በዚህ የሐሰተኛ መረጃዎች ኾነ ተብሎ በሚፈለፈልበት፣ እውነቱ ተቆርጦ ወይም ተቀጥሎ በሚነዛበት ዘመን፥ መረጃዎችን በድፍረት ማጋራት ችግር ነው። ለወትሮው የመቻቻል አርአያ በኾነችው ወሎ ከከሚሴ ጀምሮ አጣዬ እና ማጀቴ የሚሰማው አሰቃቂ ዜናም የቱ እውነት፣ የቱ ውሸት፣ የቱ ግነት፣ የቱ ቅለት እንደሆነ መረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው።
በተለይ ጣት የሚቀሳሰሩትን ብሔርተኞች መረጃ በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል። በግጭት ወቅት የሚያባብሱ መረጃዎችን እና ስሜቶችን ከማራገብ መቆጠብም ያስፈልጋል።
በበኩሌ ያለውን መረጃ ከማውቃቸው ሰዎች ለማጣራት ስሞክር ነበር። በመጨረሻ የማጀቴ ከተማ አስተዳዳሪን (ሀብታሙ ዳምጠው) በማነጋገር ያገኘሁትን መረጃ እነኾ። ይህንንም መረጃ ቢሆን በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል። “ግጭቱ የጀመረው ኤፍራታ ግድም ነው። እኛ ከተማ ውስጥ እሁድ ሌሊቱን ብዙ ትልልቅ መሣሪያዎችን የታጠቁ ሰዎች ገብተው አገኘን። እነሱ ፉርሲ የሚባለው ቦታ ማሠልጠኛ አላቸው። እነዚህ የሠለጠኑ ታጣቂዎች ምንም ሥልጠና ያልወሰዱ ገበሬዎች ላይ ተኩስ ከፍተው ከፍተኛ ጉዳት አደረሱ። 17 ሰዎች ተገድለዋል፤ ከ20 በላይ ሰዎች ቆስለዋል። አካባቢው ኦሮሞዎቹ እና አማራዎቹ አብረው በሠላም ለዘመናት የኖሩበት ነው። እነዚህ ታጣቂዎች ኦሮሚኛ ተናጋሪዎች ናቸው። ማጀቴ የኛ ነች ነው የሚሉት። አሁን መከላከያ ገብቷል፤ ግን እንደምንጠብቀው እየረዱን አይደለም። እንዲታኮሱልን አንፈልግም ግን ታጣቂዎቹን ማስወጣት አለባቸው” ብለውኛል።
መንግሥት እና የፀጥታ ኀይሉ ከግጭት በኋላ እሳት ማጥፈሰት ላይ ሳይኾን መከላከል ላይ መሥራት አለባቸው።
(በግፍ ለተገደሉት አፈሩ ይቅለላቸው፤ በዚህ ወቅት ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ ልባዊ መፅናናትን እመኛለሁ።)