቀን የመንግስት ፕሮፓጋንዳን በመደጋገሙ የሚታወቁት እና በመካሄድ ላይ ያለውን ለውጥ በፅኑ የሚቃወሙ የትህነግ ደጋፊዎች ለውጡን ከቀለም አብዮት እስክ ግብጽ መንግስት፤ ከሲአይኤ እስከ አቶ ኢሳያስ አማካኝት ኢትዮጵያን ለመበታተን የተከናወነ ሴራ ስለመሆኑ ይፈርጃሉ፡፡

መንግስት ስለለውጡ እንዲህ ሲል ያወሳል፡፡ ‹‹ በርካታ የህግ ታራሚዎች በይቅርታ ከእስር ተለቀዋል፣ በአገር ውስጥ ከሚገኙ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር መልካም ግንኙነትን መፍጠር ተጀምሯል፣ በትጥቅ ትግል ላይ የተሰማሩ ሃይሎችም ሰላማዊ የትግል መስመርን ተቀላቅለዋል፣ በውጭ አገር የነበሩ ሚዲያዎች በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ወደ አገር ቤት መመለስ ጀምረዋል፣ የዳያስፖራውም የፖለቲካ አተያይ መቀየር ጀምሯል፣ ከኤርትራ ጋር የነበረው ሞት አልባ ጦርነትም መቋጫ በማግኘት ላይ ነው። ›› ይሁን እንጂ የትህነግ ደጋዎች ግን ሙሉ በሙሉ ለውጡ ትህነግን ያገለለ እና ሆነ ብሎ ትግራይን ለመጉዳት እንደተደረገ አድርገው ብቻ መሳሉን መርጠዋል፡፡ ለዚህም ትግራይን ከመገንጠል ጨምሮ መፍንቀለ መንግስት እንዲካሄድ ጥሪ እያደረጉ ነው፡፡ መንግስት በበኩሉ ለውጡን የሚቃወሙትን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፡፡ ‹‹እየተካሄደ ያለው አገራዊ ለውጥ ቀድሞ ለፈጸሙት በደልና ጥፋት ተጠያቂነትን ያስከትልብናል ወይም ቀጣይ ህገ ወጥ የሆነውን የጥቅም ማጋበሻ መንገድ ይዘጋብናል የሚል ስጋት የፈጠረባቸው አካላት እንዳሉ መገንዘብ ተችሏል። በመሆኑም እነዚህ ቡድኖች የህዝብን የለውጥ ፍላጎት ለማደናቀፍ እስከታችኛው እርከን በዘረጓቸው የጥፋት መረቦቻቸው በመጠቀም በረቀቀና ውስብስብ በሆነ መንገድ የለውጥ ሂደቱን አቅጣጫ ለማስቀየር ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።›› ሲል ይወቅሳል፡፡ በርግጥ ከእነዚህ በጭፍን የለውጡን ተቃውሚዎች ዙሪያ እየተወሰ ስላለው የመቀነስ እና ለውጡን በውጭ ሃይሎች የመጣ መፈንቀለ መንግስት አድርጎ ማውሳት ምን አልባት ወደፊት በትህነግ ሊወሰድ የሚችለውን እርምጃ ጠቋሚ ሊሆን መቻሉ ከዚህ ቀደም ጋዜጠኞችን ሆነ የእምነት አባቶችን ሳይቀር በግፍ ለማሰር ሲወጠን ይወሰዱ የነበሩ ስም የማጥፋት ፕሮፓጋናዳዎችን እና ዶክመንተሪዎች ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ግን ከዚህ ሁሉ የለውጡ እርምጃ ላይ ከሚቃጡ የጭፍን ተቃውሞዎች በተለየ እንደ ክብሮም አድሐኖም ያሉት በትግርኛ የሚፃፉትን መስመር የሳቱ ሐሳቦች ጭምር ወደ አማርኛ በመመለስ ሕዝብን ከሕዝብ ለመለያየት የሚደረገውን ሙከራ ለማስቀየር እያደረጉ ያሉት ጥረት በተስፋ ሰጪነቱ ሊወሳ የሚገባው ነው፡፡

ከኤርትራ ጋ ሠላማዊ ግንኙነት በተጀመረበት በዚህ ሰኣት ስለመገንጠል ማውራት የጤንኝነት ሐሳብ አይደለም፡፡በሌላም በኩል በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ትርፉ ኪዳነማርያም ፡፡ “ለውጡ በትግራይም ይመጣል። ለውጡ በሕወሓት ውስጥም ይመጣል። የትግራይ ሕዝብ እየተናገረ ነው። ለውጥ ያስፈልጋል። .. እጁን መሰብሰብ ያለበት ኃይልም እጁን እንዲሰብስብ ይደረጋል የሚል ጥብቅ እምነት ነው ያለኝ።” ያሉት ነገር እውን የሚሆን ከሆነም ምን ሊከሰት እንደሚችል ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ እስከዛው ግን ጆና ጎልድበርግ እንዳለው መረጃ በሚመስሉ ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን በማሳሳት የቅነሳ እና ለውጡን ለማስቆም የሃይል እርምጃ መምረጡ የሚኖረው ጊዜያዊ እና የረዥም ጊዜ ውጤቱ የከፍ መሆኑን በመገንዘብ አሰላለፍን ማሳመር የተሻለው መንገድ ነው፡፡ ከምንም በላይ ለውጥ የማይለውጥ ብቸኛው ሕግ መሆኑን በመረዳት ጊዜው ካለፈበት የፍረጃ እና ሌላውን የማጥላላት ፕሮፓጋንዳ ታቅቦ ለተሻለ አገር ዘመን ተሻጋሪ ሐሳብ ማቅረቡ የውዴታ አገራዊ ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡

LEAVE A REPLY