የአብዲ ዒሌ እብደት /መሳይ መኮንን/

የአብዲ ዒሌ እብደት /መሳይ መኮንን/

ሰበር ዜናውን ኢሳት ላይ እንዳየሁ ነው ወደዚህ የመጣሁት። የሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጂጂጋ ሙሉ በሙሉ በመከላከያ ሰራዊት እጅ ገብታለች። የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ዋና ዋና የከተማዋ ክፍሎች በፌደራሉ መንግስት ቁጥጥር ስር ገብተው ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው። ጂጂጋ ያለው ነገር ግልጽ አይደለም።

አብዲ ዒሌ እያበደ ነው። እንደሰማሁት የሶማሌ ክልልን ከእናት ሀገሩ እገነጥላለሁ ብሎ ሊያውጅ አፉን በልቶታል። ካቢኔውን ለዚሁ ጉዳይ ትላንት ምሽት እንደሰበሰበው መረጃውን አግኝቼአለሁ። የፌደራል መንግስቱ ቁንጥጫ ሲጠነክርበትና ህዝቡም አይንህን ለአፈር ሲለው የፈረደበትን ”እንገነጠላለን” ቀረርቶ እያሰማ ነው። የጡት አባቱ ጄነራል ኳርተር ያስጠናው አንድ ነገር ቢኖር ይህቺው አንቀጽ 39 ናት። አርጩሜ በቀመሰ ቁጥር የሚመዛት የተለመደች ዲስኩር። ለአብዲ ዒሌ ህግ ከቃል ያለፈ ትርጉም የለውም። አንቀጽ 39ኝን እየጠቀሰ ማስፈራራት ለዘመናት የተጠቀመው ስትራቴጂ ነው። ዘንድሮም አልቀቀም።

አብዲ ዒሌ አፍንጫው ስር የሚያሸተው ውድቀቱ ደም እንዳስከረው ውሻ እያቅበዘበዘው ነው። የሶማሌ ኢትዮጵያውያንን ሰብዓዊ ጋሻ በማድረግ የአብይን አስተዳደር ለማስጨነቅ መዘጋጀቱን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። ትላንት ምሽት የሰበሰበው ካቢኔው ምን ውሳኔ እንዳስተላለፈ ባይታወቅም የአብዲ ዒሊን ቅዥት ይቀበላል ተብሎ የሚገመት አይደለም። አዝማሚያው ያላማራቸው ዶ/ር አብይ ዛሬ መከላከያ ሰራዊቱ ጂጂጋን እንዲይዝ አድርገዋል::

አዎን!ሶማሌ ክልል ተቃውሞው አገርሽቷል። ህዝቡ ቆርጧል። የአብዲ ዒሌን አስተዳደር ፈንቅሎ ለመጣል የመጨረሻውን ምዕራፍ ተጥግቷል። አብዲ ዒሌ ህወሀት ላይ ጣቱን ከቀሰረና የቀድሞውን ደህንነት ሃላፊ ጌታቸው አሰፋ ላይ ሃጢያቱን ከደፈደፈ በኋላም ከተጣባው የመግደል አመል አልተላቀቀም። ጄል ኦጋዴንን ዘጋሁ በሚል ዕለም ዓቀፉን ማህብረሰብ ለማደናገር የሄደበት ርቀት ከእዚያ ከጂጂጋ የሚያስወጣው አልነበረም።

አብዲ ዒሌ ለዶ/ር አብይ ብርቱ ፈተና መሆኑ ሲጠበቅ ነበር:። ህወሀት ይሄን ሰው በመጠቀም የጥፋት ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ሲገለጽ ቆይቷል። በእርግጥም ያኮረፈውና መቀሌ የመሸገው የህወሀት ቡድን እጅና እግሩ ቢቆረጥም ምላስና ገንዘቡ ግን አልተነካም። ለውጡን ለመቀልበስ እንቅልፍ አጥተው ማደር ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል። ከሰሜን እስከደቡብ: በምስራቅም በምዕራብ እሳት በመጫር ኢትዮጵያን የቀውስ ሀገር በማድረግ የዶ/ር አብይ መንግስት ያልተረጋጋ: ሰላም የራቀው አድርጎ ማሳየት የህወሀት የሽንፈት ፓለቲካ መገለጫ ሆኗል። በሰሜን ጎንደርም የቅማንትን ካርድ በመሳብ አደገኛ ጨዋታ ጀምራል:: በረከት ስምዖን በሰው ደም እድሜውን ለማርዘም ጭልጋ እየተመላለሰ መሆኑ ተስምቷል። ህወሀት በአንዳንድ የሀገሪቱ አከባቢዎችም ተመሳሳይ ግጭት በመፍጠር ላይ ተጠምዷል።

የአብይ አስተዳደር ከያቅጣጫው ጫና እየበረታ መጥቶበታል። እርምጃ እንዲወስዱ እየተጠየቀ ነው።ከኢንጅነር ስመኘው ግድያ በሃላ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ እየገፋ የመጣውና ህግን እንዲያስከብሩ እየተደረገ ያለው ግፊት ተጠናክሯል። አፋጣኝ ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮች በደህንነት መስሪያ ቤቱ መዝገብ ቤት ተከማችተው እንደሚገኙም ይነገራል። በሀገር ላይ ከፍተኛ በደልና ወንጀል የሰሩ በተለይ የህወሀት መሪዎችን ለማሰር የሚያስችል በቂ መረጃና ማስረጃ ተጠናቅሮ ማለቁ ተሰምቷል። እነዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፊርማ የሚጠብቁ ትልልቅ ጉዳዮች በቶሎ ተግባራዊ ካልተደረጉ በእሳቸው ላይ መልሶ ከመባረቅ አንስቶ ሀገሪቱን ወደ ትርምስ እንዳይከታት ስጋቱ ከአፍንጫ በር ስር የሚሰነፍጥ ሆኗል።

በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን ማረጋጋቱና የበለጠ ቀውስን ከሚፈጥሩ ውሳኔዎች ለጊዜው መራቃቸውን የሚደግፉ ሰዎች አሉ። መቀሌ መሽጎ የሚያለቃቅሰው የህወሀቱ ቡድን እጅ ባልሰጠበትና የመረበሽ አቅሙ ባልሟሸሸበት: አሁንም ከጥፋት መንገዱ ላይ የቆመው የትላንቱ መንግስት የዛሬው ሽፍታ ቡድን እያለ ከበድ ያሉ እርምጃዎችን ባይወስዱ ይመረጣል የሚሉ በርክተዋል። ህወሀት ከቤተመንግስት ተባረረ እንጂ አልሞተም። ከእንግዲህ ቤተመንግስት የመግባት እድሉ የማይታሰብ ቢሆንም የጥፋት ሃይል ሆኖ ለጥቂት ጊዜያት መቀጠል የሚያስችል አቅም እንዳለው ይታወቃል።

ህወሀት አረናዎችን ከጎኑ በማሰለፍ መቀሌ ላይ እየመከረ ነው። ብዙ ሚስጢራዊ ስብሰባዎች በመካሄድ ላይ ናቸው። ወይ እንከባበር አልያም እንበታተን የሚል መፈክር ከመቀሌ ክፍ ብሎ ይታያል። ህወሀቶች እርምጃው ወደ እነሱ ከመምጣቱ በፊት ሌላው ጋ ቀውስ መፍጠርን እንደስትራቴጂ እየተጠቀሙ ነው። ጂጂጋ ጥሩ ቤንዚን ናት። ትንሽ እሳት ካየች ትቀጣጠላለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጂጂጋ ላይ እየወሰዱ ያሉት እርምጃ ከሚመጣው አደጋ አንጻር ተገቢ ይመስላል። አብዲ ዒሌ የመጨረሻ ጥይቱን ሊተኩስ መዘጋጀቱን የሰሙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቀድመው መከላከያ ሰራዊታቸውን አስገብተዋል። ምንም እንኳን በህገመንግስቱ የመገንጠል መብት ውስብስብና ዓመታትን በሚፈጅ ሂደት የሚከናወን ቢሆንም ህዝቡን ውዥንብር ውስጥ ለመክተትና ሰላም ለማደፍረስ በቂ ሰበብ መሆኑ አይቀርም። የህወሀት ስትራቴጂ ሰላም ማሳጣት ነው። መንግስትን መረበሽ ነው። ለውጡን ማደናቀፍ ነው። ለዚህ እንደአብዲ ዒሌ ጥሩ መሳሪያ ቢፈለግ አይገኝም።

እናም ጂጂጋ ውጥረት ውስጥ ናት። መረጃዎች በየሰዓቱ እየተቀያየሩ ነው። ሰሞኑን አብዲ ዒሌ በከፈተው መጠነ ሰፊ የማጥቃት ዘመቻ ምክንያት በ10ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ወደ ጅቡቲ ሸሽተዋል። የአብዲ ዒሌ ጸሀይ እየጠለቀች ቢሆንም በቀላሉ እጅ አልሰጥም እያለ ነው። መቀሌ የመሸገው የህውሀት ቡድን በገንዘብና በፕሮፖጋንዳ ከአብዲ ዒሌ ጎን መሰለፉም ይነገራል። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የዛሬው እርምጃ የአብዲ ዒሌን ፍጻሜ ያቃርበው ይሆን?

LEAVE A REPLY