1. የፌደራል ኦዲተር ገመቹ ዲቢሶ እምቦጭ አረም በሐይቆች፣ ሃይል ማመንጫ ግድቦችና ወንዞች ላይ እያደረሰ ላለው ጥፋት ፌደራል መንግሥቱን ተጠያቂ ማድረጋቸውን ሸገር ዘግቧል፡፡ የኢትዮጵያ ብዝኻ ሕይወት ኢንስቲትዩትና የቀድሞው ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚንስቴር ጉዳዩ በቀጥታ የሚመከከታቸው የፌደራል መስሪያ ቤቶች ቢሆኑም አረሙን ለመከላከል በጥናት ላይ የተመረኮዘና የተቀናጀ ስትራቴጅ አልነደፉም፤ ተገቢውን ትኩረትም አልሰጡትም፡፡ እምቦጭ ባሁኑ ጊዜ በጣና፣ አባያ፣ ጫሞና ዝዋይ ሐይቆች፣ በአባይ፣ ባሮና አዋሽ ወንዞችና በቆቃና አባሳሞል ግድቦች ላይ ተንሰራፍቷል፤ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይም አደጋ ጋርጧል- ሲሉ አስጠንቅቀዋል ኦዲተር ጀኔራሉ፡፡ ይህን ያሉት መስሪያ ቤታቸው አረሙን ለመከላከል የተዘረጋውን ሥርዓት የገመገመበትን ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሲያቀርቡ ነው፡፡
2. የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ድርጅት ሰሞኑን ትናንት ኢትዮጵያውያን ጨምሮ 149 ስደተኞችን ከሊቢያ ወደ ጣልያን ማሻገሩን በትዊተር ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ከስደተኞች 65 ያህሉ ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ፣ ከሶማሊያና ሱዳን የሄዱ ሕጻናት ሲሆኑ 13ቱ ዕድሜያቸው ከ1 ዐመት በታች ነው፡፡ ስደተኞቹ በምግብ ዕጥረት በከፍተኛ ደረጃ የተጎዱና ለወራት በሊቢያ እስር ቤቶች ሰቆቃ ያሳለፉ ናቸው፡፡ ስደተኞቹ መውጣት የቻሉት የሊቢያና ጣሊያን መንግሥታት ከተመድ ጋር ባደረጉት የተቀናጀ ትብብር ነው፡፡
3. የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪዋ ሪታ ፓንክረስት ማረፋቸውን በብሪታኒያን የኢትዮጵያ ኢምባሲ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ ሟቿ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ መጽሃፍትን አደራጅተው ሠርተዋል፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቤተ መጽሃፍትም ሃላፊ ነበሩ፡፡ ሪታ በ92 ዐመታቸው ነው ያረፉት፡፡ በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን እንግሊዝ በጀኔራል ናፒር ዘመቻ የወሰደቻቸውን ቅርሶች እንድትመልስ በብርቱ ደክመዋል፡፡ ወይዘሮ ሪታ የዕውቁ ታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሪቻርርድ ፓንክረስት ባለቤት ናቸው፡፡
4. ዛሬ በርካታ የባሕር ዳር ዙሪያ መምህራን በባሕር ዳር ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ ሰልፈኞቹ 8 መፈክሮችን አስተጋብተዋል፡፡ የአካዳሚክ ነጻነት እንዲከበርላቸው፣ ደመወዝ ጭማሪና ጥቅማጥቅም እንዲከበር፣ ሰላሙ የተረጋገጠ የማስተማር ሁኔታ እንዲኖር፣ የአስተማሪነት ሙያ እንዲከበር፣ በሥራ ቦታቸው ለገጠማቸው አካላዊ ጉዳት የሕይወት ኢንሹራንስ እንዲሰጣቸው፣ የቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ሰልፉ ዛሬ በመላው የክልሉ ትምህርት ቤቶች እንደተካሄደ የአማራ ክልል መምህራን ማህበር ዋና ጸሃፊ ሞላ ደሴ ለDW ተናግረዋል፡፡
5. የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) አለመፍረሰም- ብለዋል መስራቹና የቀድሞው ሊቀመንበሩ ልደቱ አያሌው፡፡ ልደቱ ለኢዜአ በሰጡት ቃል እንዳሉት ለኢዴፓ ሕጋዊ ዕውቅና የሰጠው ምርጫ ቦርድም ፓርቲው እንዳልፈረሰ ገልጧል፡፡ ፓርቲውን ሊያፈርሰው የሚችለው ብሄራዊ ምክር ቤት በምርጫ ቦርድ ዕገዳ ተጥሎበታል፤ ዕገዳው ሳይነሳለት ደሞ ፓርቲውን ከሌሎች ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ማዋሃድ እንደማይችል አውስተዋል፡፡ የብሄራዊ ምክር ቤቱ አብዛኛው አባልም ከእሳቸው ጎን መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
6. ዛሬም እየተከበረ ባለው የሲዳማ ፊቸ ጨምበላላ በዓል ላይ የሲዳማ ሽማግሌዎችና አባቶች ባስተላለፏቸው መልዕክቶች ገና ስላልተመለሰው የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ ማንሳታቸውን DW ዘግቧል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማን ሕዝበ ውሳኔ የሚያካሂድበት ቀነ ገደብ ሐምሌ ላይ ያበቃል፡፡ በዛሬው በዓል በሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ በተገኘበት በሐዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ተከብሯል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሚሊዮን ማቲዎስ ለታዳሚዎች ባስተላለፉት መልዕክት በዓሉ በሰላም፣ ይቅርታና ወንድማማችነት መንፈስ ታጅቦ እየተከበረ መሆኑን አውስተዋል፡፡