ቦ ጊዜ ለኩሉ! ዓድዋን ከትናንቱ ዘመን አሸባሪ ጋር | ከ ኆኅተብርሃን ጌጡ

ቦ ጊዜ ለኩሉ! ዓድዋን ከትናንቱ ዘመን አሸባሪ ጋር | ከ ኆኅተብርሃን ጌጡ

ቀኑ ቅዳሜ የሳምንቱ 6ኛዉ ቀን መሆኑ ነዉ። የፍራንክፈርቱ ሰማይ ዝናብ ያረገዘ ደመና አንዣቦበታል። ለይቶለት አልዘነበም። መጣሁ መጣሁ እያለ ግን ማስፈራራቱን አልተወም። የካፊያ ነጋሪቱንም እየጎሰመ ነዉ። እንደ ገጀራም ባያም ዝናብም ቢሆን ላይ ላዩን ልብስ ማርጠቡ አይቀርም። ብቻ የሚሞቅ ፀሐይም አልፈነጠቀም። ስስ ብርድና ስስ ሙቀት የተቀላቀለበት አየር እየነፈሰ ነዉ። በረደም፤ ሞቀም ግን ኢትዮጵያዉያን በዚህ ቀን በፍራንክፈርት ከተማ የማይቀሩበት ቀጠሮ አላቸዉና ከጀርመን የተለያዩ ከተሞች ወደ ፍራንክፈርት ተመዋል።

ምክንያቱ 123ኛዉን የዓድዋ በዓል ለማክበር ቢሆንም፤ በዕለቱ የሚገኘዉ የክብር እንግዳ የሁሉንም ቀልብ መሳብ በመቻሉ ነዉ። እንግዲያዉ በዓሉማ ኢትዮጵያዉያን በብዛት በሚገኙባቸዉ የተለያዩ የጀርመን ከተሞች፤ በሙኒክ፤ በኑርንበርግ፤ በበርሊን በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል። በፍራንክፈርት በተከበረዉ የዓድዋ በዓል ላይ የተገኘዉ የክብር እንግዳ በዓሉን የተለየ ድምቀት ሰጥቶታል።

ተክለ  ሰዉነቱ ከተስተካከለ ቁመናዉ ጋር እንደተጀበነ ነዉ። ፀጉሩ ገብስማ ከመሆኑ በቀር ገና ችምችም እንዳለ ነዉ። ካሳለፈዉ ዉጣ ዉረድ የበዛበት ሕይወት አንፃር እብዛም ጉስቁልና አይታይበትም። የሞራል ስብራትም አልገጠመዉም። እሱን አይቶ በጠባብ ጨለማ ቤት ዉስጥ ብቻዉን ተዘግቶበት ስለ  መኖሩ ማመን ይከብዳል። የነፃነትና የዴሞክራሲ ሐዋርያ ነዉ። ከወጣትነት ዘመኑ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ …ላንች ነዉ ኢትዮጵያ… ብሎ ሕይወቱን እየገበረ ይገኛል። አምባገነን መንግሥትን አሽብሯል። የተገላቢጦሽ የአሸባሪነት ታርጋ የተለጠፈዉ ግን በእሱ ላይ ነዉ።

ይኸዉ … አሸባሪ… ዛሬ ግን ከየመን አየር ማረፊያ ተጠልፎ ወደ አዲስ አበባ አልተጉዋዘም። በክብር ተጋብዞ የ 123 ኛዉ የዓድዋ በዓል የክብር እንግዳ ሆኖ፤ ከአዲስ አበባ ለንደን፤ ከለንደን ፍራንክፈርት በጉጉት ተጠብቆ በሀገር ልጆቹ መካከል ለመገኘት የበቃ ነዉ። ትናንትን እያስታወሰ የሚቆዝም ፖለቲከኛ ሳይሆን ነገን በብሩህ አዕምሮ አሸጋግሮ እየተመለከተ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሙሉ ሕይወቱን ለትግሉ የሰጠ ቁርጠኛ የኢትዮጵያ ልጅ ነዉ። ሆደ ሰፊነትና ትዕግስት ሕይወቱን ተላብሰዉታል። በሰዉ ልጅ ላይ መድረስ የማይገባዉና የማይታሰበዉ ግፍና ሰቆቃ ደርሶበት አሁንም ስላለፈ ቁስል ማውሳት ፍላጎቱ አይደለም። የእራሱን ሰብዕና ሳይቀር የሚነካ አጉራ ዘለል ጥያቄ ለሚያነሳበትም ሆነ፤ በሽሙጥ አዘል ተረብ ለሚጎንጠዉ ፈገግ እያለ ተገቢዉን መልስ ከመስጠት በቀር አጉራ ዘለል የሆነ ቃል የመሰንዘር መታበይ አይታይበትም።

ከታዋቂ የፖለቲካ ሰዉነቱ ባሻገርም፤ ተናዳፊ ብዕረኛም ነዉ። ከቅንጅት መመታት ማግሥት ጀምሮ በየጊዜዉ ያዋጣቸዉ በነበሩ ፅሁፎች ጥልቅ መልክት የነበራቸዉ  መጣጥፎችን (አርቲክሎችን) በተባ ብዕሩ እየቀመረ አንባቢን መግቧል። በየጊዜዉ በሚያቀርባቸዉ ፅሁፎች ብቻም ባለመወሰን፤ በመፅሐፍ ደራሲነትም ይታወቃል። በተለይ …ነፃነትን የማያዉቅ ነፃ አዉጭ…በሚል ርዕስ አዘጋጅቶ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለንባብ ባበቃዉ ድንቅ መፅሐፍ በፅሁፍ ክሂሎቱም ያለዉን እምቅ ችሎታ ፍንትዉ አድርጎ አሳይቶበታል። ቀደም ባሉት ጊዜያትም ለሁለት ዓመታት ያህል ከወያኔ ጋር አብሮ በሰራባቸዉ ዓመታት ቆይታዉ በርካታ አወዛጋቢና አነጋጋሪ መዘዝ ያስከተለበትን …አማራ ከዬት ወዴት… የተሰኘ መፅሐፍ ለንባብ ማብቃቱ አይዘነጋም። በቅርብ ቀንም አዲሱ …እኛም እንናገር፤ ትዉልዱም አይደናገር! … በሚል ርዕስ የተከተበዉ መፅሐፉ ገበያ ለይ እንደሚዉል በጉጉት እየተጠበቀ ነዉ። ባጭሩ ጽሁፍ ነክ ተግባራቱን ለተመለከተም፤ ይህ ሰዉ ፖለቲከኛ? ወይንስ ብዕረኛ? የሚል ጥያቄ እንዲያጭር ያስገድደዋል።

መቀመጫዉን ፍራንክፈርት ከተማ ያደረገዉ በጀርመን የኢትዮጵያዉያን የዉይይትና የትብብር መድረክ ባለፉት ዓመታት በርካታ እንግዶችን አስተናግዷል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ጥቁሩ ወርቃችን ኦባንግ ሜቶ መድረኩን ጎብኝቶቷል። የዝነኛዋ ጦቢያ መፅሔት ዓምደኛ ብዕረኛዉ ሐሰን ዑመር አብደላ የአሁኑ … ኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት… መፅሐፍ ደራሲ ዩሱፍ ያሲን ስለ ኢትዮጵያዊነት የዜግነት ፖለቲካዊ ምንነት ገልጾበታል። ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላ፤ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና በመድረኩ ከኢትዮጵያዉያን ወገኖቻቸዉ ጋር ተገናኝተዉበታል። ታዋቂዉ የጀርመን ድምፅ ራዲዮ የበርሊኑ ወኪል ይልማ ኃይለሚካኤል ተገኝቶ ስለ ዓድዋ ተርኩዋል።

የዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስን በመቅደላ የመሰዋት 150ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ወጣቱ ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌ፤ የዓጼ ቴዎድሮስ የቅርብ ቤተሰብ የሆነዉ ወጣቱ ምሁር ዓቢዩ በለዉ፤ አንጋፋዉ የጀርመን ድምፅ ራዲዮ ጋዜጠኛ የነበረዉ ተክሌ የሁዋላ በእንግድነት ተገኝተዉ መድረኩን አስበዉታል። ታሪክን ዘክረዉበታል። ዛሬንም አስታምረዉበታል። ነገንም አሸጋግረዉ አሳይተዉበታል።

የአቶ አንዳርጋቸዉ ፅጌ ለዕለቱ የዓድዋ በዓል የክብር እንግዳ ሆኖ መጋበዝና መገኘትም ከላይ መድረኩ በየጊዜዉ እንዳስተናገዳቸዉ በተለያዩ ምክንያቶች አገራዊ እዉቅናን እንዳተረፉት ባለዝና ኢትዮጵያዉያን ተደርጎ የሚታይ እንጅ እንደ ሌላ አመክንዮ ተተርጉሞ የሚወሰድም አይደለም። ይኸዉ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረዉ የዕለቱ የክብር እንግዳ ወደ በዓሉ የማክበሪያ አዳራሽ ሲደርስ የነበረዉን ድባብ ለመግለፅ ቃላት ማግኘት ያስቸግራል። በሀገር ልብስ የተዋቡ ሴቶቻችን፤ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ያሸበረቁ ሕፃናት፤ ወጣቶች፤ የዕድሜ ስብጥሩ ያጠቃለለዉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንኩዋን ደህና መጣህ በማለት ልባዊ ፍቅሩን ገለጸለት። በትናንት ዘመን ካሜራን በሩቅ ነበር። ካሜራዉ ካሳደደም ጀርባን መስጠት እንጅ ፊትን (ገፅታን) ማሳየት የተለመደ አልነበረም። ነፃነቱ ከቀጠለ አሁን ያ ዘመን ያለፈ ይመስላል። እናም ሽሚያዉ ፎቶ አብሮ ለመነሳት እንጅ ሽሽት አልነበረም። እንዲያም ሆኖ የአንዳንዶቹ ወገኖቻችን ዓይኖችም ዕንባን ያስተናግዱ ነበር። ድብልቅልቅ ባለ ስሜት አንዳርጋቸዉ በመካከላቸዉ  መገኘቱን እያዩ ማመን ተሳናቸዉ። ስሜታቸዉን መቆጣጠር ያልቻሉ የትናቱን እያስታወሱ፤ አሁንም ከየመን ሰንዓ አየር ማረፊያ በእጁ ካቴና አስገብተዉ እኒያ አረመኔዎች አፍነዉ እንዴት እንደወሰዱት በምናብ ዓለም ወደ የመን በመጉዋዝ ፍራንክፈርት መሆናቸዉንም የረሱ ነበሩ ቢባል እዉነታውን መግለፅ እንጅ ማጋነን አይሆንም።

ከአቀባበሉ ወደ ዕለቱ መርኃ ግብር በመሸጋገር የመድረኩ ሊቀ መንበር (አቶ አፈወርቅ ተፈራ) አጭር የመግቢያ ንግግር ካደረጉ በሁዋላ፤ መድረኩን ለክብር እንጋዳዉ አስረከቡት። ታሪክን መነሻ በማድረግም አቶ አንዳርጋቸዉ  ዓድዋን ተነተኑት። አገራችን የብዙ ታሪክ ባለቤት ብትሆንም፤ ዓድዋ የታሪካችን ፈርጥ፤ የታሪኩ ባለቤቶችም እኛ ኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳንሆን የመላ ጥቁር ሕዝቦች መሆኑን የታሪክ ድርሳናትን በማጣቀስ ለዛ ባለዉ አንደበታቸዉ መድረኩን አስደመሙት። በሀገር የመከላከል ታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀለም፤ ዘር፤ ቁዋንቁዋ ሳይለየዉ የመሪዉን የዳግማዊ ዓፄ ምኒልክን የክተት አዋጅ ጥሪዉን ተቀብሎ ወደ ዓድዋ እንደተመመና ዘመን የማይሽረዉን አኩሪ ድል እንደተቀዳጀ በኩራት ለታዳሚዉ በድንቅ ገለጻቸዉ አስረዱት። ዓድዋ የዓለምን የቅኝ ግዛት ታሪክ ያስቀየረ፤ ጥቁር ሕዝቦች በዓለም አንገታቸዉን ቀና አድርገዉ፤ ደረታቸዉን ነፍተዉ ለመሄድ ያስቻለ የዓለም የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ በቀይ ቀለም እንዲጻፍ ያስደረገ ገድላችን መሆኑን ታሪክን እያጣቀሱ ፈትፍተዉ አቀረቡት።

የትናንት አኩሪ ታሪካችን ትናንትን እያየንበት፤ ነገንም አሸጋግረን ለመመልክት በዋቢነት የምናጣቅሰዉ መዘክራችን እንጅ ታሪክን አገር ለማፍረሻ መሣሪያነት ማዋል ዓድዋ ላይ የወደቁት የጀግኖቻችን አፅም ምንጊዜም ሊፋረደን እንደሚችል ሁሉም ሊገነዘበው የሚገባዉ ሐቅ መሆኑን አስምረዉበታል። ትንተናቸዉን በመቀጠል በታሪክ ዘመነ መሳፍንት ስለሚባለዉ የታሪካችን አካል፤ ከዚያም በሁዋላ በተከታታይ በመጡት የየዘመኑ ነገሥታት የተፈጸሙትን  አላስፈላጊ የታሪካችን ሕፀፆችና በጎ ጎናቸዉንም በማዉሳት ሁሉም ግን ታሪካችን መሆኑን ለመቀበል መቸገር እንደሌለብን አስፈላጊነቱን አብራርተዋል። ዓፄ ቴዎድሮስም ይሁኑ ዓፄ ዮሐንስ፤ ዓፄ ምኒልክም ይሁኑ ሌሎቹ ነገሥታት በዘመናቸዉ የፈጸሟቸዉን አሉታዊም ይሁኑ አዎንታዊ ተግባራት ስንመረምር መዉሰድ ያለብን ለምንፈልገዉ ዓላማ ለማዋል ብቻ እየመረጥን ታሪክን መተርጎም ሳይሆን ታሪክን በታሪክነቱ መቀበልና የሁላችንም መሆኑን መጋራት ያለብን እዉነታነቱን መጋት ግድ እንደሚል በግልፅ ቁዋንቁዋ ለታዳሚዉ አብራርተዋል።

አቶ አንዳርጋቸዉ ፅጌ የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት ለ 123ኛዉ የዓድዋ በዓል አከባበር ቢሆንም፤ እየኖርን ባለነዉ ያለፈ ታሪክ ብቻ ሳንወሰን አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደምንገኝ ደግሞ ማጣቀሱ አስፈላጊ ብቻም ሳይሆን ግድም ስለሚል የገለጻቸዉ ተከታይ ክፍል በወቅቱ የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታም ላይ ያተኮረ ነበር። በሀገራችን እየተካሄደ ያለዉ ለዉጥ ብዙ ተስፋ ሰጭ ጅምሮች እንደሚታዩበት፤ የዚያኑ ያህልም አስቸጋሪ እንቅፋቶች እየገጠሙት እንደሚገኙ በሚገባ አስረድተዋል። ለዉጡ የታሰበለትን ዓላም ግብ እንዲመታ ካስፈለገ በዋንኛነት የመሠረታዊ ተቁዋማት ግንባታ ተገቢዉን ትኩረት ሊያገኝ እንደሚገባዉና ተቁዋማት ሳይኖሩንም ለዉጡን ማስቀጠልና ዳር ማድረስም እንደማይቻል ሥጋታቸዉን ከመግለጽ አልተቆጠቡም። ችግሮች እንዳሉ ሆነዉም ለዉጡ ከእጅ እንዳያመልጥ የሁሉም ዜጎች ርብርቦሽ  አስፈላጊነት ሊነፈገዉ እንደማይገባ ማብራሪያቸዉን ከመለገስ ወደሁዋላ አላሉም። ታሪክንና ወቅታዊ የሀገሪቱን ሁኔታ ያጣመረዉን ማብራሪያቸዉን መነሻ በማድረግ ከስብሰባዉ ታዳሚዎች የተለያዩ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዉ አጥጋቢ መልስ ተስጥቶባቸዋል።

በበዓሉ አከባበር መርኃ ግብር መሠረት በተለይ …ዓድዋ… በሚል ርዕስ የቀረበዉ ሙዚቃዊ ተዉኔት ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ሰጥቶት አልፏል። ተዋንያኑ አዳራሹን በመብረቀ ድምፅ ሲያስተጋቡት ያለ ማጋነን የበዓሉን ታዳሚ ፍራንክፈርት ሳይሆን፤ አዲስ አበባ ብሔራዊ ትያትር ያለ አስመስሎት ነበር። በተዋጣለት ትወና የበዓሉን ተሳታፊም አስፈንድቀዉታል። ከትወናዉ ጎን በሥነ ፅሁፉ ዘርፍ የቀረቡት ልዩ ልዩ ሥነ ግጥሞችም ቀስቃሽና ትምህርት ሰጭም ነበሩ። በተለይ  የ 10 ዓመቱ ዕድሜ ለግላጋ  ወጣት የአብስራ ከበደ …አድዋ የማን ነዉ?… በሚል ርዕስ ያቀረበዉ ግጥም የሁሉንም ሕዝብ የዉስጥ ስሜት ኮርኩሮት አልፏል። በዚህ ስሜት የሚነካ ሥነ ግጥምም ለትዉልድ የታሪክ ርክክብና ቅብብሎሽ እያደረግን መሆናችንን ማስመስከር ተችሏል። መርኃ ግብሩ የሸፈነዉ ሌላዉ ክፍል የጨረታ ፕሮግራም ነበር። በመጨረሻም ወርቅ እጅ ባለዉ በአቶ ግርማ ወልዴ የእጅ ሥራ  የተሳለዉ የአቶ አንዳርጋቸዉን መልክ ገፅታ የሚያሳየዉን ሥዕል ለበዓሉ የክብር እንግዳ በማበርከት የበዓሉ ፍፃሜ ባማረ ሁኔታ ተጠናቁዋል።

በዚህ አጋጣሚም ሳይጠቀስ የማይታለፈዉ ድርጊት እና በዚህ ዘገባም መካተት ያለበት ቁምነገር ቢኖር፤ በዘንድሮዉ የበዓል አከባበራችን ክእንቁላልና ከቲማቲም ዉርወራ ወጣ ባለ መንገድ በአንድ አገር ልጅነት መንፈስ ከሀገራችን የኤምባሲ ቆንስል ተወካይ አምባሳደር በረደድ አንሙት በመካከላችን በመገኘትና ስለ ሀገራችን የወቅቱ ሁኔታ ገለፃ በማድረግ በዓሉን በጋራ ማክበር መቻላችን ነዉ። አቶ በረደድ ይህንንም አጋጣሚ ተጠቅመዉ ባለፈዉ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ የአዉሮፓ ጉብኝት ወቅት ፍራንከፈርት ላይ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ተፈጥሮ በነበረዉ ችግር የእሳቸዉ ቀጥታ ተጠያቂነት ባይኖርበትም፤ የቆንስላዉን ጽ/ቤት በመወከል ይቅርታ ከመጠየቃቸዉም በላይ በዚህ ዙሪያ የሚነሱ ችግሮችን ምዕራፍ ዘግተን ለወደፊቱ አሸጋግረን በማየት እጅ ለእጅ ተያይዘን ሀገራችንን በጋራ ለመለወጥ መሥራት ያለብን መሆኑን ለኢትዮጵያዉያን ወገኖቻቸዉ መድረኩን በመጠቀም አስረድተዋል።

LEAVE A REPLY