የአንድ የአድቮኬሲ ውይይት ላይ ነው፡፡ ተናጋሪው ኬንያዊ ነው፡፡ በሲቪል ማኀበራት ከፍተኛ ልምድ ያለው ስመጥር እንደሆነ ተነግሮናል፡፡ ሰብዓዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች የበለጠ እንዲከበሩ አረማጆች መከተል ያለባቸው ስትራተጂ እና ከዓለም ዙሪያ የተገኙ ውጤታማ ተሞክሮዎች እየነገረን ነበር፡፡ ኬንያዊ ተናጋሪ አንደኛው ስልት የፖለቲካ እስረኞችን ስም ማጉላት የፖለቲካ ኮዝን ወደፊት ለማራመድ ይጠቅማል አለ፡፡ በጣም ገረመኝ፡፡
የሞራል ጥያቄ አነሳኹኝ፡፡ ይህ ነገር እንዴት ይሆናል እስረኛው እየደረሰበት ያለውን መከራ ለምን ለፖለቲካ ዓላማ ማዋል ልክ ነው ወይ? ብዬ ጠየኩኝ፡፡ ሰውዬው እንግሊዘኛዬ ይግባው አይግባው አላውቅም ስለ የትኛው ሞራል ነው የምታወራው ብሎ ጥያቄዬን አጣጣለብኝ፡፡ there is no moral issue here አለኝ፡፡ በኬንያ እንግሊዘኛ ስላንግ ሹዋዋ? Sure? ብዬ ጥያቄየን ደገምኩኝ፡፡ ሰውዬው ኮስተር ሲልብኝ ምን አልባት ከተረዱኝ ብዬ በአዳራሹ ውስጥ ያሉትን ኢትዮጵያውያን በአይኖቼ ተማጸንኩኝ፡፡ እነርሱም የስልቱን ጥሩነት የሚያጠናክር ሐሳብ ሰነዘሩ፡፡ በልዩነት ወጣኹኝ፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሚደረጉ የአድቮኬሲ ስራዎችን በጎሪጥ እንዳየሁኝ አለኹ፡፡ በወቅቱ እስር ቤት የነበረችውን ርዕዮት ዓለሙን እያሰብኩኝ ተብከነከንኩኝ፡፡ ለፖለቲካ ዓላማዬ ነው እንዴ ቃሊቲ ሄጄ የምጠይቃት ብዬ ራሴን ጠየኩኝ፡፡ ያለወንጀሏ በእርስ መንገላታቷ ከሚያሳስበኝ በቀር ምንም የኋላ አጀንዳ እንደሌለኝ ስረዳ ተጽናናኹኝ፡፡ ኬንያዊው ቋንቋ ወይም የባህል/እሴቶች ልዩነት ምክንያት ተለያይተን ሊሆን ይችላል ግን የሀገሬ ሰዎች ይህ እንዴት አልገባቸውም ብዬ አዘንኩኝ፡፡
የፖለቲካችን ባህላችን የዚህ መርዛማ ልማድ ተጠቂ ነው፡፡ ሰው ሰብዓዊ መብቱ መገፈፉ፣ ለጥቃት መጋለጡ፣ ለመከራ እንግልት ብቻ መጋለጡ ብቻ ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ሳንፈልግለት የሆነው ልክ አይደለም በሚል ልንተባበር በተገባ ነበር፡፡ ሰው አካሉ ሲጎድል ነፍሱን ሲያጣ የእሱን አካል መጉደል ነፍስ መጥፋት እንዴት የፖለቲካ ትርፍ ሊያስገኝልን እንደሚችል በማሰብ መንቀሳቀስ አግባብ አይደለም፡፡ አይጠቅመንም ወዴትም አያደርሰንም፡፡
ብዙዎቹ የዘውግ ፖለቲካ ነጋዴዎች የዚህ አይን ያወጣ አውሬኔት አቀንቃኝ ናቸው፡፡ ለተጎዳው ሰውዬ ሳይሆን የሰውየውን ስም በማንሳት የእነርሱን የፖለቲካ ዓላማ እንዴት ማሳካት እንዳለባቸው የሚያሰሉ ናቸው፡፡ ለይምስል ሲጮኹ ይታያሉ፤ ነገር ግን ወገኔ ስለሚሉት ሰው ጉዳት ለአፍታ እንኳን አይጨነቁም፡፡ በዚህ ምክንያት ከእነርሱ ወገን በሆነ ሰው ላይ አሰቃቂ ጉዳት ወይም መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰት እንዲፈጸም የሚመኙ ናቸው፡፡
ሰሞኑን በአማራ ክልል የሞቱ ወገኖቻችንን ለፖለቲካ ትርፍ ማካበቻነት ለገበያ ቀርበዋል፡፡ የትግራይ ክልል የማኀበራዊ ሚዲያ ሰራዊት የዐቢይ አሕመድን ሪፎርም ለመቃወሚያነት እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ሪፎርሙ ከወገኖቻችን መሞት ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም፡፡ ይህን የፈጸሙ አውሬዎችን ተከታትሎ መያዝ በስራ ላይ ባለው የወንጀል ሕግ መጠየቅ ይገባል፡፡ ከዚያ በተረፈ የሪፎርሙ አካል የሆኑትን የአማራ ክልል ባለስልጣነት እና ሪፉርሙን ራሱን ለመተንኮስ መሞከር ለሟቾቹ ምንም እንዳላዘንን ያሳብቅብናል፡፡ የፈሰሰው የንጹኃን ደም የተቋረጠ አበል ማስቀጠያ እና የዘረኝነት መንጋ መቀስቀሻ መሆን የለበትም፡፡
ፍትሕ ለተጎዱ ወገኖቻችን፡፡ ወንጀለኞች ይጠየቁ፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ምንም ስጋት በሰላም በመላው ኢትዮጵያ በሰላም የሚኖርበት ስርዓት ይዘርጋ፡፡ መንግስት የዜጎቹን ደኅንነት ይጠብቅ፡፡