በዶ/ር ዐቢይ ደማቅ አቀባበል ተደረገ፤ በአዲስ አባ ሥራና ትምህርት ተስተጓጉሎ ውሏል
የዓለም የኖቤል የሰላም ሎሬት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ማለዳ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደተደርጎላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ 2019 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ በመሆን ሽልማታቸውን ከትናንት በስቲያ በኖርዌይ ኦስሎ በተካሄደ ልዮ ስነ ሥርዓት መቀበላቸው ይታወሳል።
ተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬ አዲስ አበባ ሲደርሱከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች አቀባበል አድርገውላቸዋል። ለክብራቸውም 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።
በአውሮፕላን ማረፊያው የባህል ውዝዋዜ አቅራቢዎች እና የማርሽ ባንድ አባላት ለአቀባበሉ ድምቀት ሰጥተውት ታይተዋል።
ዶክተር ዐቢይ ለሰላም እና ለዓለም አቀፍ ትብብር ላደረጉት ጥረት፣ በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀው የድንበር የይገባኛል ውዝግብ በሰላም እንዲፈታ ተነሳሽነትን በመውሰዳቸው የ2019 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ እንዳደረጋቸው ኮሚቴው መግለፁ አይዘነጋም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል በሚል ከአራቱም አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ ለሚገቡ ሰዎች አብዛኛው የከተማዋ መንገዶች ከሌሊቱ 11 ሰዐት ጀምሮ ዝግ እንዲሆኑ መደረጋቸወን ተከትሎ ብዙኃኑ የአዲስ አበባ ሕዝብ ከሥራና ከትምህርት ገበታው እንዲሁም ከዕለት እንቅስቃሴው መስተጓጎሉን አቀባበሉን በተለያዮ ሥፍራዎች ተገኝቶ የተከታተለው የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ዘጋቢያችን አስታውቋል::
ዶክተር ዐቢይን ለመቀበል በፈረስና በትራንስፖርት ተጭነው ወደ ከተማዋ የገቡ ሰዎች የመዲናዋን የትራፊክ ፍሰት ከመጠን በላይ በመጨናነቃቸውና በየአደባባዮ እየቆሙ በመጨፈራቸው በተለይም ከጠዋቱ አንድ ሰዓት እስከ ሦስት ሰዐት ድረስ አብዛኛው መንገዶች ከመኪና እንቅስቃሴ ውጭ እንዲሆኑ በመደረጋቸው ተማሪና ሠራተኞች በትራንስፖርት እጦት ከመጠን በላይ ለማርፈድ መዳረጋቸውን ዘጋቢያችን ታዝቧል።
አንበሳ የከተማ አውቶቢሶች በየመውጫው አካባቢ እና በየክፍለ ከተማው ተመድበው ደጋፊዎችንና አባላቶችን ወደ ኤርፖርት እንዲያደርሱና እንዲመልሱ በመወሰኑ ግልፅ የሆነ የትራንስፖርት እጦት በመዲናዋ መከሰቱንም ለመረዳት ችለናል።
የጥምቀት በዓል የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ዮኔስኮ ወሰነ
በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የጥምቀት ክብረ በዓል ፤ በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ መወሰኑን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ገለፀ።
ድርጅቱ በኮሎምቢያ-ቦጎታ በቅርስ ጥበቃ ዙሪያ እያካሄደ ባለው ስብሰባ ላይ የጥምቀት ክብረ በዓል አከባበር “በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ” (Representative List of Intangible Cultural Heritage of Humanity)ሆኖ እንዲመዘገብ ውሳኔ አስተላልፏል።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የጥምቀት ክብረ በዓል አከባበርን፣ በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የትምህርትና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ)በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት የተጀመረው ከሁለት ዓመት በፊት መሆኑ አይዘነጋም ።
ኢትዮጵያ እስካሁን ሦስት የማይዳሰሱ ቅርሶቿን ፣ እነርሱምየመስቀል በዓል፣ ፊቼ ጫምባላላና የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ አስመዝግባለች፡፡ የገዳ ሥርዓት በ2009 ዓ.ም. አዲስ አበባ በተደረገው የዩኔስኮ ጉባኤ መመዝገቡ ይታወሳል፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት ከኢትዮጵያ ውጪ የማይዳሰስ ቅርሳቸውን ካስመዘገቡ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ማላዊ፣ ኒስማ በሚባለው ባህላዊ ምግቧ፤ ሞሪሸስ ሙዚቃ፣ ዳንኪራና ዝማሬን ባካተተው ‹‹ሰጋ ታምቡር›› በሚባለው ባህላዊ ሙዚቃዋ፤ አይቮሪኮስት ዛዑሊ በሚባለው የጉሮ ማኅበረሰብ ባህላዊ ሙዚቃና ዳንኪራ ይገኙበታል።
የጥምቀት በዓል በወርሃ ጥር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በአደባባዮች በድምቀት ተከብሮ የሚውል ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ሲሆን ፣ በዓሉ ከዋዜማው ጥር 10 ቀን ተጀምሮ ጥር 12 የሚጠናቀቅ ከመሆኑ ባሻገር ቃና ዘገሊላም በድምቀት ይከበራል።
ኢሚግሬሽን ለሁሉም ክልሎችና ከተሞች 1 ሺኅ ሞተር ሳይክሎች በስጦታ አበረከተ
የኢሚግሬሽን ዜግነትና እና ወሳኝ ኩነት ኤጄንሲ 1ሺህ ሞተር ሳይክሎችን ለሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ማስረከቡን ገለፀ።
ሞተር ሳይክሎቹ ከዓለም ባንክ በተገኘ 102 ሚሊየን 524 ሺህ 400 ብር ድጋፍ ፣ እንዲሁም ከመንግሥት ከቀረጥ ነጻ በ 56 ሚሊየን 38 ሺህ 156 ብር የተገዙ መሆናቸው ነው የተሰማው። ይህም በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ያለውን የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ እና ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል። እርዳታው በወረዳ ወሳኝ ኩነት ጽሕፈት ቤቶች የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ያስችላሉ ነው የተባለው ።
በሀገሪቱ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓት ዓለም አቀፍ መርኾችን በጠበቀ መልኩ በዜጎች ላይ የሚከሰቱ እንደ ልደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ እና ሞት ወሳኝ ኹነቶችን ለመመዝገብ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ወጥቶ ሥራ መጀመሩ አይዘነጋም።
ድምጻዊት ቤቲ ጂ ለዝግጅቱ የመረጧት የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ አባላት መሆኑን ገለጸች
ድምጻዊት ብሩክታዊት ጌታሁን (ቤቲ ጂ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማታቸውን በተቀበሉበት መድረክ ላይ ሁለት ሥራዎቿን ማቅረቧ ይታወሳል።
ሀገሬና ‘ሲንጃለዳ’ (Sin jaaladha) የተሰኘ የኦሮምኛ ሙዚቃዎችን የተጫወተችው ቤቲ ጂ መድረኩ ላይ ባቀረበቻቸው የሙዚቃ ሥራዎች፣ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መነጋጋሪያ ሆናለች።
ቤቲ ጂ በዕለቱ ሥራዋን እንድታቀርብ የኖቤል ኮሚቴ ከመረጣት በኋላ በማኔጀሯ በኩል መመረጧን እንደነገሯትና ይህም ሁኔታ ”ትንግርት” እንደሆነባት ለቢቢሲ አስታውቃለች።
“‘እኔ ነኝ የመረጥኩሽ’ ያሉትን የኮሚቴ አባል አግኝቻቸው ነበር” ያለችው ድምጻዊት ብሩክታዊት “ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ አንጋፋ ድምጻውያን ሁሉ ለይተው እኔን እንዴት መረጡኝ?” ብላ መጠየቋንና እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ድምጻውያን ሁሉ እርሷን በመምረጣቸው ደስተኛ እንደሆነች መግለጿንም በቆይታዋ አብራርታለች::
የኖቤል ኮሚቴ አባላቱ” አንቺን በመምረጣችን ደስተኛ ነኝ” ከማለት ውጪ መስፈርታቸውንም ሆነ ምክንያታቸውን እንዳልገለጹላት ያመላከተችው ወጣቷ አቀንቃኝ ቤቲ ጂ፤ “እኔም የፈጣሪ ሥራ ብዬ ነው የማምነው” ብላለች::
ድምጻዊት ብሩክታዊት በሰላም ኖቤል ሽልማቱ ላይ እንደምትዘፍን ያወቀችው የዛሬ ሦስት ሳምንት ገደማ እንደሆነ ብትናገርም፣ ለዚህ ሥራዋ ምን ያህል እንደተከፈላት ተጠይቃ ስትመልስ ብዙ አለመሆኑንና ዋናው የሄደችበት ምክንያት ልክ እንደሌሎች አንጋፋ የሙያ ባልደረቦቿ ኢትዮጵያን ለሌላው ዓለም ለማስተዋወቅ ነው ስትል ተደምጣለች።
ቤቲ ጂ “ለኔ የኖቤል ሽልማቱ ዝግጅት ፍራቻና ደስታ የተሞላበት ነበር፤ ንጉሥና ንግሥት ፊት መዝፈን በየጊዜው አያጋጥምም” በማለት የኢትዮጵያውያንን አደራ ተሸክማ ሥትሠራ ‘አበላሽ ይሆን?’ የሚል ስጋትና ጭንቀት እንደነበረባት ገልጻለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዕለቱ ሥራዋን እንደምታቀርብ እንደማያውቁና ለመጀመሪያ ጊዜ ያይዋት መድረክ ላይ ሥራዋን ስታቀርብ እንደሆነ የገለፀችው ቤቲጂ ፤ ይህ የሆነው ለእርሳቸው የኖቤል ሽልማቱን ያዘጋጁት አካላት እንደ ‘ሰርፕራይዝ’ በማሰባቸው መሆኑን ተናግራለች። በዕለቱ የነበረው ዝግጅቷን በተመለከተ በርካቶች መውደዳቸውን እንደነገሯት አስታውሳ እርሷ ደግሞ ሀገሬ የተሰኘውን ሙዚቃ ቪዲዮ ስታየው እንባ እንደሚተናነቃት ገልጻለች።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከመድረክ ሥራዋን ካቀረበች በኋላ እንዳገኘቻቸውና ” በጣም ጥሩ ሥራ ነው ያቀረብሽው፤ በርቺ” ማለታቸውን ይፋ አድርጋለች።
የሙዚቃ ሥራዎቿን እርሷ እና የኖቤል ኮሚቴው በጋራ መምረጣቸውን የምትናገረው ድምጻዊት ብሩክታዊት ጌታሁን፣ ‘ሲንጃለዳ’ (Sin jaaladha) የተመረጠበትን ምክንያት ስታስረዳ በወቅቱ ከልብሷ እስከ ሙዚቃዋ ኢትዮጵያን ለመወከል በማሰብ መሆኑን ተናግራለች። ቤቲ ጂ የለበሰችው የባህል ልብስና የፀጉር አሰራሯ ትግራይን፣ ሀገሬ ሙዚቃ አማርኛ ተናጋሪውን፣ ‘በሲንጃለዳ’ (Sin jaaladha) ደግሞ ኦሮሚያን ለመወከል አስባ መሥራቷን ገልጻለች። እጇን የተጌጠችበት የምስራቁን የኢትዮጵያ ክፍልን ለመወከል በማሰብ ይሁነኝ ተብሎ የተሠራ ነውም ብላለች።
ለኮሚቴው አባላት በሙዚቃ ምርጫዎቿ ወቅት የሙዚቃዎቹን ትርጉም በመላክ ለማስረዳት መሞከሯን በመናገርም “በነበረን አጭር ዝግጅት ጊዜ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አይቶት የሚወደው ሥራ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ” ትላለች።
‘ሀገሬ’ የሚለውም ሙዚቃ ከምን ጊዜውም በላይ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት ምድሪቷና ሕዝቦቿ በጋራ ሲሆኑ እንደሚቻል የሚገልጽና ለበዓሉም ሆነ ለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ መልዕክት የያዘ መሆኑን ትናገራለች።
‘ሲንጃለዳ’ (Sin jaaladha) ላይ ለመደነስ ሁለት ሳምንት መለማመዷን የምትናገረው ቤቲ ፣ መጀመሪያ አካባቢ ያዞራት እንደነበር፣ በኋላ ላይ ግን ለዳንሱ የሚረዳትን ሙዚቃ ካስገባች በኋላ መቀየር እንደማትችል ስለተረዳች በልምምዷ ጠንክራ መግፋቷን ገልፃለች።
ቤቲ ጂና የሙዚቃ ባንዱ ሥራቸውን ከማቅረባቸው በፊትም ሆነ በኋላ የመድረኩን እንግዶችና ታዳሚያን እጅ ሲነሱ ታይቷል። በኖርዌይ እንዲህ ዓይነት መርሃ ግብሮች ላይ ንጉሳውያን ቤተሰቦች እንዲሁም የኖቤል ሽልማት ተቀባዮች ሲኖሩ እጅ መንሳት ባህል መኖሩን አመላክታ፤ ሥራቸውን ሲጀምሩም ሲጨርሱም እጅ መንሳታቸው ለዚያ መሆኑን አረጋግጣለች። “እኛ ኢትዮጵያውያንም ተመሳሳይ ባህል ስላለን ስንሰለጥን ብዙ አላስቸገርናቸውም።” ብላለች።
የሙዚቃ ሥራዋን ከማቅረቧ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ከኖርዌጂያን ተቀባዮቿ ጋር ረዥም ልምምድ ማድረጓን በመጥቀስም፣ ከዚህ ቀደም ባለው ጊዜ ከኢትዮጵያ ባለሙያዎች ጋር በሀገር ቤት ልምምድ ስታደርግ መቆየቷን ያስታወሰችው ድምጻዊት ቤቲ ጂ፤ ልምምዶቹን ቀርጻ ለተቀባይዎቿ ትልክ እንደነበርና በአጠቃላይም የሁለት ሳምንት ልምምድ እንደፈጀባት ለቢቢሲ ገልጻለች።
በፖለቲካ ጥቃቶች ንብረታቸው ለወደመ ባለሀብቶች ብድር ተዘጋጀ
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከተለያዮ የመንግሥት ተቋማት ጋር በመተባበር በኢንቨስትመንት ተቋማት ንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት ማገገሚያ የሚረዳ ብድር ለማመቻቸት የደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ቡድን ማሰማራቱ ተገለፀ::
ከልማት ባንክና ከመድህን ድርጅቶች የተውጣጡ አባላት ጉዳት ደርሶባቸዋል የተባሉትን የኢንቨስትመንት ቦታዎች ላይ ጥናት በማድረግ የጉዳታቸውን መጠን ለይተው ያቀርባሉ ነው የተባለው:: በጥናቱ ወይም ዝርዝር ሪፖርቱ መነሻ መሠረት ለተጎጂዎች ብድሩ እንደሚመቻችም ተገልጿል::
ባለፉት ጥቂት ወራት ኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተው አለመረጋጋት በቋሚ ንብረት እና በማሽኖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የገለጸው የኢንቨስትመንት ኮሚሽን መንግሥት በ2008 እና በ2009 በኢንቨስትመንት ላይ ለደረሱ ጉዳቶች ካሳ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ አስችሏል ብሏል:: በተለያዮ ማሽኖች ላይ በደረሰው ጉዳት ባለሀብቶች ከውጭ ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ እንዲያስገቡ መደረጉም ተጠቁሟል::
በሦስት ወራት ውስጥ የ20 ቢሊዮን ብር ነዳጅ ተገዝቷል ተባለ
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በ2012 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 932 ሺኅ ሜትሪክ ቶን በላይ ነዳጅ ወደ አገር ማስገባቱን አስታወቀ::
ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ድርጅቱ በጥቅሉ 913 ሺኅ 167 ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ለገበያ አቅርቦ የነበረ ሲሆን በዚህኛው በጀት ዓመት ወደ አገር ውስጥ የገባው የነዳጅ አቅርቦት እስከ 20 ሺኅ ሜትሪክ ቶን የሚደርስ ጭማሪ አሳይቷል::
ወደ አገር ውስጥ ከገቡ የነዳጅ ምርቶች ውስጥ ቤንዚን 141 ሺኅ ሜትሪክ ቶን ፣ ነጭ ናፍጣ 577 ሺኅ ሜትሪክ ቶን እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ 190 ሺኅ ሜትሪክ ቶን በመያዝ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል:: የነዳጅ ምርቶቹ ከኩዌት፣ ከዱባይ እና ከሱዳን መንግሥታት ጋር ኢትዮጵያ ባላት የኹለትዮሽ በጅቡቲ ወደብ በኩል ወደ ሀገር ቤት የገቡ ናቸው::
በኪሳራ የሚዋልለው ልማት ባንክ በ3 ወር፣ የ2 ቢሊዮን ብር ብድር ፈቀደ
በከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ተዘፍቆ የሰነበተው ልማት ባንክ በ2012 የበጀት ዓመት ለተለያዮ ዘርፎች ኹለት ቢሊዮን አንድ መቶ ሚሊየን ብር ብድር መፍቀዱ ተሰምቷል::
ባለፉት ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ባንኩ ካጸደቃቸው ብድሮች ውጪ ከዚህ ቀደም የተፈቀዱ ኹለት ቢሊዮን ብር የሚደርሱ ብድሮችን መክፈሉም ታውቋል::
ልማት ባንኩን ለኪሳራ ዳርጓል ቀተባለው ዝናብን ጠብቆ የሚከናወን የሰፋፊ እርሻ የሚሰጡ ብድሮችን በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ አቁሟል:: ይሁን እንጂ የአበባና የወተት ልማቶችን ጨምሮ ለተለያዮ ፕሮጀክቶች 99 ሚሊዮን ብር መስጠቱን የባንኩ የእቅድና ስትራቴጂ ክፍል ሓላፊ ገልጸዋል::
በሩብ ዓመቱ የተፈቀደው ብድር አልሚዎች የራሳቸውን ሃብት ፈሰስ አድርገው ከጨረሱ እስከ ኹለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ በተለያዮ ደረጃዎች የሚከፈሉ መሆናቸው ተነግሯል:: “ባንኩ የልማት ባንክ እስከሆነና የአገሪቱ ከፍተኛ ኢኮኖሚ መሠረትም ግብርና እስከሆነ ለግብርናው የምንሰጠውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲሉ በኪሳራ የሚዋልለው የልማት ባንክ ከፍተኛ አመራር አስረድተዋል::

























