ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የሰብኣዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ በዚህ ወቅት ከተለያየ አቅጣጫ ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራሪያ እየተሰነዘረባቸው መሆኑን ተናገሩ።
“ዛቻና ማስፈራራት አለ፤ እኔ ግን ላለፉት ዐሥራ ሥድሥት ዓመታት ለራሴ ሞቼ ለሰው ልጆች መብት ስሟገት ነው ያሳለፍኩት። እናም ዛሬ ብሞት አዲስ ነገር የለውም። ከህሊናዬ ጋር መክሬ የገባሁት ቃለ አለ። ያ ቃል ዛሬም በልቤ ነው። የብሄር አክቲቪስት መሆን አልችልም። ቃል ኪዳኔም አይደለም ” ያሉት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ፤ አሁን ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የጄኖሳይድ ፍኖተ ካርታ እንድትቀመጥ የሚያስችል ሥራ መጀመራቸው ስጋት የገባቸው አካላት ማስፈራሪያ ላይ አተኩረዋል ብለዋል።
” ማንም እንደሚያውቀው ላለፉት በርካታ ዓመታት ከዩኤስ አሜሪካ ኮንገርስ አባላትና የሚመለክታቸው ተቋማት፣ ጄኖሳይድ ፎረም፣ ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከሰብኣዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፣ ከዓለም ዐቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፣ ከአፍሪካው ፍርድ ቤት ጋር ሥሠራ ኖሪያለሁ። አሁንም ከነዚሁ አካላት ጋር በስፋት እየሰራሁ ነው” በማለት የተናገሩት ኦባንግ ሜቶ ሕይወታቸው ቢያልፍ እንኳን ሥራው እንደማይቆም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በተመድ የጄኖሳይድ ፍኖተ ካርታ እንድትሰፍር አየተሠራ ነው ፤ ጄኖሳይድ አልተካሄደም ማለት ከሰውነት ደረጃ መውረድ ነው በማለት ያለውን እውነት በገሀድ ያስቀመጡት የሰብኣዊ መብት ተሟጋቹ፤ ከ16 ዓመት በፊት 424 አኝዋኮች በማንነታቸው ተመርጠው እንደተጨፈጨፉና ከእነርሱ ውስጥም 317 ያህሉን በደንብ እንደሚያውቋቸውም ይናገራሉ።
በጊዜው አስተማሪዎቻቸው ፣ አጎቶቻቸው፣ የወንድማቸው ሚስት፣ ባልደረቦቻቸው፣ አብሮ አደጎቻቸውና የአካባቢያቸው ሰዎች መጨፍጨፋቸውን በጥልቅ የሀዘን ስሜት ውስጥ ሆነው ያስታወሱት ሀገር ወዳዱ አክቲቪስት፤ የሁሉም ስም ዝርዝር እጃቸው በመግባቱ ዝርዝሩን እያዩ የተጨፈጨፉትን ንጹሃን ሲቆጥሩ የተሰማቸው ከባድ ሀዘን ለሰው ልጆች መብት ለመሞገት ቃልእንዲገቡ ያስገደዳቸው መሆኑን ገልጸዋል።
” አንድም የሰው ልጅ በተመሳሳይ እኔ እንዳገኘሁት በማንነታቸው የተጨፈጨፉ ሰዎችን ማንነት የሚያሳይ ዝርዝር እንዳይደርሰው ለማድረግ ፣ ለዘር ሳይሆን ለሰው ልጆች ሁሉ የሰብኣዊ መብት መከበር ለመታገል ወሰንኩ። ዛሬም እዛው ቃሌ ላይ ነኝ” ያሉት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር፣ በዚህ መሀላዬ ላይ ቆሜ የምሠራው ሥራ ማንንም ለማስቀየም ሳይሆን ለእውነት ስል እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።

























