ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በህዳሴው ግድብ ላይ ኢትዮጵያ ግብፅ እና ሱዳን ወደ ውይይት ለማምራት መስማማታቸው የሚደገፍ ነው በማለት መግለጫ ያወጣው በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ፤ ጉዳዩን ሩሲያ በቅርበት እየተከታተለችው መሆኑንም ጠቁሟል።
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛከሃሮቫ በግድቡ ዙሪያ የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት ውይይት ማድረግ እና ቀድሞ የተቀመጡ ዓለም ዐቀፍ መርሆችን መከተል እንደሚገባ ሩሲያ የማይናወጥ አቋም አላት ብለዋል።
በተለይም እ.ኤ.አ. በ 2015 የተደረገውን እና በግድቡ ዙሪያ የተካሄደውን የካርቱም ስምምነት ውሳኔዎች እና የዓለም ዐቀፍ ህግጋትን መሰረታዊ መርህ በተከተለ መልኩ ለአለመግባባቶች መፍትኄ መፈለግ እንደሚገባ ሩሲያ አሳስባለች።
ከታላቁ የህዳሴ ግብድ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታ እና ከውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዙ የሚነሱ ጉዳዮች፤ ከየሀገራቱ ብሔራዊ ደህንነት ፍላጎቶች እና ከአባይ ተፋሰስ ሀገራት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገቶች ጋር አስተሳስሮ ማየት እንደሚያስፈልግም የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መናገራቸውን መግለጫው አብራርቷል።

























