ፓርላማው አማራጭ የውሳኔ ሐሳቡን በ25 ድምፅ ተቃውሞ ዛሬ አፀደቀ

ፓርላማው አማራጭ የውሳኔ ሐሳቡን በ25 ድምፅ ተቃውሞ ዛሬ አፀደቀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 3ኛ ልዩ ስብሰባ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  ቀጣዮን ሀገራዊ ምርጫን በተያዘለት ጊዜ ማካሄድ እንደማይችል ማስታወቁን በተመለከተ የቀረቡ የመፍትኄ አማራጮችን የውሳኔ ሐሳብ፣ እንዲሁም የብድር ስምምነቶችን ተመልክቷል።

የሕግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ንዑስ ሰብሳቢ አቶ አበበ ጌዴቦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማከናወን አለመቻሉን አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በምክር ቤቱ መፅደቅን ተከትሎ፤ ቀጣይ ሕገ መንግሥታዊ የመፍትኄ ሐሳብ እንዲያቀርብ በተመራለት መሠረት ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ  ዛሬ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

በተጨማሪም የምክር ቤቱ አባላት ፤ በሕግ ባለሙያዎች ምክር ቤቱን መበተን፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ፣ ሕገ መንግሥት ማሻሻልና ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜን መጠቀም እንደሚቻል ማስቀመጣቸውን ጠቁመው፤ ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ ሕገ መንግሥታዊ ትረጓሜን መሠረት በማድረግ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ተገቢነት ያለው መሆኑንም አብራርቷል።

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 ምርጫን ማካሄድ የፌዴራል መንግሥት፣ የምርጫ ቦርድ ሥልጣንና ተግባር በመሆኑ ቦርዱ ምርጫን ለማራዘም ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ተገቢና ሕገ መንግሥታዊ ነው፤ ከዚህ ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ኢ-ህገ መንግሥታዊ ናቸው ተብሏል።

ከፓርላማው አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ማብራሪያ የሰጡት አቶ አበበ ጌዴቦ ፤ ኮሚቴው የተሰጠውን ሓላፊነት ተቀብሎ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የማይጣረስ አማራጭ የመፍትኄ ሐሳብ ያቀረበ መሆኑን ጠቁመው፤ ምክር ቤቱም የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ተቀብሎ እንዲያጸድቅ ጠይቀዋል።

ምክር ቤቱም ሕገ መንግሥታዊ የመፍትኄ ሐሳብ እንዲያቀርብ በተመራለት መሠረት የቀረበውን ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ መጠየቅ የሚለውን አማራጭ የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ በ25 ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል።

LEAVE A REPLY