ከሹክ_ወደ_ሹካ… የሴራ ሀገር ፖለቲካ‼ || ስዩም ተሾመ

ከሹክ_ወደ_ሹካ… የሴራ ሀገር ፖለቲካ‼ || ስዩም ተሾመ

ዛሬ ጠዋት የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ #ንጉሱ ጥላሁን ዶ/ር አብይ #በኦሮምኛ_ቋንቋ ንግግር እንዲያደርግ ቀስ ብለው ሹክ ያሉት ነገር ባልተዘጋው ማይክራፎን በኩል ሾልኮ የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል። ህዝቤ ደግሞ ድሮም ሽክሹክታ ይወዳል፣ አቶ ንጉሱ “ከእነ ሽመልስ ጋር ስለተነጋገርን በኦሮምኛ ንግግር አድርግ!” በማለት የተናገሩትን ዓ.ነገር ይዞ የሴራ ፖለቲካውን መሸክሸክ ጀምሯል።

ማታ ላይ የሆነ ባር ውስጥ ቢራ እየጠጣችሁ፣ ቀን ላይ ቢሆን የጆሮ ታንቡር የሚቀደው ሙዚቃ ሳይበግራችሁ ጮክ ብላችሁ እያወራችሁ ሳለ በድንገት ዘፈኑ ሲቋረጥ የሚሰማችሁ ስሜት አለ። ከመጠን በላይ ጮክ ብላችሁ እያወራችሁ እንደነበር የሚገባችሁ ሙዚቃው በድንገት ሲቋረጥ ነው። ይህን ግዜ በይሉኝታ በዙሪያችሁ ያሉትን ሰዎች ትመለከታላችሁ። ሙዚቃው ዳግም ሲከፈት ደግሞ እንደ ቀድሞ ሞቅ ያለ ጫዋታችሁን ትቀጥላላችሁ። ዘፈኑ ባይቋረጥ እኮ ነገሩ ትዝ አይላችሁም። እኔ ራሴ ይሄ ነገር ትዝ ያለኝ ከላይ የተቀስኩት አጋጣሚ ዛሬ በመከሰቱ ነው።

ለማንኛውም የሆነው ምንድነው? በዛሬው ዕለት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተደረገውን አቀባበል ያዘጋጁት ሦስት አካላት ናቸው። እነሱም የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳደር ናቸው። የፕሮግራሙን መርሃ ግብር የተዘጋጀው በሦስቱ አካላት ነው። በአንድ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ደግሞ ቦሌ ኤርፕርት እስከሚደርሱ ድረስ በዝግጅቱ ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ አያውቁም ነበር። በሌላ በኩል አዘጋጆቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማርኛ፣ ኦሮምኛ እና ትግሪኛ ቋንቋ ንግግር እንዲያደርጉ ቀድመው ተስማምተዋል።

ምንአልባት ጠ/ሚ በአማርኛ ብቻ ተናግሮ ቢሆን ኖሮ ይሄ ሁሉ ሹክሹክታ ባልተነሳ ነበር። ነገር ግን ለዚሁ ፕሮግራም ሲባል ኦሮምኛ ብቻ የሚናገሩ ፈረሰኞች በቦታው ተገኝተዋል። እዚያ ድረስ መጥተው መሪያቸው ምን እንደተናገረ እንኳን ሳይሰሙ ቢመለሱ በጣም ነውር ነው። (አስታውሳለሁ፤ የሰኔ 16ቱ ሰልፍ ግዜ “መድረክ መሪው በአማርኛ ብቻ ይናገር” ሲሉ “በፍፁም ሞቼ እገኛለሁ” ያልኩት እኔ ነበርኩ። ጋዜጠኛ ግሩም ጫላ መድረክ መሪ እንዲሆን የተመረጠው ለዚህ ነው። ዛሬ እሱ አባቴ ብጠራው አይሰማኝም..) እሺ… ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማርኛ እና ኦሮምኛ ብቻ ቢናገሩስ? ኧረ በለው… ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትግሪኛ አቀላጥፎ መናገር እየቻለ በአማርኛ እና ኦሮምኛ ብቻ ተናገረ ይባላል። ከዚያስ… እነ ዳንኤል ብርሃኔ እና ፕሮፌሰር መድሃኔ “ኦሮማራ ዘረኛ ነው፣ ጉረኛ ነው” የሚለውን ዜማ ዳግም (Remix) ያወጣሉ።

በአማርኛ፣ ኦሮምኛ እና ትግሪኛ ስለተናገረ የሲዳማ ብሔርተኛ እንደ እነ ዳንኤል ማልቀስ አይችልም። ምክንያቱም ጠ/ሚ አብይ ሲዳምኛ በደንብ አቀላጥፎ መናገር አይችልም። ወዳጄ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጣጣው ብዙ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩን በድንገት ሰርፕራይዝ አድርገህ ንግግር አድርግ ብትለው ንግግሩ በታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ትርጉምና ፍቺ ተሰጥቶት ታገኘዋለህ። ስለዚህ ሲሆን ንግግሩን ፅፈህ ትሰጠዋለህ። ነገር ግን የዛሬው ፕሮግራም ለዚህ የሚሆን አይደለም። የትኛውም ፀኃፊ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስሜትና ሃሴት ሊሰማውና እሱ በሚፈልገው መልኩ ሊገልፀው አይችልም።

በዚህ መሰረት የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ኃላፊ ከጎኑ ቁጭ ብሎ በምን በእነዚህ ቋንቋዎች ተናገር ብሎ ቢለው አግባብና ትክክል ነው። እንዳልኳችሁ የእኛ ጣጣ ብዙ ነው። ዶ/ር አብይ ከተናገረው መልዕክት ይልቅ የተናገረው የቋንቋ ዓይነት በሚያስጨንቀው የፖለቲካ ልሂቅ ዘንድ “በኦሮምኛ ተናገር” ብሎ ማለት ግራ ያጋባል። ከዚያ ይልቅ “ፕሮግራሙን ከእነ ሽመልስ ጋር ተነጋገርን ያዘጋጀነው ስለሆነ በኦሮምኛ ጭምር ንግግር ማድረግ አለብህ” ብሎ ሹክ ማለት የግድ ያስፈልጋል። በዚህ መሃል ይህቺ ዓረፍተ ነገር በድንገት አምልጣ ስትሰማ ደግሞ የሴራ ፖለቲካ ተንታኞች ለአመት የሚበቃ ሰንቅ አገኙ ማለት ነው። ምን ታረገዋለህ; የእኛ ሀገር ፖለቲካ እንደዚህ ነው፤
“ቢናገሩ አፈኛ፣ ዝም ቢሉ ሞኝ
ቢወፍሩ ዘጦ፣ ቢቀጥኑ ወረንጦ…” አለ ጋሽ አበራ ሞላ

LEAVE A REPLY